2016-08-16 13:31:00

በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ወቅታዊ “ግጭት” በተመለከተ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የተላለፈ የሰላም ጥሪ


“ በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደረጉ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ ደስ ይበላቸው” ማቴ. 5፡9

በኢትዮጵያ አገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ወቅታዊ “ግጭት” በተመለከተ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ለመላው ምዕመናን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ የተላለፈ የሰላም ጥሪ፡

የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች !

አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ኃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ ቀለምና አካባቢያዊ ድንበር ሳይገድባቸው በፍቅር የሚኖሩባት መሆኗ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ በጥልቅ ባህልና የኃይማኖት እሴቶች በአንድነት የተሳሰሩ ሕዝቦች ያሏት፤ በብዙ አገሮችም የምትደነቅና እንደተምሳሌት የምትቆጠር ናት፡፡ ይሁንና አገራችን በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ተርታ የምትመደብ እንደመሆንዋ መጠን ያለፈውን የድህነት ገጽታዋን ዘግታ በሕዝቦቿ የተባበረ ክንድ ወደ ልማትና ብልፅግና በማሳደግ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ሆናለች፡፡ ይህን መስመርም ይዛ እንድትቀጥል የማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነትና ግዴታ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በሰላማችን ውስጥ አንዳንዴ ያልታሰቡ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በቅርቡ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው አለመግባባት የፈጠረው ሁከት የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ምክንያት ሆኖአል፡፡ ይህም መጥፎ ጠባሳ ፈጥሯል፡፡ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተፈጠረው ችግር በሰው ሕይወት መጥፋት እጅጉን አዝናለች፡፡ ለዚህም ለሟች ቤተሰቦችና በዚህ ምክንያት ላዘኑ ወገኖች ሁሉ መጽናናትን ትመኛለች፡፡ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በሰማይ እንዲቀበልልንና ተጎጂ ወገኖችንም እንግዚአብሔር እንዲያበረታቸው እንጸልያለን፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ይዛ የቆየችውን የሰላም፣ የምሕረት፣ የመከባበርና የአብሮ መኖር እሴቶችን ጠብቃ መኖር ለዘለቄታዊ ልማትና ለሕዝቦቿ ዕድገት እንዲሁም ለቀጣይ ትውልድ መልካሙን አውርሶ የማለፍ አሁን ካለው  ትውልድ የሚጠበቅ ሚና ነው፡፡

በተለያዩ አገሮች ሰላም ሲደፈርስ ሰላም የማስፈን ተልዕኮ የምትወጣ አገር በግጭት ምክንያት ሰላሟ መታወክ የለበትም፡፡ ስለዚህ ከጥላቻ የፀዳ ኅብረተሰብ በመገንባት ለቀጣዩ ትውልድ እንድናወርሳቸው ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

መላው የአገራችን ሕዝቦች በመካከላችን የሚነሳውን ማንኛውንም አለመግባባት በሰከነ መንፈስ በውይይት የመፍታት ባህል እንዲያዳብር በታላቅ በእክብሮት እንጠይቃለን፡፡

በአገራችን ሰላም የመገንባት የሁሉም ዜጋና መንግሥት ኃላፊነት እና ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ፤

< > የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰላም መሣሪያ እንድትሆኑ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡< > ካቶሊካዊያን ምዕመናን፣ ገዳማዊያን በዚህ የፍልሰታ ለማርያም የጾምና የጸሎት ጊዜ ሁላችንም ስለ ሰላምና ፍቅር ልዩ የምህለላ ጸሎት እንድታደርጉ እናሳስባለን፡፡< > ሕዝብ ለማገልገል ኃላፊነት የተጣለባችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፤ የሕዝብን ጥያቄ በየደረጃው አፋጣኝ መልስ በመስጠትና የሰላም ውይይት፣  መድረኮችን በማዘጋጀት የማረጋጋትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጠንክራችሁ እንደትሠሩ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አበክራ ትመክራለች፡፡< > ሽማግሌዎች በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ የተለመደው የማረጋጋት፣ የማወያየት፣ የእርቅና ሰላም ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡< > ወጣት ልጆቻችን በሰላምና እድገት የበለጸገች ኢትዮጵያ እንጂ በሰላም እጦት የታወከች አገር እንድትረከቡ አንሻም፡፡ ስለዚህ ይህ ተጀምሮ ያለ ታላቅ የሰላምና የዕደገት ተስፋ የመረከብና የማስቀጠል ሃገራዊ መብትና ግዴታ እንዳለባችሁ ለማስታወስ እንፈልጋለን፡፡

በመጨረሻ፡- በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ  የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ በልዩ ልዩ የሥራ መስክ የተሰማራችሁ ወገኖች እና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች  የማኅበራዊ እሴቶች ማለትም “እውነት፣ ነጻነት፣ ፍትህና ፍቅርን” (ሁለተኛ ቫቲካን ጉባኤ GS 26, 1966) መርህ በማድረግ ለዓለም፤ የሰላም፣ የመተባበር፣ ግጭትን በውይይት በመፍታት እንደቀድሞው የታወቅን ሕዝብ ሆነን እንድንቀጥል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ቤተክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ስም ትማጠናለች፡፡

ውድ የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች!

ማንኛውንም ለስብዕናችን እና ለዕድገታችን እንቅፋት የሆኑ ድርጊቶችን  በማስወገድ ወደ ውይይት እና መደማመጥ ፍቅር፣ ምሕረት፣ መተሳሰብ፣ መከባበርና ወደ አንድነት ጎዳና በመመለስ፣ ለሀገራችን ሕዝብ ዕድገት የሚጠበቅብንን እናበረክት ዘንድ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡ ይህንንም የሰላም ጥሪያችንን ቸሩ እግዚአብሔር የሁላችንንም ህሊና ወደ ሰላምና አንድነት እንዲመራን ጸሎታችንና ምህለላችን ወደ እርሱ እናቀርባለን፡፡

ሰላም በምድራችን ይስፈን !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ !

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ

  ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

  የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዝደንት

  የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔዎች ኅብረት ሊቀመንበር

  ነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም

  አዲስ አበባ

 








All the contents on this site are copyrighted ©.