2016-05-12 11:28:00

ቅ.አ. ፍራንቸስኮ "መንፈስ ቅዱስ ሚስዮናዊያንን ለወንጌል አገልግሎት እራሳቸውን እንዲሰው ያነሳሳል" ማለታቸው ተገለጸ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ ዘወትር ጥዋት በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት ስራዓት ቅዳሴን እንድሚያሳርጉ የሚታወቅ ሲሆን በግንቦት 2,2008 ባሳረጉት ስርዓተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት እና  ከገዛ ሀገራቸው ውጭ ለመሄድ እና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የወሰኑ ወንድ እና ሴት ሚስዮናዊያንን ባሕሪ ላይ ትኩረት ባደረገው ስብከታቸው መንፈስ ቅዱስ በቀዳሚነት ሚስዮናዊያንን ወንጌልን ለማወጅ የምንበለበለውን ፍላጎታቸውን እና ራቅ ወዳለ ስፍራ ሄደው ወንጌልን ያውጁ ዘንድ ሕይወታቸውንም ለእዚህ አገልግሎት መስዋዕት ያደርጉ ዘንድ ይመራቸዋል ማለታቸው ተገልጸ።

በእለቱ በተነበበው የመጀመሪያ ምንባብ ሐዋሪያው ጳውሎስን መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ እንዳዘዘው እና እርሱም ለመንፈስ ቅዱስ ታዛዥ እንደ ነበረ በምያወሳው ምንባብ ላይ ተመስርተው ቅዱስ አባታችን እንደ ገለጹት ይህ በመንፈስ ቅዱስ የተደረገ ጥሪ ሊቀለበስ የማይችል፣ ሕይወታችንን ለክርስቶስ መስዋዕት እንድናደርግ እና ለእርሱ አገልግሎት እንድናውል ወይም በእርሱ ምትክ እንድንሰቃይ የምጋብዘን ጥሪ ነው ብለዋል። ይህ የሐዋሪያው ጳውሎስን ልብ በመንፈስ ያነደደው የእሳት ነበልባል ዛሬም ቢሆን በብዙ ሀገራቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ጥለው የኢየሱስን መልካም ዜና ለማወጅ በሄዱ ወጣት ሚስዮናዊያን ልብ ውስጥም ዛሬም ይንበለበላል ብለዋል።

ሐዋሪያው ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ እያከናወነ የሚገኘውን ታላቅ ምስጢር ምንም እንኳን የተለያዩ መከራዎች እና ችግሮች ቢኖሩበትም፣ ሁል ጊዜም ወንጌልን እንድያበስር ይገፋፋው ነበር ያሉት ቅዱስነታቸው እኔ እንደ ማምነው ይህ ጥቅስ በየዘመናቱ ሚስዮናውያን ሕይወታቸውን ለወንጌል አገልግሎት እንዲያውሉ የሚያበረታታ ስሜት ይፈጥርባቸዋል ብለዋል።

