2016-05-16 11:42:00

“ጌታ በእርግጥም ተነስቱዋል ለስምዖንም ታይቱኋል” ሉቃ 24:34


ጌታ በእርግጥም ተነስቱዋል ለስምዖንም ታይቱኋል” ሉቃ 24:34

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ፣ በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ።

በስርዓተ አምልኮኋችን አቆጣጠር እና ደንብ መሰረት በትንሳኤ ወቅት እንገኛለን። በእዚህ ወቅት የምናነባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ይህንኑ  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ እርግጠኛነትን የሚገልጹ ናቸው፣ ምክንያቱ የወቅቱ አብይ ዜና የጌታ ትንሳኤ ነውና።

“ጌታ በእርግጥም ተነስቱኋል ለምዖንም ታይቱኋል” ይላል የዛሬ የወንጌል ቃል ማጠቃለያ። የኤማሆስ መንገደኞች ታሪክ በክርስቶስ ሞት ምክንያት በደቀ መዛሙርቱ ዘንድ የነበረው ተስፋ መቁረጥ፣ እና በትንሳኤው ምክንያት እንደ ገና ተስፋቸው ለምልሞ የትንሳኤው ምስክሮች ለመሆን እንደ በቁ ያስረዳናል።

ከትንሳኤ እሁድ እስከ ጴራቂሊጦስ ያለውን ወቅት በእምነታ ዓይን ስንመለከተው እንደ አንድ ቀን ነው። የትንሳኤን ምስጢር የምናውጅበት እና የምናከብርበት ወቅት ወይም ቀን ነው። ትንሳኤ የእምነታችን በዓል ነው፣ ክርስትናን ክርስትና ያሰኘው ነገር ቢኖር የክርስቶስ ሞት እና ከሙታን መነሳቱ ወይም ትንሳኤው ነው። ክርስቶስ ከሙታን ባይነሳ ኖሮ እምነታችን እንደ ማንኛውም ርዕዮተ ዓልም ሞቅ ደመቅ ብሎ ይጠፋ ነብር።

ከዛሬ ወንጌል እንደ ምንረዳው የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ ነገር አብቅቱኋል ብለው ወደ ቀድሞ ኑሮኋቸው እና ሥራቸው መመለስ ጀምረው እንደ ነበረ ነው። ነግር ግን ክርስቶስ ከሞት በመንሳቱ ሁሉም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን መሰረት እና የትንሳኤው ምስክሮች ሆኑ። በሌላ አነጋገር የክርስትና ታሪክ ከኋላ ወደ ፊት ተጻፈ ማለት ይቻላል። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው እውነት በመንሳት ነው ሙሉ ዝርዝሩ ተጽፎ የምናየው ወይም ከሞት በመንሳቱ ነው ታሪኩ በጣም አስፈላጊ የሆነው።

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ያስታውሱት የነበረው በዓል የጌታን ቀን ማለትም የትንሳኤውን እለት ብቻ ነበር ቀስ በቀስ ሌሎች በዓልትም መከበር ጀመሩ። እኛም እያአንድ አንዳችን የተጠምቅነው በጌታችን በኢየሱ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ ነው። ጌታ የሰውን ልጆች ለማዳን መሞቱን እና ከሙታን መነሳቱን አምናለው። እኔም ከክርስቶስ ጋር ለኋጥያት ሞቻለው፣ በክርስቶስ በተገኘው አዲስ ሕይወት ለመኖር ከክርስቶስ ጋር ከሞት ተነስቻለሁ። ዘላቂ ተስፋዬም ከሞት የተነሳው ክርስቶስን ክብር ተሳታፊ እሆናለሁ የሚል ነው ስለእዚህም ትንሳኤ የእምነታችን በዓል ነው።

ትንሳኤ የእግዚኣብሔር ምሕረት ወይም መኅሪነት የሚዘከርበት በዓል ነው። ስለትንሴው ስንናገር ለምን እና እንዴት ሞተ? የሚለውን ዋናውን ጥያቄ ያስታውሰናል። እግዚአብሔር አባታ በታላቅ ፍቅር እና ርህራኄ ሰውን ለማዳን አንድ ልጁን መስዋዕት እንዲሆን ሰለ ላከው ነው። በኋጥያታችን ምክንያት መሞት የነበረብን ነበርን። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ፋንታ ሞታችንን ሞቶልን በትንሳኤውም ሕይወትን ሰጠን በእዚህም የእግዚኣብሔር አብ መኅሪነት እና ታላቅነት ተገለጸ ስለእዚህም የትንሳኤ በዓል የእግዚኣብሔር አብ ምህረት የሚዘከርበት በዓል ነው።

በእዚህ ዓመት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የታወጀው ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመት ኢዩቤሊዩ ይህንኑ የእግዚአብሔር ምሕረት የሚያስታወሰን ነው። ትንሳኤ ተስፋ የማድረግ ወይም የተስፋ በዓል ነው። ሁኔታዎች ተስፋን በምያስቆርጡን ጊዜ ሁሉ እና ሁሉም ነገር አብቅቱኋል በምንልበት ወቅት እና ሰዓት እንኳ እግዚአብሔር ሕያው እና ሁሌም ቢሆን የሚሠራ መሆኑን የምያስታውሰን በዓል ነው።  የኤማሆስ መንገደኞች ንግግር እና ሁኔታ ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። “እኛ እስራኤልን ነፃ የምያወጣ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፣ ነገር ግን ይህ ሁሉ ከሆነ እነሆ ሦስት ቀን አልፎታል” (ሉቃ. 24,21)። ከሞት መነሳቱን ሲረዱ ግን የጠወለገው ተስፋቸው ለመለመ። ለእኛም ዛሬ የትንሳኤ ምስጢር በእየለቱ ኑሮዋችን እና ሕይወታችን ተስፋችንን የሚያለመልም እውነታ ነው። ይህም የእምነታችን መሰረት ነው።

