2016-05-29 14:23:00

የ5ኛው የፋሲካ ሳምንት እዑድ ስብከት በአባ ሀብቴ አንቱዋን


5ኛ ሣምንት የትንሳኤ ሰንበት ንባባት ፡

ሮሜ 6 ፡ 1፥14

1ጴጥ 4 ፡ 4፥11

ሐዋ  23 ፡15፥21

ዮሐ 21 ፡ 15፥2

 

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!!

 

የምንገኝበት ወቅት ትልቅ የፀጋ ወቅት ነው። ለምን ቢባል? ትልቁና ዋነኛው የእምነታች መሰረትና ምስጢር የሆነውን ትንሳኤን የምናስተነትንበት ወቅት በመሆኑ።  ዛሬ የምንገኘው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያ ስርዓተ  ሉጥርጊያዊ የቀን አቆጣጥር የምንገኘው በ5ኛው  ሣምንት የትንሳኤ እሁድ ነው።  ከመጀምሪያው የትንሳኤ እለት ጀምሮ ለተከታታይ ሃምሳ ቀናት እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያለው ጊዜ የትንሳኤ ወቅት በመባል ይታወቃል ፤ ታዲያ በእዚህ እጅግ ድንቅ በሆነ ወቅት የትንሳኤ ትርጉምና ምስጢር እንድናስተነትን  እንጋበዛለን። ምክንያቱም የትንሳኤ በዓል የእምነታችን መሰረት ስለሆነ ነው። የክርስትና ትልቁ ምስጢር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው። እምነታችን የተመሰረተው በትንሣኤ ነው፥ እምነታችንም የሚደመደመው በትንሣኤ ነው። ክርስትና የትንሣኤ እምነት ነው። ምክንያቱም የምናምነው ሞትንና ክፋትን ሁሉ ድል አድርጎ በተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ  ስለሆነ ነው። ሞትን ባሸነፈው ክርስቶስ ማመን ጥቅሙ ምንድን ነው? ክርስቲያን መሆን ተስፋው ምንድን ነው? የክርስትና እምነት መጨረሻው የት ነው? የሰው ልጅ መጨረሻው ምን ይሆናል? ለእነዚህ ጥያቄዎች የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መልስ ይሆነናል። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሰው ልጅ በሠራው ኅጥያት ምክንያት ያጣውን ክብር መልሶ ያገኛል፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ሰውና እግዚአብሔር ታርቀዋል ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሰው ልጅ ትክክለኛ ትርጉምና ክብሩን ይጎናፀፋል ፤ ለእዚህ ነው ትንሣኤ የክርስትና እምነት መነሻና መድረሻ ነው የምንለው። ክርስቶስ በትንሣኤው አምላካዊ ክብሩን ተጎናፅፉዋል ፤ እንደዚሁም በርሱ አምነው ለሚሞቱም ይህን ክብር እንደ ምንጎናፀፉ እናምናለ።

 

ጌታችን በትንሣኤው፥ ሞትን በሕይወት፥ በደለን በይቅርታ፥ ጥላቻን በፍቅር  ሥቃይን በዕትግሥት  አሸነፈ። ፍቅርና ምሕረት የክርስቶስ የጦር መሣሪያዎች ናቸው፥ ፍቅርና ምሕረት የክርስቶስ ማሸነፊያ መሣሪያዎች ናቸው።ፍቅርና ምሕረት ድልን ያጎናፅፋሉ።

የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብርና ስናስተነትን ታሪክ እያሰብን አይደለም የምናስተነትነው፥ ወይም የክርስቶስ ትንሣኤ ነበረ  እያልን በትዝታ የምናስተነትነው አይደለም። ለምን ቢባል? ክርስቶስ ሁሌም አዲስና ኅያው ነው። ክርስቶስ ዛሬም ያፍቅራል፥ ክርስቶስ ዛሬም ይምራል፥ ክርስቶስ ዛሬም ያሸንፋል፥ ክርስቶስ ዛሬም ያድናል፥ ክርስቶስ ዛሬም ከኛ ጋር ነው። የክርስቶስ የትንሣኤ ብርሃን ዛሬም ያበራል፤ ዛሬም መቃብሩ ባዶ ነው፤ ስለእዚህ የምናስተነትነው፥ የምናምነው ታሪክ ሳይሆን እውነት ነው.።  ለእዚህ ነው እምነታችን ክርስትና በታሪክ የተመሰረተ ሳይሆን ፥ እውነት ፥ ሕይወ ት ፥  ብርሃንና አሸናፊው እየሱስ ክርስቶስ ነው።

