2016-08-09 12:45:00

የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ የዕረፍታቸው 38ኛ ዓመት ታስቦ ዋለ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ እ.አ.አ. ነሐሴ 6 ፣ 1978 ዓ. ም. በካስተል ጋንዶልፎ በተባለ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልክ መለወጥ በሚከበርበት ዕለት ማረፋቸው ይታወሳል። በቀድሞ ስማቸው ጆቫኒ ባቲስታ ሞንቲ በመባል የሚታወቁት ቅዱስነታቸው በጣሊያን አገር ብሬሻ ክፍለ ሀገር፣ እ.አ.አ. ሰኔ 21 ቀን 1897 ዓ. ም. የተወለዱ ሲሆን ነሐሴ 21 ቀን 1963 ዓ. ም. የርዕሰ ሊቃነ ጳጳስነትን ማዕረግ ተቀብለዋል።

በወቅቱ ሰፊ ለውጥ በማካሄድ የምትገኘውን መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በጥበብና በማስተዋል የመሩት ቅዱስነታቸው፣ በቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የተከፈተውን ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ እስከ ፍጻሜ አድርሰውል። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን በማድረግ ለአቢያተ ክርስቲያናት መቀራረብም ብዙ ጥረው እንደነበር ይታወሳል። በሕይወት ዘመናቸው ያከናወኑት ታላቅ ገድላቸው ተመስክሮላቸው እ.አ.አ. ከታኅሳስ 20 ቀን 2012 ዓ. ም. ጀምሮ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት 16ኛ እውቅና፣ ልዩ አክብሮትን በመቀበል፣ እ.አ.አ. ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ. ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብጽዕናቸው መታወጁ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዝክረ ዕለቱን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ ኢየሱስ ክርስቶስንና እርሱ የመሰረታትን ቤተ ክርስቲያን በመውደድ ያሳዩትን ምስክርነት አስታውሰው፣ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ለማሳካት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ ቆራጥ ክርስቲያንና ሐዋርያ ነበሩ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “የጊዜአችንን ሁኔታ በማጤንና በጊዜው የሚታዩትን ምልክቶች በመገንዘብ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለሚከሰቱ ለውጦች ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ መርህ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በመቀጠል አንድ ኅብረተሰብ በጭካኔና በዓለማዊነት ሲዋጥም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ቤተ ክርስቲያንን በጥበብ፣ አንዳንድ ጊዜም በብቸኝነት  በመምራት ከእግዚአብሔር የሚሰጣቸው ደስታና እምነት አልጎደለባቸውም ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ለእግዚአብሔር መስጠትን ሳያቋርጡ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን መልዕክት በምድር ላይ ማሰራጨትን ቀጥለው የሁሉ አፍቃሪ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በፍቅር በመምራት አገልግለዋል ብለዋል።     








All the contents on this site are copyrighted ©.