ቅዱስ አባታችን ሚስዮናዊያንን በተመለከተ ምስክርነት ሲሰጡ “በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ወደ ፊት የምያራምዳቸውን ጥሪ ይጎናጸፋሉ፣ ወደ ቀብር ስፍራም በምንሄድበት ወቅት ሁሉ የቀብር ስፍራቸውን እናያለን ብዙዎቹም 40 ዓመት ሳይሞላቸው በወጣትነት እድሜያቸው ነበር ያረፉት ምክንያቱ ልያገለግሉ የሄዱበት ስፍራ ልምድ ስላልነበራቸው ታመው ከሕመማቸው ሳያገግሙ በመቅረታቸው ነው። ሀገራቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን የሚወዱዋቸውን ሰዎች ሁሉ ጥለው የወጣትነት እድሜያቸውን ሰውተዋል። ‘ይህንንም ማድረጌ ተገቢ ነበር’ ይሉም ነበር” በማለት በታላቅ ስሜት ውስጥ በመሆን የወንጌል ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የእዚህ ሁሉ መሰረት እና አነሳሽ የነበረው መንፈስ ቅዱስ እንደ ነበር ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም “ብዙ ሚስዮናዊያን ለወንጌል አገልግሎት በሚሄዱበት ስፍራ ምን ዓይነት ነገር እንደ ሚጠብቃቸው እንኳን አያውቁም” ብለው “ሐዋሪያው ጳውሎስ በሚሊጥንም ባደረገው የመሰናበቻ ሰላምታ ላይ ‘መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ ግድ እያለኝ ነው። ነገር ግን በምሄድባቸው ከተሞች ሁሉ እስራት እና መከራ እንደ ሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ ይመክረኛል’ እዳለው ሁሉ ሚስዮናዊ የምሄዱበት ስፍራ የምጠብቃቸው ሕይወት ቀላል እንዳልሆነ እያወቀም ቢሆን በእኛ ግዜ እንደ ሚታዩ ሐዋሪያት ወደ ፊት መሄዱን ግን አላቋረጡም” ብለዋል።

“ምስክርነትን የሚሰጡ የእኛ ሚስዮናዊያን አሁን እኛ ባለንበት ወቅት የሚገኙ ጀግኖች ናቸው ብለው ከአውሮፓ ወደ ሌሎች ሀገሮች የሄዱ ሚስዮናዊያን ወደ እናት ሀገራቸው መመለስ እንኳን ሳይችሉ ብዙዎቹ በእዚያው ቀርተዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው “ለሰጡት ታላቅ ምስክርነት እግዚአብሔርን ልናመስግን ይገባል” ብለዋል። “ብዙ ስማቸው እንኳን የማይታወቅ ሚስዮናዊያን ነበሩ” ያሉት ቅዱስነታቸው ሕይወታቸውን ለወንጌል አገልግሎት የሰው ስማዕት መሆናቸውን ገልጸው ሚስዮናዊያን የእኛ እና የቤተ ክርስቲያናችን ክብር ናቸው ብለዋል።

በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ቁልፍ የሆነ የአንድ  ሚስዮናዊ ጥራት የሚለካው ለመንፈስ ቅዱስ በምያሳየው “ታዛዥነት” መሆኑን ገልጸው ዛሬ በወጣቶቻችን ላይ የሚታየው የእርካታ ማጣት ስሜት ይወገድ ዘንድ እና በምትኩም ሕይወታቸውን ክቡር ለሆነ ነገር እንዲሰው እጸልያለው ካሉ ቡኋላ “ለእናንተ ወጣቶች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት በተለይም በአሁኑ ወቅት ‘በእዚህ ፍጆታን እንደ ባሕል አንድርጎ በሚቆጥረው  እና በእራስ ወዳድነት ባሕል በተሞላ ማህበርሰብ ደስተኛ አይደለሁም’   ለምትሉ ሁሉ ወደ አድማስ አሻግራችሁ ተመልከቱ፣ እዛም የእኛ ሚስዮናዊያንን ትመለከታላችሁ። እነ እርሱ እሩቅ ሀገር እንዲሄዱ እና ሕይወታቸውን እንዲሰው ወደ ላካቸው መንፈስ ቅዱስ ጸልዩ። ምንም እንኳን ይህ ከባድ ቃል ቢሆንም ቅሉ፣ ተገቢ በሆነ መንገድ ሕይወታችንን እንድንኖር ያደርገናል። ነግር ግን ይህንን ጥሪ ተገቢ በሆነ መንገድ መኖር ይኖርብናል፣ ሕይወታችንን ለእዚህ አገልግሎት መሰዋዕት ማድረግ እና ወደ ፊት መጓዝ  ያስፈልጋል። ይህም ወንጌልን በማወጅ የሚገኝ ደስታ ነው።” በማለት ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.