2016-06-04 12:46:00

ቅዱስነታቸው ባሳረጉት ስርዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት "ካህናት ሁሉን አቀፍ ሊሆኑ ይገባል"ማለታቸው ተገለጸ።


ቅዱስ ልዩ የምሕረት አመት ኢዩቤሊዩን በማስመልከት ከግንቦት 24-26/2008 ከመላው ዓለም ለተውጣጡ ካህናት እና የአብይ ዘረዐ ክህነት ተማሪዎች የተሳተፉበት እና በሮም ከተማ በሚገኙ አበያተ ክርስቲያናት ውስጥ በቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ መሪነት ለሦስት ቀናት የተካሄደው ሱባሄ በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 26/2008 በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ መፈጸሙ ተገለጸ።

እነደ አውሮፓዊያን የላቲን የስርዓተ ሉጥርጊያ አቆጣጠር በእለቱ የተከበረውን የኢየሱስ ቅዱስ ልብ በዓልን በማስመልከት እና ለሦስት ቀናት ያህል የተካሄደውን ሱባሄ ለመደምደም በቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ መሪነት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ  ስርዓተ ቅዳሴ የተደረገ ሲሆን ያሰሙት ስብከትም ትኩረቱን “ሁለት ልቦች” ያሉዋቸውን የመልካም እረኛ ልብ እና የካህናት ልብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደ ነበረም ለመረዳት ተችሉዋል።

“የመልካም እረኛ ልብ ይቅርታን የምያደርግ ልብ ብቻ ሳይሆን እራሱ ይቅርታ ነው” በማለት ስብከተ ወንጌላቸውን የቀጠሉ ቅዱስነታቸው “የመልካም እረኛ ልብ ለእኛ እና በተለይም ደግሞ በጣም እርቆ ላሉትም የመድረስ ብቃት እንዳለው”  ለካህናቱ ገልጸዋል።

የመልካም እረኛ ልብ የሆነው የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ላይ የሚደርገው አስተንትኖ “ልቤ ወደ የት እያመራ ነው  ያለው?” የሚለውን ጥያቄ ካህናት እራሳቸውን እንዲጠይቁ የሚጋብዝ አስተንትኖ ነው ያሉት ቅድስነታቸው የካህናት አገልግሎት በአብዛኛው “በእቅድ፣ በፕሮጄክት እና በተለያዩ ሥራዎች” የተተበተበ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። ይህ መልካም ነገር ቢሆንም ቅሉ ቅዱስነታቸው ካህናት የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ወደ ሚመራቸው ሁለት አበይት እሴቶች ወደ ሆኑ ወደ አብ እና ወደ እራሳቸው እዲመለሱ ጋብዘዋል። የኢየሱስ ቀናት “ወደ አብ በመጸለይ እና ከሰዎች ጋር በመገኛኘት” የተጠመደ ነው፣ እንደ ኢየሱስ ካህናትም የግድ ልባቸው ወደ እግአብሔር፣ ወደ እህት እና ወንድሞቹ ሊመለስ ይገባዋል” ብለዋል።

ቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በስብከታቸው ወቅት የካህናት ልብ በመልካም እራኛ ፍቅር ይመሰጥ ዘንድ ሦስት ጥቆማዎችን ለካህናት ያቀረቡ ሲሆን እነዚህም መፈልግ፣ ሁሉን አቀፍ እና መደሰት መሆናቸውን ገልጸዋል። የጠፋውን በግ ለመፈለግ እንደ ሄደው መልካም እረኛ ካህንም በሩን ብቻ መክፈት ሳይሆን የጠፉትን ለመፈለግ አበክሮ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል። በተጨማሪም ካህናት ሁሉን አቀፍ ሊሆኑ ይገባል ማንም ሰው ቢሆን ከካህን “ልብ፣ ከካህን ጸሎት ወይም ፈገግታ” ሊገለል አይገባውም ብለዋል። በመጨረሻም በኢየሱስ የሚገኝ ደስታ ያስፈልጋል ካሉ ቡኋላ “መልካም እረኛ ደስታው የእርሱ የግሉ ብቻ ሊሆን ሳይሆን የሚገባው ከሌሎች እና ለሌሎች እና እውነተኛ የደስታ ፍቅር” ያስፈልገዋል ካሉ ቡኋላ “ይህ ነው የካህን ደስታ ሊሆን የሚገባው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን ያጠቃለሉት በእየ እለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ በሚደረግበት ወቅት ካህናት በሚያደርጉት የመለውጫ ጸሎት ላይ “ይህ ለእናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ነው” የሚለውን ጸሎት በማስታወስ ሲሆን “ይህ የሕይወታችን ሕልውና ነው፣ በዚህም ቃል በእየ እለቱ ማዕረገ ክህነት በወሰድንበት እለት የገባነውን ማሀላ እናድሳለን” ካሉ ቡኋላ ይህንን የኢየሱስ ጥሪ “እሺ” ብላችሁ ተቀብላችሁ “ከኢየሱስ ጋር ስለተዋሀዳችሁ” አመሰግናችኋለሁ  በማለት ስብከታቸውን አጠናቀዋል። 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.