2016-08-31 17:48:00

በሴቶች ላይ ቅድመ ሁኔታዊ ፍርድ መስጠት ኣይገባም! ኢየሱስ የተገለሉትን ነጻ ያወጣል!


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ተሰብስበው ትምህርታቸውን ለመስማትና ሓዋርያዊ ቡራኬኣቸውን ለመቀበል ይጠባበቁ የነበሩትን ተዘዋውረው ሰላምታ ካቀረቡና ከባረኩ በኋላ የመክፈቻ ጸሎት ኣሳርገው ከማቴዎስ ወንጌል 9,20-20 ‘እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤  በልብዋ። ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና። ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች።’ የሚለው በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎችና በኣረበኛ ከተነበበ በኋላ የሚከተልውን ትምህርት ኣቅርበዋል፣

ውድ ወንድሞችና እህቶች! እንደምን ኣደራችሁ!

ዛሬ ሲነበብ የሰማነው የወንጌል ክፍል በእምነቷና በብርታትዋ ጸጋ የምታገኝ ሴት ፍጻሜ ይተርካል፣ ጌታ ኢየሱስ ደም የሚፈስሳት ሴት እንደፈወሰ የሚገልጥ ክፍል ነው፣ ይህች ሴት ምን ያህል እምነት እንደነበራት ተመልከቱ፣ በልቧ ‘ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደሆነ እድናለሁ’  ለማለት የቀሰቀሳት የእምነትዋ ብዛትና የተስፋዋ ጽናት ነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የመዳን ፍላጐት በሙሴ የተጻፈውን ሕግ ለመሻር ኣስቻላት፣ ይህች ምስኪን ሴት ለብዙ ዓመታት ስትሰቃይ ኖራለች የባሰውኑ ደግሞ ደም ይፈሳት ስለነብር እንደ ርኲስትና ንጽሕት ያልሆነች ይመለክትዋት ስለነበር በሙሴ ሕግ ማንም ሊነካት ወይንም ማንንም ልትነካ  ኣትችልም ነበር (ዘሌ 15.19-30)ለዚህም ከስርዓተ ኣምልኮ ጸሎት ከትዳርና የዕለት ተዕለት ግኑኝነቶች ተነጥላ ነበር፣ ነገር ግን በእምነትዋ ብዛት እንዲያው ማንም ሳያውቅ በሚል ፈሊጥ የኢየሱስን ልብስ በመንካት ብቻ ዳነች፣  ወንጌላዊ ማርቆስ ስለዚህ ታሪክ ሲገልጽ ‘ብዙ ሓኪሞችን ጠይቃ እንደነበር ግን ምንም እንዳልረድዋት` ይናገራል፣ ይህች ሴት ከሕብረተሰቡ የተነጠለችና የተገለለች ነበር፣ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበርችና ስሜትዋን ለመረዳት ይህን ብቻ ማሰብ በቂ ነው ክህብረተሰቡ የተገለለና የተነጠለ መሆን ምንኛ ከባድ መሆኑን እሰቡት፣ ከዚህ ለዓመታት ያሰቃያት ሁኔታ ነጻ ሊያወጣት የሚችል ኢየሱስ መሆኑን በልብዋ ኣመነች፣ ባጭር ቃላት ኢየሱስ ሊያድናት እንደሚችል ታውቃለች በልብዋም ይሰማት ነበር፣

ይህ ፍጻሜ ባለፉት ዘመናት ኣንዲት ሴት እንዴት ይመልከትዋት እንደነብር ይገልጻል፣ እኛም ነጻ ኣይደለንም እንደ ክርስትያን ማህበረሰብ የሴት ልጅ ጉዳይ በሚመለከት ያሉን ቅድመ ሁኔታዊ ፍርዶች ኣስተያየቶች ጥርጣሬዎች ስለ ክብርዋ ያሉን እምነቶች ማሰብ ይቻላል፣ ከዚህ ዓይነት ኣስተሳሰብ ነጻ ሊያደርገን የሚችልና እውነተኛውን የሴት ልጅ ሁኔታ የሚገልጥልን ወንጌል ብቻ ነው፣ ኢየሱስ የዚህን ሴት እምነት ያደንቃል፣ ስሟ ኣናውቅም ነገር ግን በወንጌል ተጠቅሰው ያሉ ጥቂት መስመሮች የእምነት ጉዞዋና ከኢየሱስ ጋር የነበራት ግኑኝነት እውነትን እንዴት እንደሚገልጣና የእያንዳንዱ ኣካል ክብር ታላቅነት እንዴት ኣጉልቶ እንደሚያሳይ እንረዳለን፣ ከኢየሱስ ጋር መገናኘት በተለያዩ ዘመናትና ቦታዎች የሚገኙ የብዙ ወንዶችና ሴቶች ሕይወት እንዴት እንደሚከፈትና የነጻነትና የደህንነት መንገድ እንደሚያገኙ ያስረዳናል፣

