2016-06-09 10:12:00

ቅዱስነታቸው "አንድ ሰው ብዙ መልካም ተግባራትን ልያከናውን ይችላል. .የማይጸልይ ከሆነ ግን ሁሉም ነገር ጨለማ ይሆንበታል"።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ ዘወትር ጥዋት በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴን እንደ ሚያሳርጉ የሚታወቅ ሲሆን በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 30/2008 ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ምዕመናን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ አሳስበው እና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ጣዕም መፍጠር እንደ ሚገባቸው አውስተው፣ ብርሃን በእራሳቸው ሕይወት ውስጥ ብቻ እንዲበራ ከሚገፋፋ ፈተና ተቆጥበው የእምነትን ብርሃን ለጎረቤቶቻቸው እና ለሰው ዘር ሁሉ እንዲዳረስ ማድረግ ይኖርባቸዋል ማለታቸው ተገለጸ።

በእለቱ በተነበበው እና ከማቴዎስ ወንጌል ከምዕራፍ 5: 13-16 በተወሰደው የወንጌል ቃል ላይ ተመርኩዘው ቅዱስ አባታችን እንደ ገለጹት ኢየሱስ ለሐዋሪያቱ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፣ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ማለቱን ገልጸው ክርቲያኖችም ጨው እና ብርሃን መሆን የግድ ይኖርባቸዋል ካሉ ቡኋላ ነገር ግን ይህ በፍጹም እራስን ለማገልገል ብቻ ሊሆን አይገባውም ብለው ጨው የግድ ጣዕም መስጠት ይኖርበታል፣ ብርሃንም የግድ ለሌሎች ማብራት ይኖርበታል በማለት ጨምረው አሳስበዋል።

“ክርስቲያኖች የጨውነት ጣዕማቸውን እንዳያጡ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ብርሃን እንዲሰጡ የሚያደርጋቸውን ጋዝ (ዘይት) እንዳያልቅባቸው ምን ማድረግ አለባቸው? ብለው ጥያቄን በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች ብርሃን እንዲያመነጩ የሚጠቅማቸው ነገር በአጭር ቋንቋ “ጸሎት” ነው ብለዋል።

“አንድ ሰው ብዙ ተግባራትን ለምሳሌም የበጎ አድርጎት ተግባራትን ሊፈጽም ይችላል፣ በካቶሊክ ዩኒቨርስቲ፣ ኮሌጅ፣ ሆስፒታል የመሳሰሉትን ብዙ ታላላቅ ተግባራትን ለቤተ ክርስቲያን ልሰጥ ይችላል፣ ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉም የቤተ ክርስቲያን የክብር ተሸላሚ ሊሆን ይችላል ነገር ግን” አሉ ቅዱስነታቸው “ነገር ግን የማይጸልይ ሰው ከሆነ ሁሉም ነገር ጨለማ እና ድንግዝግዝ ይሆንበታል” ብለዋል።

“ጸሎት” አሉ ቅዱስነታቸው “ጸሎት የክርስቲያን ሕይወት እንዲበራ የሚያደርግ ነገር ነው በማለት  ስበከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ጸሎት “መሠረታዊ” የሆነ ነገር መሆኑን አጉልተው እና አጽኖት ሰጥተው ገልጸው “ለእግዚአብሔር አባት የሚደረግ የአምልኮ ጸሎት፣ ለቅድስት ስላሤ የሚደረግ የወዳሴ ጸሎት፣ የምስጋና ጸሎት እንዲሁም እግዚአብሔርን የምንለምንበት ጸሎት. . .ወዘተርፈ” አስፈላጊ መሆኑን በአጽኖት ገልጸው “ማንኛውም ዓይነት ጸሎት የግድ ከልብ ሊመንጭ እንድሚገባም” አስረግጠው ገልጸዋል።

ክርስቲያኖች ጨው እንዲሆኑ ተጠርተዋል የሚለውን ዐረፈተ ነገር በተመለከተ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ጨው መሆን የሚቻለው ለሌሎች መሰጠት ስንችል ብቻ መሆኑን በማስረዳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አክለውም “በወንጌል መልዕክት ላይ በመመሥረት ለሰዎች ሕይወት ጣዕምን መስጠት” የአንድ ክርስቲያን አመለካከት ሊሆን ይገባዋል ብለዋል።

ጨው ልንጠቀምበት የሚገባ ነገር ነው እንጂ ለእራሳችን የምናስቀምጠው ነገር አይደለም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ጨው እና ብርሃን ለሌሎች የምንጠቀምባቸው ነገሮች ናቸው እንጂ ለእራሳችን ብቻ የሚሆኑ ነገሮች አይደሉም ምክንያቱም “ጨው ለእራሱ ጣዕም ሊሰጥ አይችልም፣ እንደዚሁም ብርሃን ለእራሱ ማብራት እንደ ማይችል ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው” ብለዋል። 

በመጨረሻም ክርስቲያኖች ሁል ጊዜ ደምቀው መብራት እና ለራሳቸው ብቻ ብርሃን እንዲሰጡ ከሚያደርጋቸው ማንኛውም ፈተና መጠበቅ እንዳለባቸው አበክረው ገልጸው “የመስታወት መንፈሳዊነት” ብለው በሰየሙት እና “ለራስ ብቻ ማብራት መጥፎ ነገር” መሆኑን ገልጸው “ለሌሎች የሚያበራ መብራት ሁኑ፣ ለሌሎች ጣዕም የሚሰጥ ጨው ሁኑ” በማለት ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.