2016-03-22 11:46:00

“ሰውነታችሁ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው” ።


በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንድሁም  በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የእግዚኣብሔር ፀጋ እና ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

በኢትዮጲያ ስርዓተ ሉጥርጊያ አቆጣጠር ዛሬ ሶስተኛ የዓብይ ጾም ሰንበት ላይ የምንገኝ ስሆን፣ እለቱም ሰንበተ “ሙክራብ” ይባላል።

ይህ እለተ ሰንበት “ሙክራብ” ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ከዩሓንስ ወንጌል ከምዕራፍ 2, 12-25 በተጠቀሰው መሰረት፣ የአይሁድ የፋሲካ በዓል በተቃረበ ጊዜ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ወቅት በሙክራብ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚሸጡ እና የሚለውጡ ሰዎችን ባየ ጊዜ በገመድ የተሰራ ጅራፍ አዘጋጅቶ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አደረጋችሁት” በማለት ገርፎ እንድስውጣቸው እና ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ መዋል እንዳለበት በመመስከሩ እና በተጨማሪም መድኋኒታችን በአይሁድ ምኩራብ ተገኝቶ ለታሰሩት ነጻነትን ለሞቱት ሕይወትን፣ ልድሆች ፍትህን  በፍርድ ላይ ላሉ ሁሉ የምህረት ዓመትን ለመስጠት መምጣቱን የምንዘክርበት ሰንበት በመሆኑም ጭምር ነው።

 

የዛሬ ዕለተ ሰንበት የውንጌል አስተምሮኋችን የምያተኩረው ኢየሱስ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አደረጋችሁት” ብሎ በቤተ መቅደስ ሲነግዱ እና ስለውጡ የነበሩ ሰዎችን ከቤተ መቅደሱ ማስዎጣቱን በጥልቀት እንመለከታለን።

ለ መሆኑ ቤተ መቅደስ ምንድነዉ? በመጻሐፍ ቅዱስ ወስጥ እንዴት ይገለጻል?

በብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስ   የእግዚአብሔር ታቦት ማደሪያ በምድር የእግዚኣብሔር ህልውና መገለጫ ተደርጎም ይታያል።

በተጨማሪም ቤተ መቅደስ በኦሪት ዘፍጥረት በምዕራፍ 26:24 ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ይሳቅን “እኔ ካንተ ጋር ነኝ አትፍራ” እንዳለው እና በኦሪት ዘፀአት 33:7 ጀምሮ  እንደ ተገለጸው ሙሴ ከእግዚኣብሔር ጋር የመገናኛ ድንኳን በመሥራት እግዚአብሔርን ይነጋገር እንደነበረና፣ የእግዚአብሔር ታቦት ማደሪያ ቤተ መቅደስ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበረ ማውሳቱ፣ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር  በምድር ከሕዝቦቹ ጋር መኖሩን የምያሳይ ቋሚ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።  

ዛሬ በወንጌል የተጠቀስው ቤተ መቅደስ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀው በንጉስ ሰለሞን ጊዜ እንደነበረ 1 መጻሓፈ ነገስት ምዕራፍ 8 ከቁጥር 22 ጀምሮ የተጠቀሰ ስሆን ሰለሞንም በምረቃው ወቅት ለእግዚኣብሔር ባቀረበው ጸሎት “ነገር ግን አምላክ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፣ ታዲያ እኔ ያሰራሁት ቤተ ማቅደስ ምኑ ሊበቃህ!” ብሎ እርሱ ያሳነጸው ቤተ መቅደስ ለታላቁ እግዚአብሔር ማደሪያነት ይሆን ዘንድ በቂ እንዳልሆነ መናገሩ ይታወሳል።

ነገር ግን እግዚአብሔር ለሰለሞን “በፊቴ ያቀረብከውን ጸሎት እና ልመና ሰምቻለው፣ ይህን የሠራኸውን ቤተ መቅደስ ስሜን ለዘላለም በዚያ እንዲኖር በማድረግ ቀድሸዋለው። ዐይኖቼ እና ልቤ ምን ጊዜም በዚያ ይሆራሉ” ብሎ እንዳጸናው 1በመጻሓፈ ነገስት በምዕራፍ 9:3 መገለጹ ይታወቃል።

እግዚአብሔርም  ቤተ መቅደሱን አስመልክቶ ለሰለሞን እንዲህ ስል ተናገረ “ነገር ግን አንተም ሆንህ ልጆችህ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ ብትመለሱ፣ የሰጠኋችሁ ትእዛዞች እና ