2016-05-04 09:41:00

ቅ. አ. ፍራንቸስኮ ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመትን ምክንያት በማድርግ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባደረጉት አስተምሮ ላይ ከሰማኒያ ሺ በላይ ሰዎች መገኘታቸው ታወቀ።


በሚያዝያ 22, 2008  ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመትን ምክንያት በማድረግ ዘወትር ቅዳሜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚደረገው የጠቅላላ አስተምሮ ላይ ለተገኙ ከ80 ሺ በላይ ለሚሆኑ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ “በምስጢረ ንስኋ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚፈልገውን ሰው ካህናት ኋጢያተኛው በመከራ የተሞላ ክፍል ውስጥ እንደገባ እንዲሰማው ከማድረግ ይልቅ ጥንቃቄ በተሞላው  እና አባትነትን በተላበሰ መልኩ መቀበል ይገባቸዋል” ማለታቸው ተገለጸ።

በቤት ውስጥ በተፈጠረው አለመግባባት  በተፈጠረ ቁርሾ ምክንያት የማይነጋገሩ ወንድማማቾች እንዲታረቁ የሚያደርገውን እና እንዲሁም በማሕበረሰብ ውስጥ ሰላም ይፈጠር ዘንድ አስፈላጊ የሆነው የሰላም ድልድይ መገንባት የሚጀመረው ምስጢረ ንስኋ በሚከናወንበት ሥፍራ በመሆኑ ምክንያት የእግዚአብሔርን ምሕረት በመሻት ወደ ንስኋ መጥቶ በአንድ ካህን ፊት የተንበረከከውን ኋጢያተኛ የባሰውኑ በነገር ማቁሰል ሳይሆን ከካህኑ የሚጠበቀው የእግዚአብሔርን ምሕረት ይለማመድ ዘንድ  በደንብ ማገዝ እንደ ሚጠበቅበት አበክረው ገልጸዋል።

ከ80 ሺ በላይ የሚሆኑ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመትን አስመልክተው የአስተምሮዋቸውን ትኩረት እርቅ እና ሰላምን መፍጠር በሚል አርዕስት ላይ በማድረግ አስተምሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እርቅ ምሕረትን ለማድረግ አንድ ወሳኝ ገጽታ” መሆኑን በአጽኖት ገልጸዋል።

“ብዙውን ጊዜ እኛ” አሉ ቅዱስነታቸው “ኋጢያታችን ከእግዚአብሔር ያርቀናል ብለን እናስባለን” ብለው “እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኃጥያትን በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ ከእርሱ መራቃችን አይቀሬ ነው” ካሉ ቡኋላ “እርሱ ግን እኛ በአደገኛ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ስለሚረዳ ከማንኛውም ጊዜ በላይ እኛን በመፈልግ እንደ ሚጠመድ” አስረድተዋል።

“አምላክ በምንም ዓይነት መልኩ አንድ ሰው ከእርሱ ፍቅር እርቆ እንዲኖር አይፈቅድም” በማለት አስተምሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ከእኛ የሚጠበቅብን ነገር ቢኖር በሠራነው ክፉ ነገር ማዘናችንን የሚገልጽ የጸጸት ምልክት ማሳየት እንደ ሚጠበቅብን” አበክረው ገልጸዋል።

“እኛ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ሁሉ ከአምላክ ፊታችንን እናዞራለን” በማለት አስተምሮዋቸውን የቀጠሉ ቅዱስነታቸው “ኢየሱስ አንድ ጊዜም እንኳን ፊቱን ከኋጢያተኛ አዙሮ አያውቅም፣ ነገር ግን እንደ አንድ መልካም እረኛ የጠፋውን በግ ፈልጎ እስክያገኝ ድረስ ደስ ስለማይሰኛ በቀጥይነት የጠፉትን በጎች ሁሉ ፈልጎ እስኪያገኝ ድረስ እረፍት እና እርካታ ሊኖረው አይችልም” ብለዋል።