የምንሰማው ወይም የምናነበው መፅሐፍ ቅዱስ የእግዚእብሔርን ታሪክ አይደለም የሚተርክልን። ወይም ብዙ ጊዜ  ብዙ  ሰዎች ፥ መፅሐፍ ቅዱስ ከዘመናት በፊት እግዚአብሔር የሠራውን ስራ የሚተርክልን ፤ ወይም ደግሞ የእግዚአብሔር ታሪክ እንዳይረሳ ተብሎ ተፅፎ የተቀመጠ የእግዚአብሔር ታሪክ እንደ አንድ የታሪክ መዝገብ አድርገንም እናስብ ይሆናል። ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም ፤ የምንሰማው ወይም የምናነበው  መፅሐፍ ቅዱስ ኅያውና ሁሌም አዲስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ለምን ? ዛሬም እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ፥ ዛሬም እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነውና ፥ ዛሬም እግዚአብሔር ይሰራል ፥ ያድናል ፥ ያፈቅራል  ፥ ይምራል። በእግዚእብሔር ዘንድ ነበር ወይም አድርጎ ነበር ብለን የምንለው የለንም።

 በክርስቶስ የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች! ዛሬ በአምስተኛዉ የፋሲካ ሳምንት ፥ ክርስቶስ እንድናስተነትንበት፥ እንድንፀልይበት እንዲሁም ሕይወታችንን እንድንመረምርበት የሚጋብዘን ቃል ይናገረናል። ቤተክርስቲያን ሄደን ፥ ፀልየን ፥ አመስግነን፥ እልል ብለን ዘምረን ፥ ቅዳሴ አስቀድሰንና ቆርበን ቢቻ አንቆምም። ያ! የሰማነው የክርስቶስ ቃል ፥ ያ ! የበላነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ደም ፤  በየ ቀኑ በምናደርገው የሕይወት ውጣ ውረድ፥ በምንገባበትና በምንወጣበት ሁሉ ፥ በምንስራበትና በምናርፍበት ሁሉ ፤ እንድናስተነትነው ነው ፤ የሕይወታችን መመሪያ እንዲሆን ነው ፤ ያስተሳሰባችን ፥ ያነጋገራችን ፥ የኑሮአችን    መምሪያና እንዲሆን ነው ፤ እምነታችን ታሪክ አይደለም፥ እምነታችን ሃሳብ ወይም ፍልስፍና አይደለም፥ እምነታችን ሕይወት ነው ፤ እምነታችን ክርስትና ተወርቶ የሚነገር ሣይሆን የሚኖር ነው። ክርስትና ኖረህ ወይም ሆነህ የምታሣየው እንጂ አውርትህ የምታሣየ አይደለም፥ ነግር ግን አብዛኛው የዛሬ ክርስቲያኖች ክርስትናችንን አውርተን ለመተረክ ይቀለናል። ብዙ ሰዎች የክርስትና እምነት በህግና በስርዓት የተሞላ ፥ አድርግና አታድርግ ፥ ንካ ወይም አትንካ በሚሉ ወጎች የታጠረ ፥ አድርግና አታድርግ በሚል ሕግ የተሞላ ፥ እግዚአብሔርን  እንደ እንድ  ግሕ አውጪ ዳኛ ፥ መላዕክት ደግሞ እንደ ጨካኝ ሕግ አስከባሪ ብለው የሚያምኑና የሚያወሩ እጅግ ብዙ ናቸው ፤ ወይም ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስን እንደ የሕግ መፅሐፍ አድርገው ያስባሉ።  ነገር ግን ክርስቶስ ለሕይወት የሚጠራን እና የሚጋብዘን አፍቃሪያችን ፥ ወድማችንና ጋደኛችን እንጂ ህግ ሰጪና ቀጪ አይደለም። መፅሐፍ ቅዱስም የሕይወት መንገድ ነው።

