2016-09-29 11:41:00

ቅዱስነታቸው "የጨለማ ጊዜያትን ማለፍ የምያስችሉን መሳሪያዎች ዝምታ እና ጸሎት ብቻ ናቸው" አሉ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር በመስከረም 27/2016 በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ስብከት በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰቱትን የጨለማ ጊዜያትን ማለፍ የምያስችሉን መሳሪያዎች ዝምታ እና ጸሎት ብቻ ናቸው እንጂ መድኋኒት ወይም የአልኮል መጠጥ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

በእለቱ ከመፅሐፈ ኢዮብ ከምዕራፍ 3.1 ላይ በተወሰደው እና ኢዮብ የመንፈስ ድርቀት በተሰማው ወቅት በአምላክ ፊት ሐዘኑን እየገለጸ እንደ ነበር በስብከታቸው መጀመሪያ ላይ ያወሱት ቅዱስነታቸው በቀጣይነትም ትኩረታቸውን እያንዳንዳችንን ስለሚያጋጥመን እና በሕይወታችን ውስጥ አንድ አንዴ ስለሚከሰቱት የጨለማ ጊዜያት እና የመንፈስ ድርቀትን ማዕከል ያደረግ ሲሆን ቅዱስነታቸው ከእዚህ ጨለማ ውስጥ መውጣት የሚያስችሉንን አንድ አንድ ነጥቦችን በስብከታቸው በጠቆሙበት ወቅት ኢዮብ በታላቅ ጭንቀት ውስጥ በነበረ ጊዜ እና ንብረቱን ሁሉ ባጣ ጊዜ እግዚአብሔርን አልርገመም ነበር ነገር ግን “በአባቱ ፊት በንዴት ገንፍሎ እንደ ቆመ ልጅ ነበር ” የሆነው ብለዋል።

“የመንፈስ ድርቀት ሁላችንም የሚያጋጥመን ነገር ነው” በማለት ስብከታቸው የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ጠንካራ ወይም መኋከለኛ ሊሆን ይችላላ. . . ነገር ግን በመንፈስዊ ሕይወት ውስጥ የሚታየው የጨለማ ስሜት፣ ተስፋ ማጣት፣ አለመተማመን፣ በሕይወት ውስጥ የብርሃን ጭላንጭል የማይታይበት ፍላጎት የጎደለው ኑሮ መኖር፣ ልባችን በከፍተኛ ሁኔታ በሐሳቦች እና በተለያዩ ነገሮች ሲላወስ. . .ወ.ዘ.ተ. በሚያጋጥሙን ወቅት ሁሉ የመንፈስ ድርቀት ነብሳችን እንደጠፋች፣ ወጤታማ እንዳልሆንን እንዲሰማን ያደርገናል፣ ይህም ውጤታማ እንዳልሆንን የሚሰማን ስሜት የሕይወትን ትርጉም እንድናጣ በማድረግ መኖር እንዳንፈልግ ያደርገናል ብለዋል።

ስለዚህም “ሞትን እንመርጣለን! ይህ ነበረ ኢዮብ በንዴት እንዲገነፍል ያደረገው። ከመኖር ይልቅ መሞትን የመረጠበት ምክንያት ይሄው ነበር፣ ከሞኖር ይልቅ መሞትን የመረጠው በእዚሁ ምክንያት ነበር።” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ልንረዳው የሚገባው ሀቅ ሕይወታችን በእዚህ ዓይነት ጠቅላላ ሐዘን ውስጥ በምትገባበት ወቅት ይህንን ጭንቀት እና ሐዘናችንን አውጥተን በምንተነፍስበት ወቅት ይብዛም ይነስም ሁላችንም የደስታ ስሜት ይሰማናል፣ በልባችን ውስጥ ምን እየተካሄደ መሆኑንም ማወቅ ይገባናል” ብለዋል።