“በእዚህ በያዝነው ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመት ሁላችንም ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ይገባናል”  ቅዱስነታቸው ብለው “ብዙ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር መታረቅን ቢፈልጉም ቅሉ፣ ነገር ግን እንዴት መታረቅ እንደ ሚገባቸው ግራ የተጋቡ ወይም እራሳቸው ተገቢ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው እና እንዲሁም ኋጢያተኛ መሆናቸውን አምኖ መቀበል የማይፈልጉም ብዙ ሰዎች ይኖራሉ” ብለው “በእዚህ ረገድ የክርስቲያን ማሕበረሰብ እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች  ከእግዚአብሔር ጋር ከልብ ይታረቁ ዘንድ ማበረታታት ይኖርባቸዋል” በማለት አሳስበኋል።

“ይህንን የእርቅ ተግባር እንዲፈጸም የምያደርገውን ምስጢረ ንስሐን የሚመሩ ካህናት፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ምሕረት ይዳሰሱ ዘንድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ያስፈልጋል” ያሉት ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ለካህናት በምያቀርቡት ማሳሰቢያ “እባካችሁን ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ለሚፈልግ ሰው እንቅፋቶችን አትፍጠሩ” ካሉ ቡኋላ “አንድ አናዛዥ ካህን በእግዚአብሔር የተሰጠውን ቦታ ስለያዘ እንደ አንድ ጥሩ አባት መሆን ይገባዋል” ብለው “ምስጢረ ንስሐን የሚፈጽም ካህን እርቅን በመሻት ወደ እርሱ የሚመጡትን ኋጢያተኞች ተቀብሎ ማስተናገድ እና በእዚህ በያዘው የእርቅ ጎዳን ይራመድ ዘንድ ማገዝ እንደ ሚጠበቅበት” አበክረው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዜና “በዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመትን አስመልክቶ በሚካሄደው የጠቅላላ አስተምሮ ላይ በወታደራዊ የሙዚቃ የማርሽ ባንድ ታጅበው  ከ20ሺ በላይ የሚሆኑ ወታደሮች እና የፖሊስ አባላት መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸውም በታላቅ ደስታ ሰላምታን እንዳቀረቡላቸውም ታውቁዋል።

እነዚህ ሴት እና ወንድ ወታደሮች ወይም የፖሊስ አባላት በተለያዩ አስቸጋሪ ሊባሉ በሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩትን ስደተኞች ከባሕር ላይ አደጋ የታደጉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ሕይወታችውን ለአደጋ በምያጋልጥ አጋጣሚ እንኳን ለእራሳቸው ነብስ ሳይሳሱ የሌላውን ነብስ መታደጋቸው ታላቅ ምስክርነት እንደሆነም በዕለቱ ተወስቶ ቅዱስነታቸውም “እናንተ የእርቅ ድልድይ ገንቢዎች እና ሰላምን የምትዘሩ ሰዎች ናችሁ፣ በእዚህ ተግባራችሁ ልትቀጥሉ ይገባል በማለት የማበረታቻ ቃላትን መሰንዘራቸውም ታውቋል።

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው “እኛም እራሳችን እርቅን መፍጠር የሚችል የመሸጋገሪያ ድልድዮችን መገንባት ይጠበቅብናል” ብለው “ያለነው በቅዱ ልዩ የምሕረት ዓመት ውስጥ በመሆኑ እርስ በእርሳችን እና እንዲሁም ከእግዚኣብሔር ጋር መታረቅ አስፈላጊ ነው” ብለው “በምንገኝበት ቦታ ሁሉ ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ ተግባራትን በመፍጠር ለሰው ልጆች ሕልውና መሰረት የሆነውን ሕብረት እና ለሁሉም ተደራሽነትን ማሳየት ይጠበቅብናል” በማለት አስተምሮዋቸውን አጠናቀው ለሁልም ሰላምታን ካቀረቡ ቡኋል ቡራኬን ሰጥተው የእለቱን ዝግጅት ተጠናቋል። 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.