ለእዚህ ነው ዛሬ በቃሉ ከኛ ኃጥያት የእግዚአብሔር ምሕረት ይበልጣል እያለ በማፅናናት፥ በኃጥያታችን አዝነን ተስፋ ቆርጠን ከራሱ እንዳንርቅ የሚጣራን። የጠላታችን ዋና ስራ ኃጥያት እንድንሰራ ፤ ከዛም በሰራነው ኃጥያት አዝነን ፤ ተስፋ እንድንቆርጥ ፤  ከዛም እንዳናምን ከዛም እንዳናፈቅር ፥ ምክኒያቱም ተስፋ የቆረጠ ሰው ማመን አይችልም፥ የማያምን ሰው ማፍቅር አይችምል ፤ የማያፈቅር ሰው ደግሞ ይፈራል። ፈሪ ድግሞ እግዚአብሔርን እንደ ጨካኝና ክፉ  ንጉሥ እንደሆነ ያምናል።   ለዚህ ነው ውዱ አፍቃሪ  ጌታችን ኢየሱስ መጀመሪያ ለምሕረት የሚጋብዘን ፥ ለዚህ ነው መጀመሪያ ምሮን እፅናንቶን ተስፋ ሰጥቶን  አበርትቶን፥ ዳግመኛ ኃጥያት አትስራ፥ ከኃጥያት ቀንበር ተላቀቅ፥ አንተ እኮ እንቺ እኮ በእኔ ደም የተገዛህ ፥ የተገዝሽ፥ በእኔ የሚያምን ከሃጥያ ለመንፃት እንዳለበት ፥ በታላቁ የክርስትና መምህር በሆነ በቅዱስ ጳውሎስ አማካይነት እነሆ ዛሬም ጌታችን ይናገረናል።

ክርስቲያን በየቀኑ የሚሰማው የክርስቶስ ቃል፥ በየቀኑ ወይም በየ ሰንብቱ በሚካፈለው ቅዳሴ፥ በሚበላው የክርስቶስ ቅዱስ  ሥጋና  ቅዱስ ደም ፤  የእራሱ ሕይወት በፀጋ ተሞልቶ ሌላውን በፀጋ  እንዲሞላ፥ የእራሱ ሕይወት  በፍቅር ታንፆ ሌላውን በፍቅር እንዲያንፅ ፥ እራሱ በእምነት ተሞልቶ ሌላዉን በእምነት እንዲሞላ፥ እራሱ በተስፋ በርትቶ ለሌላው በተስፋ እንዲያበረታ ክርስቶስ በቃሉ ይጋብዘናል።

ክርስቲያን ኃጥያት ሳይሆን ክርስቶስ እንዲገዛው፥ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር እንዲገዛው፥ ቂምን ሳይሆን ምሕረት እንዲገዛው፥ ሞትን ሳይሆን ሕይወት እንዲገዛው ፥ የክርስቶስ ቃል ይጠራዋል። የክርስቶስ ቃል ፥ የክርስቶስ ሕይወት፥ የክርስቶስ ሥራ፤ የሰላም ሁሉ ምንጭ ነው፥ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፥ ክርስቲያንም በክርስቶስ የሚያምን፥ በተቀበለው የጥምቀት ፀጋ  አማካይንት የክርስቶስ ወንድም ፥ የእግዚእብሔር ልጅ ወይም ሌላኛው ክርስቶስ ሆነዋል፤ ስለዚህ ክርስቲያን ሁለተኛ ክርስቶስ ሆኖዋል  እርሱም የሰላምና የፅድቅ መሳሪያ እንዲሆን ዛሬ የክርስቶስ ቃል ይጋብዘዋል።

 

ሌላው በዛሬው የጌታ ቀን ፥ በሰንበተ ክርስቲያ ፥ እንደ ሁሌዉም ፥ ዛሬም ጌታችን ክርስቶስ ለምህረትና ለፍቅር ይጋብዛናል። የክርስቶስ የማሸነፊያ መሳሪያዎች ምሕረትና ፍቅር ናችው። የክርስቶስ ሕጎች ምሕረትና ፍቅር ናችው። ክርስቶስ በምሕረቱና በፍቅሩ ክፋትን ሁሉ፥ ዓለምን ሁሉ እሸንፋዋል። ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሕረትና ፍቅርን እንደ ሕግ ይሰጣል። ምሕረትና ፍቅር ሁለቱ የማይለያዩ የክርስቶስ ኃይሎች ናችው። ስለ ሚያፈቅረን  ይምረናል ፤ ስለ ሚምረን ያፈቅረናል። ማፍቀር ይሚችል ቢቻ ነው መማር የሚችለው፤ መማር የሚችል ቢቻ ነው ማፍቀር የሚችለው። ማፍቀርና መማር ማሸነፊያ የክርስቲያን የጦር መሳሪያዎች። ለዚህ ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህን ዓመት የምሕረት ዓመት ዓውጃ ፤ በዚህ ዓመት የክርስቶስን ምሕረትና ፍቅር በስፋትና በጥልቀት እንድናስተነትን እና ይህን የክርስቶስን የአስተማሪኣችን፥ የወንድማችን፥ የአዳኛችንን ፀባይና ባህሪ እንድንላበስ የምንጋበዘው። “የሰማይ አባታችሁ መሓሪ እንደ ሆን እናንተም መሓሪዎች ሁኑ”