የኤማሆስ መንገደኞችም ሆኑ ሌሎች ከሞት የተነሳውን ጌታ ለመጀመሪያ ጊዜ የምያዩት አያውቁትም ነገር ግን በመነሳቱ አምነው ሲያውቁት ግን ይሰወራል ምክንያቱም ከሞት የተነሳውን ጌታ የምናውቀው በእምነት ዓይን ብቻ ስለሆነ።

ዛሬ የምንኖርበት ዓለም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች፣ ጥያቄን የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ እንኖራለን፣ የኤማሆስ ሰዎች ታሪክ ታሪካችን ነው።

ለምሳሌም በምዕራቡ ዓለም የምናየው የእግዚአብሔር ህልውናን ችላ ያለ ሐይማኖትን እና ግብረ ገብነትን ችላ የሚል ባሕል፣ ሰው እራሱ የሕይወቱ ማዕከል እና ባሌበት እንደ ሆነ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ዝንባሌ ይታይበታል። ቀድመው የክርስትና መዕከል በነበሩ ሀገራት ሳይቀር የክርስቶስን መስቀል በይፋ በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎች መሰቀል አለበት ወይም የለበትም ብለው ይከራከራሉ። በአጭሩ እግዚአብሔር እንደ ሞተ ያስባሉ ታዲያ እንዴት ነው ትንሳኤውን በእውነት ማክበር የሚችሉት?

በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በእመነታቸው ምክንያት እየተሰደዱ፣ እየሞቱ በአጠቃላይ ብዙ መከራ እየደረሰባቸው ይገኛል። እንደት ነው እነዚህ ወገኖች የትንሳኤን ምስጢር ተስፋ ሊያከብሩ የሚችሉት? ተስፋቸውስ ማን ነው? እነርሱ የዘመኑ የኤማሆስ መንገደኞች ናቸው።

ብዙ ወገኖች በስደት መንገድ ላይ ይገኛሉ። በየጊዜው የምንሰማው ዜና በበረሃ እና በባሕር ጉዞ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ነው። ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በአሸባሪዎች ይገደላሉ። በሚያዩት እና በሚሰሙት ነገር ተስፋ ቆርጠው ወይም የተሻለ ነገር ፍለጋ ሲሰደዱ የከፋ ነገር እያጋጠማቸው ይገኛል። እንዴት ነው እነእዚህ ሰዎች የትንሳኤን ምስጢር እና ተስፋ የምያከብሩት? እኛስ ይህንን ሁሉ ነገር እያየን እየሰማን የትንሳኤውን ተስፋ የምናምነው እና የምንኖረው እንዴት ነው? በመንገዳቸው ስለ ምን ይሁን የሚያወሩት? ስለተስፋ መቁረጣቸው ወይስ ስለብቸኝነታቸው? እነርሱም የኤማሆስ መንገደኞች ናቸው።

ትንሳኤን መኖር እና ማክበር ማለት ተስፋ በምያስቆርጡ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆንም እንኳን እግዚኣብሔር ባለ ማቋረጥ ከእኛ ጋር እንደ ሆነ ማሰብ ማለት ነው። ከኤማሆስ መንገደኞች የነበረው ጌታ ዛሬም በእያንዳንዱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን በመኋከላችን መሆኑን እና ብቻችንን አለምሆናችንን ያስታውሰናል።

ክርስቲያንች ስለሆንን ብቻ ችግሮች አያጋጥሙንም ማለት ሳይሆን በችግሮቻችን ሁሉ እግዚኣብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን እና ችግሮቻችንም ጊዜያዊ እንደ ሆኑ፣ ጨለማው አልፎ ብርሃን እንደ ምናይ መሆኑን የምያረጋግጥልን ነው።

በመጨረሻም በእዚህ በትንሳኤ ወቅት እና በያዝነው ልዩ የምሕረት ኢዩቤሊዩ ዓመት በምሕረቱ ተደግፈን እና በደግነቱ ተማምነን ወደ እግዚኣብሔር በሙሉ ልብ እንድንመለስ ያስፈልጋል።

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ወገኖች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እግዚአብሔር መሐሪ እና ደግ እንደሆነ ሁሉ እኛም በአምሳሉ የተፈጠርን ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ድግነትን እና ምሕረትን እንድናደርግ ያስፈልጋል።

የምሕረት እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የእግዚአብሔር ተስፋ ቃል ያመነችው እኛም በሙሉ ተስፋችን በእግዚአብሔር እንድናድግ፣ ምሕረትም እንድናገኝ፣ በፀሎትዋ፣ በአማላጅነቱዋ ትርዳን!! አሜን።

በአባ ገብረመስቀል ሽኩር የተዘጋጄ

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.