2016-05-14 09:54:00

የሀዋሳ ሀገር ስብከት ጳጳስ የነበሩ አቡነ ዮሐንስ ሚልዮራቲ ከእዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።


የሀዋሳ ሀገር ስብከት ጳጳስ የነበሩ አቡነ ዮሐንስ ሚልዮራቲ በግንቦት 4.2008 በ74 ዓመታቸው ከእዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። አቡነ ዮሐንስ ሚልዮራቲ በሰሜን ጣሊያን በሎምባርዲያ ክፍለ ሀገር በብሬሻ ጠቅላይ ግዛት ፓቮኔ ዴ ሜላ በሚባል ስፍራ እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በኔሐሴ 24, 1942 ተወለዱ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት ስፍራ ካጠናቀቁ ቡኋላ በጥቅምት ወር 1953 በኮምቦኒ ማሕበር ዘረዐ ክህነት በመግባት በእዚያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀቁ።  እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1963-1965 የተሞክሮ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ ሀገር በኮንቦኒ ማሕበር የተከታተሉ ሲሆን በመቀጠልም በሴሜን ጣሊያን በምትገኜው በክሬማ የአራት ዓመታት የነገረ መለኮት ትምህርታቸውን ተከታትለው እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በየካቲት 12, 1969 በጣሊያን በምትገኘው በብሬሻ ጠቅላይ ግዛት ማዕረገ ክህነትን ከተቀበሉ ቡኋላ በተመሳሳይ ዓመት በሕዳር ወር 1969 ወደ ኢትዮጲያ ተልከው በመሄድ የሚስዮናዊ ስራቸውን ጀመሩ።

አቡነ ዩሐንስ ሚልዮራቲ ለ24 ዓመታት ያህል በኢትዮጲያ ያገለገሉ ሲሆን በመጀመሪያ የአማሪኛን በመቀጠልም የሲዳሜኛን ቋንቋ በመማር የተለያዩ የሚስዮናዊ አገልግሎቶችን ያበረከቱ ሲሆን እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር 1973 የመጀሪያውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጌድዮ ዞን በመክፈት የአከባቢው ነዋሪ መሰረታዊ ትምህርትን እንድያገኝ ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክተዋል። በመቀጠልም እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከ1975-1979 የትምህርተ ክርስቶስ መስጫ ማዕከል አላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከ1989-1993 የሀዋሳ ሀገረ ስብከት ንዑስ ዘርዐ ክህነት አለቃ በመሆን አገልግለው እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከ1979-1984 የኮንቦኒ ማሕበር የተሞክሮ ቤት አለቃ በመሆን አገልግለው እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከ1986-1993 የሀዋሳ ሀገር ስብከት ካቴድራል በቆሞስነት አገልግለዋል።

እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በጥቅምት ወር 1993 በጣሊያን እና በእንግሊዝ ሀገር ለተወሰነ ጊዜ እረፍት ለማድረግ ከኢትዮጲያ የወጡ ሲሆን በእዚያ ቆይታቸው የሐዋሪያዊ ሥራን የተመለከተ የነገረ መለኮት ትምህርት ተከታትለው በተጨማሪም በስርዓተ አምልኮ የማጠናከሪያ ትምህርት መውሰዳቸውም ከሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሉዋል። 

እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር 2001 ወደ ኢትዮጲያ በመመለስም የሀዋሳ ሀግረ ስብከት የዐብይ ዘረዐ ክህነት ሀላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከአላፊነት ሥራቸው ጋር በማጣመር በካፑቺን የፍልስፍና እና የነገረ መለኮት ተቁዋም በመምህርነት ማገልገላቸውንም ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሉዋል።

እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በሚያዚያ 21, 2009 በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በበኔዴክቶስ 16ኛ ማዕረገ ጵጵስናን ተቀብለው የሀዋሳን ሀገረ ስብከት ማስተዳደር ጀመሩ።

አቡነ ዩሐንስ ሚልዮራቲ በገጠማቸው ሕመም ህክምናን በጣሊያን ሲከታተሉ የነበረ ሲሆን በግንቦት 4,2008 ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የቫቲካን ሬዲዮ የአማሪኛ እና የትግረኛ ክፍል በእዚህ አጋጣሚ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለኮንቦኒ ማሕበር አባላት በተለይም ለማሕበሩ የበላይ አለቃ ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ፣ ለሀዋሳ ሀግረ ስብከት ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን እንዲሁም ለምያውቁዋቸው እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

እግዚአብሔር ምህረቱን ይስጥልን ነብሳቸውንም በአብረሃም በይሳቅ በያዕቆብ ጎን ያኑርልን። አሜን።

ምንጭ፣ www.comboni.org








All the contents on this site are copyrighted ©.