የክርስቶስ ቤተሰቦች! ዛሬ የሚነበብልን  ቅዱስ ወንጌል የኅያው እግዚእብሔር ኅያው ቃል ፤ በየዋሁ ፥ እጅግ ችኩሉ ፥ ጌታውንና  መምሕሩን ሶስት ጊዜ አላውቀውም ብሎ  በካድው ጴጥሮስና በክርስቶስ መካከል የተደረገውን የሕይወት ውይይት ይተርክርልናል።  በወንጌል እንደ ምናገኘው ጴጥሮስ ፤ እጅግ ችኩል ነው ፤ በሁሉም ቦታ ላይ እሱ ቀድሞ መታይት ሚፈልግ ፤ ሁል ጊዜ ቀድሞ መናግር የሚወድ  ፤ እጅግም የዋህ ነው ሕይወቱን እንክዋን አሳልፎ እንደ ሚስጥ ይምላላ ፤ እጅግም ፈሪና ድንጉጥ ነው  ፤ ለሕይወቱ በመፍራት  አንተ የኅያው እግዚአቤሔር ልጅ መሲህ ነህ ብሎ የመሰከረለትን ሶስት ጊዜ አላውቀውም  ብሎ  ካደው።  ያ! የሕይወት ጌታ፥ ያ ! እጅግ መሃሪው ፥ ያ ! እጅግ አፍቃሪው ፥ ያ! እጅግ አዛኙ ፤ ይህን ከሃዲ ለአዲስ ሕይወት ይጋብዘዋል  ፤ በፍቅሩ ኅጥያቱን ያጠፋል፥ በምሕረቱ ክፋቱን ያስረሳዋል። በፀጋው ያበረታዋል ፤ ዳግም እንዳይወድቅ ፤ ዳግም እንዳይከዳ ፤  ክርስቶስ ጴጥሮስን በኅጥያቱ አልከሰሰውም፥ በድክመቱ አልተቆጣዉም ፥ ክኅደቱን እያስታወ አልተበቀለውም ፤  ምክኒያቱም ከጴጥሮስ ክፋት የክርስቶስ ደግነት ይበልጣል  ፤ ምክኒያቱም ከጴጥሮስ ኅጥያት የክርስቶስ ምሕረትና ፍቅር ይበልጣልና። ክርስቶስ አለማፍቅር አይችልም፥ ክርስቶስ አለመውደድ አይችልም፥ ክርስቶስ አለመማር አይችልም ፤  ምክኒያቱም ክርስቶስ ፍቅር ነውና ፥ ፍቅር ደግሞ በደልን አይቆጥርም። ፍቅር በማፍቀር ቢቻ ነው የሚደሰተው፥ ፍቅር በምሕረት ቢቻ ነው እረፍት የሚያገኘው። ስለዚህ ክርስቶስ ሁል ጊዜ የፍቅርና የምሕረት ጋባዥ ነው። ጵጥሮስ!  ትወደኛለህን? ጵጥሮስ!  ትወደኛልህን? ጴጥሮስ! ትወደኛለህን? ሶስት ጊዜ አስረግጦ በርግጠኝነት ክዶ የነበረውን፤ ሶስት ጊዜ አስረግጦ በዕግጠኝነትና በፍፁም  እንዲያፈቅረው ጋበዛው።  በመፅሐፍ ቅዱስ  ቁዋንቁዋ ሶስት ቁጥር የፍጹምነት ምሳሌ ነው። የእውነት ካደው ፤ የእውነት አፍቀረው።