“በቤተሰባችን ውስጥ አሳዛኝ ነገሮች አጋጥሞን ሊሆን ይችላል፣ በሽታ አጋጥሞን ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ በአጠቃላይ በጣም ከባድ ነገር ገጥሞን ጭንቀት ውስጥ ከቶን ሊሆን ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ እንደነዚህ ያሉ የጨለማ ጊዜያት በሚያጋጥሙን ወቅት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? ብለው ጥያቄን በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አንድ አንድ ሰዎች እንደ ሚያስቡት ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት የእንቅልፍ መድኋኒት ወስዶ መተኛትን የመርጣሉ ወይም ሁኔታውን ለመርሳት አንድ፣ ሁለት ወይም ሦስት ብርጭቆ መጠጥ መጠጣት ለችግሩ መፍትሄ ልያስገኝ እንደ ማይችል” ገልጸው ነገር ግን በምትኩ የዛሬው ስርዓተ አምልኮ የመንፈስ ድርቀት በሚያጋጥመን ወቅት ሁሉ እንዴት መወጣት እንዳለብን ያስረዳናል ብለዋል።

ለእዚህ ችግር ፍትሁን የሆነ መፍትሄ ለማግኜት የሚያስችለን መሳሪያ ልክ ኢዮብ እንዳደርገው ቀን ከሌሊት መጸለይ መሆኑን በማመለከት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ጌታ ሆይ ነብሴ በጣም እየተሰቃየች ነው። እኔ ብርታት የለሌኝ ሰው ነኝ ብለን  በብርታት የአምላክን በር ማንኳኳት አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው “ በሕይወታችን ብርታት ያጣንባቸው አጋጣሚዎች ስንቴ ገጠመውናል? ካሉ ቡኋላ ጌታ እራሱ እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ሁሉ ‘ጌታ ሆይ! ወደ መቀመቅ ከተህኛል። በላዬ ላይ ከፍተኛ ክብደትን ጭነህብኛል። ጌታ ሆይ ጸሎቴ በፊትህ ይድረስ’ ብለን  መጸለይ እንደ ሚገባን አስተምሮናል ብለው በመክራ እና በጨለማ ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ሁሉ መጸለይ የሚገባን ይህንን ጸሎት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ጸጥታ፣ ቅርበትን ማሳየት እና መጸለይ አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን ቅዱስነታቸው በስብከታቸው አጽኖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን አክለውም ጓደኞቻችን ሕይወታቸው ጨለማ ውስጥ በሚገባበት ወቅት ሁሉ በእነርሱ ላይ ከመጮኽ እና የተላያዩ ቃላትን መጠቀም የበለጠ እንደ ሚጎዳቸው አሳስበው በምትኩ ከላይ የተጠቀሱትን የመፍትሄ መንገዶችን እንዲከተሉ ማድረግ ግን ያስፈልጋል ብለዋል።

“በመጀሪያ የመንፈስ ድርቀት በሕይወታችን እንደ ተከሰተ እና በጨለማ ውስጥ መሆናችንን ማወቅ እንዲሁም ለምን እና እንዴት ወደ እዚህ ሁኔታ ለመግባት እንደቻልን መገንዘብ አስፈላጊ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልክ ዛሬ በመዝሙር 87 እንደ ተጠቀሰው “ጌታ ሆይ ጸሎቴ በፊትህ ይቅረብ” ብለን ልንጸልይ ይገባል ብለው በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በህመም ወይም በተለያዩ ምክንያቶች በስቃይ ወስጥ እና በመንፈስ ድርቀት የሚሰቃዩ ሰዎችን በምንቀርብበት ወቅት ሁሉ በፍቅር በተሞላ፣ የቀረቤታ ስሜት ባለውና የእንክብካቤ መንፈስ ባለው ጸጥታ መቅረብ አስፈላጊ መሆኑንና እርሱን ሊረዱ የማይችሉ ጠቃሚ ያልሆኑ ንግግሮችን ማሰውገድ እንደ ሚገባም አክለው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ የመንፈስ ድርቀት እንዳጋጠመን ማወቅ የምንችልበትን ፀጋ፣  በእንደዚህ ዓይነት የመንፈስ ድርቀት በምንሰቃይበት ወቅት ሁሉ እንድንጸልይ የሚያደርገን ፀጋ እና በእዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እንዴት መቅረብ እንዳለብን ማወቅ የሚያስችለንን ፀጋ እግዚኣብሔር ይሰጠን ጸንድ ተማጽነው የእለቱ ስብከታቸውን አጠቃለዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.