2016-10-08 09:52:00

የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎች የተሰጠ መግለጫ።


የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎች የተሰጠ መግለጫ

 

እኛ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሪዎች እና የበላይ ጠባቂዎች፤ ሰላም በዋጋ የማይገመት የፈጣሪ ፀጋ መሆኑን እናምናለን፡፡ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ማምለክና መፀለይ የሚቻለውም አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን እናስተምራለን፡፡ ዘመን ተሻጋሪው የሃገራችን ታሪክም ከዚህ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር የተስማማ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደስታና ሀዘናችንን፣ መከራና ችግራችንን ሁሉ በጋራ በመጋራት በአብሮነት ኑረናል፤ እየኖርንም እንገኛለን፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል፤ የአካልና የመንፈስ ጉዳት ደርሷል፤ ሀብትና ንብረትም ወድሟል፡፡

እኛ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች ከዚህ ቀደም በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትርና ከሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጠናት ጋር፤ የሕዝቡ ጥያቄ በአግባቡ ተደምጦ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው መወያየታችን፣ ይህንንም አስመልክቶ በተደጋጋሚ መግለጫ ማውጣታችንና በአባል የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ለአገራችን ሰላምና መረጋጋት ጾም ጸሎት እንዲደረግ ማወጃችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሃገራችን ሰላም እየደፈረሰ መጥቷል፡፡  ይህ ደግሞ እኛን የሃይማኖት መሪዎች በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ በቅርቡ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በእሬቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ በተፈጠረው ግርግርና ሁከት ምክንያት በዜጎቻችን ላይ በደረሰው የህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት አደጋ እጅግ ጥልቅ ሐዘን የተሰማን ሲሆን፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ዘመድ-ወዳጆች  እንዲሁም ለመላው የአገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እንዲሰጥ ፈጣሪን እየተማፀንን የሚከተለውን መልዕክት እናስተላልፋለን፤

< > ሃይማኖት አስተምህሮ የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው ሲባል ክቡርነቱ ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱና ዋናው በሕይወት የመኖር መብቱ ከምንም በላይ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባው መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለማርገብም ሆነ  ሃሳብ ለመግለጥ በሚደረገው ጥረት ማንኛውም ክፍል ከምንም ነገር በላይ ለሰው ሕይወት ክፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እናሳስባለን፡፡ < > መንግስት በአገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ አካላት ሁሉ ጋር በመነጋገር፣ የሕዝቡን ብሶትና ጥያቄ በአግባቡ እንዲያደምጥና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡ < > በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው አለመግባባት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ዜጎች የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች  እንጠይቃለን፡፡ < > የአገራችን ክፍሎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የንግዱ ማህበረሰብ የሚሳተፉበት የሰላም ግብረ ኃይል በማቋቋም ብሔራዊ መግባባት፤ እርቅና የህሊና ፈውስ እንዲፈጠር ለምናደርገው ጥረት መንግስትና ሕዝባችን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ < > እምነት ተከታይ የሆናችሁ መንፈሳዊ ልጆቻችን፤ በይቅርታና በምህረት እርስ በእርሳችሁ ተቀባብላችሁ ለሰላምና ለአገር ልማት እንድትቆሙ፣ የአገራችሁ ልጆች የሆኑትን ኢትዮጵያውያንን በሙሉ እንደ ወንድምና እንደ እህት እንድትመለከቱ፣ ከጥላቻ፣ ከአድማ፣ ከሁከት እንድትርቁና ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ እንድታቀርቡ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡< > ልማቶች የአገራችን ሃብት እንደመሆናቸው መጠን በዜጎቻችን ሁሉ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን፡፡< > በላይ አሁን በሀገራችን ያለውን ግጭት ወደ ሰላም የመለወጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት መንግስት ስለሆነ በአርቆ አስተዋይነት እና አባታዊ መንፈስ ተገቢውን ሁሉ እንዲያደርግ እየጠየቅን ሕዝባችንም አገራዊ አላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡ < > ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር ለህዝብ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ የመገናኛ ቡዙሃን፣ ማህበራዊ ድህረ ገፆች እና ግለሰቦች ሕዝብን ወደ ጥላቻ፣ ግጭትና ሁከት ብሎም ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ወደ ማጥፋት ከሚመራ ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች

መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ








All the contents on this site are copyrighted ©.