የክርስቶስ ቤተሰቦች!  ዛሬ ጴጥሮስ የለም ፤ የጴጥሮስን ቦታ ለኛ ተሰጠን ፤ በሰማነው ታሪክ እራሳችንን እናስገባ ፤ ዛሬ ክርስቶስ ከጴጥሮስ ጋር ሳይሆን ከእኔና ከናንተ ጋር ማውራት ይፈልጋ ፤ ዛሬ ከጴጥሮስ ጋር ሳይሆን ከያንዳንዳችን ጋር መወያየት ይፈልጋ ፤  እያንዳንዳችንን በስማችን እየጠራ ፤ ልጄ ሆይ!  ትወደኛለህን? እገሌ  ሆይ!  ትወደኛለህን? እገሊት ሆይ!  ትወጂኛለሽን? ክርስቶስን ቀርበን ለማዋየት አንፍራ ፤ ከክርቶስ ጋር ለማውራት አንፈር ፤ ሊወቅሰን ፥ ሊፈፈርድብን ወይም ሊቀጣን አይደለም የሚጠራን ።  አዎ እርግጥ ነው እንደ ጴጥሮስ እያንዳንዳችን እጅግ ብዙ ጊዜ ፤ በርግጠኝነት  ሶስት ጊዜና ከዛም በላይ ክደነው ይሆናል ፤ እጅግ ብዙ ጊዜ ችኩሎች ሆነን ክርስቶስንና የክርስቶስን ወንድሞች አስቀይመናል ፥ እጅግ ዙ ጊዜ ለሕይወታችን ፥ ለጤናችን ፥ ለስራችን ፥ ለቤተሰባችን ፥ በብዙ በብዙ ምክኒያት ፈርተን ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታ ፥ አፍቃሪያችንን ፥ ወዳጃችንን ከድተነዋል ፤ የእውነት በእውነት አላቀውም ብለን ይሆናል ፥ በጭራሽ ከዕርሱ ጋር አልነበርኩም ፥ በእውነት አላየሁትም ብለን ምለን ተገዘተን ይሆን ይሆና ፤ የሕይወት ማእበል ሲነሳ ፈርተን እርሱን ማየት ትተን ማዕበሉን አይተን ይሆናል ፤  ቢኖንም ከኛ ክፋት የክርስቶስ ፍቅር ስለሚበልጥ ፤ ከኛ ኃጥያት የክርስቶስ ምሕረት ስለሚበልጥ ፤ ሁሉንም እረስቶ ክርስቶስ ለምሕረትና ለፍቅር ይጠራናል ፤ ልቡን ከፍቶ እጁን ዘርግቶ ፤ ፍቅር በደልን እንደ በደል ስለማይቆጥር ፤ ልጄ ሆይ! ትወደኛለህን? እገሌ ሆይ! ትወደኛለህን? እገሊት ሆይ! ትወጅኛለሽን?  እንግዲ ይህ የፍቅር ጥያቄ ቀርቦልና ፤  መልሳችን ምንድን ነው ለአፍቃሪኣችን?  ፍቅር ሁል ጊዜ እረሃብና ጥማቱ ፍቅር ነው  ፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፤ ክርስቶስ ፍቅር ነው ፤  ፍቅርን ተርቦአል ፤ እንግዲ የክርስቶስ ቤተቦች!  ቤተክርስቲያን የምንሄደው ፤ ለሥርዓትና ለሕግ ሳይሆን ይህን የክርስቶስ የፍቅር ጥሪን ምላሽ ለመስጠት ነው። ጴጥሮስ ለክርስቶስ የፍቅር ጥያቄ መልስ ከሰጠ በኁዋላ ፤ የታዘዘው ነገር ቢኖር ያ የተቀበለውን ፍቅር ለሌላ እንዲያካፍል ነው። ግልግሎቼን መግ ብ. . .  ጥቦቶቼን ጠብቅ . . .  በጎቼን አሰማራ . . . እንግዲያዉስ ለቀረብልን የፍቅር ጥሪ እንመልስ እንስጥ ፤ መጀመሪያ በመፈቀራችን እንደሰት፤ የተፈጠርነው ለፍቅር ነው ፤ የዳነው በፍቅር ነው ፤ የምንኖረው በፍቅር ነው ፤ ከእግዚአብሔርና ከወንድሞቻችን ጋር በክርስቶስ ፍቅር እንዋሃድ ፤ እግዚእብሔርን ስለ ዕራሱ እናፍቅረው ፤ እራሳችንና ሌሎችን ደግሞ ስለ እግዚአብሔር እናፍቅር።  አዎ አፈቅርሃለሁ ብለን መልስ መስጠትን አንፍራ ፤ በክርስቶ ፍቅር ሌሎችን እናፍቅር ፤በክርስቶስ ፍቅር  የክርስቶስን በጎች እናፍቅር፥ በክርስቶስ የክርስቶስ ጥቦቶች እንጠብቅ  ፤ በክርስቶስ ፍቅር የክርስቶስ በጎችን እናሰማራ።

 

ይህን ትልቅ የክርስቶስ ፍቅር ተቀብላ ክርስቶስን አፍቅራ የሰውን ሁሉ ልጅ ማፍቀር የቻለች እመቤታችን ቅስት ድንግል ማርያም ፤ የክርስቶስ የልጅዋ የምሕረትና የፍቅር አስተማሪ ዛሬም ለእኛም መሓሪነትንና አፍቃሪነትን ታስተምረን።

 

አሜን አሜን አሜ

በአባት ሀብቴ አንቱዋን

ኢትዮጵያን ኮሌጅ

ቫቲካን

 

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.