በማቴዎስ ወንጌል ሴቱቱ ልብሱን በነካች ግዜ ‘ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና።’ ይላል! መስኪንዋ ሴት በስውር ያደረገችው ገሃድ ስለሆነ እንዲሁም የባህል የእምነትና የሕብረተሰቡ ኣስተሳሰብ ከሁሉ ስለነጠላት በፍርሃት ትቅበዘበዝ ነበር። ኢየሱስ እንዳወቃት ልብ ባለችም ግዜ ምናልባት እኛ እንደምናስበው ‘ኣንቺ ደግሞ እዚህ ምን ኣለሽ! ሂጂ! ከዚህ ራቅ በይ!’ ሳይሆን በምሕረት ዓይንና እርህራሄ በሞላበት ልብ ይመለከታታል፣ ኢየኡስ ምን እንደተፈጸ ያውቃል ልክ ሴቱቱ እንደፈለገችውም የግል ኣዳኝዋ ለመሆንና ከእርስዋ ጋር ግኑኝነት እንዲኖረ ይፈልጋል፣ በዚህም ኢየሱስ ሊቀበላት ብቻ ኣለመወሰኑ ነገር ግን ይህ መብትዋ መሆኑን ለማሳወቅና ልቡና ቀልቡ ከእርሷ ጋር መሆኑን ለመግለጥ ‘ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት።’

በዋነኛው የወንጌሉ ትረካ መዳን የሚለው ቃል ሶስት ግዜ ተደጋግሞ እናገኘዋለን። ‘ልብሱን የነካሁ እንደሆነ እድናለሁ! እምነትሽ ኣዳነሽ እንዲሁም ሴትየዋ ከዛ ግዜ ጀምሮ ዳነች’ በማለት ይተነትነዋል፣ ያ ‘ኣይዞሽ ልቤ’ የሚለው ቃል ለእያዳንዱ ሰው የሚሰጥ የእግዚኣብሔር የምሕረት ተስፋ ነው፣ ወደ ገዛራሳችን መለስ ብለን ያሰብን እንደሆነ ስንት ግዜ ነው የተጣልን የተገለልን እንዲያው በሓጢኣት ምክንያት በሕልናችን ኣይገባኝም የሚል ግላዊ ፍርድ ኣብጅተን ሳለን ጌታ ግን ‘ኣይዞህ ና ልጄ የተገለልክ ኣይደለህም ልጄ ነህ’ ይለናል፣ ይህም የጸጋ ግዜ የምሕረት ግዜ ነው፣ ዛሬም ቢሆን በታናሽ ነገርም ይሁን በታላቅ ነገር ሓጢኣተኞች ለሆነን ለእኛ ሁላችን ጌታ ‘ኣይዞህ ና! የተገለልክ ኣይደለህም ሓጢኣትህን ሁሉ ይቅር ብያለሁ በምሕረት ኣቅፍሃለሁ’ ይለናል፣ የእግዚኣብሔር ምሕረትም ይህ ነው፣ ብርታት ሊኖረን ያስፈልጋል፣ ይህንን ብርታት ኣንግበን እርሱ ጋ በመሄድ ለሓጢኣቶቻችን ይቅሬታ በመጠየቅ ወደፊት መራመድ ኣለብን፣ የዚች ሴት ብርታት ያስፈልገናል፣ መዳን ሲባል ብዙ ነገር ያጠቃልላል፣ በመጀመርያ ሴትየዋ ጤና ታገኛለች በሁለተና ደረጃ ከማሕበረሰባዊና ሃይማኖታዊ መገለል ነጻ ትወጣለች በመጨረሻም በልቧ ኣምቃ ይዛው የነበረችውን የመዳን ተስፋን ታገኛለች፣ ይህም ተደብቃ ያደረገችውን ነገር ግልጥ በማድረግ ከኣሁን ወዲህ ፍርሃት መደበቅ የሚባል ነገር የለም ነጻ ነሽ እንደማለት ይሆናል፣ ወደገዛ ራሳችን መለስ ብለን ያሰላሰልን እንደሆነ ስንት የዘመናችን ለምጻሞች ሓጢኣተኞች እኛንም ጭምር ተደብቀን ምንና ምን እንሰራለን። ምክንያቱም ሃፍረት ይሰማናልና፣ ጌታ ግን ከዚህ ነጻ በማውጣት ‘ተነስ በሁለት እግሮችህ ቁም’ በማለት ጌታ እንደፈጠረን ነጻ ሆነን መቆም እንጂ በሃፍረት ተውጠን መሽኮርመም እንደሌለብን ይገልጥልናል፣ ጌታ ኢየሱስ የሚሰጠን የመዳን ጸጋም ሙሉና ፍጹም ሆኖ ከእግዚኣብሔር ፍቅር ጋር የሚያስተሳስርና ሙሉ መብትና ክብር የሚያለብስ ነው፣

ባጠቃላ ለሴቱቱ ይህንን የመዳን ጸጋ የሰጠው የነካችው ልብስ ሳይሆን የጌታ ኢየሱስ ቃልና ቃሉን በእምነት መቀበል ነው፣ ይህም ቃል መጽናናትን መዳንን ሰጥቶ ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግኑኝነት እንደገና በማሳደስ ከሕዝቡ ጋር ኣንድ እንድንሆን ያደርጋል፣ ለዚሁ የመዳን ጸጋ ኣንድያ ምንጭ ኢየሱስ ሆኖ ለሁሉም የሰው ልጆች የሚሆን ነው፣ ከእኛ የሚፈለገው እምነትና ቃሉን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ብቻ ነው፣ ጌታ ኢየሱስ ዛሬም ቢሆን ምሕረት በተሞላበት መንገድ ቤተ ክርስትያንን ይህንን የደህንነት ስራ ለመስራትና እያንዳንዱ ፍጡር በስጋውና በመንፈሱ እንዲፈውስና የእግዚኣብሔር ልጅ የመሆን መብት ክብር እንዲያገኝ እንድትሰራ መንገዱን ኣጣርቶ ያመልክታል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.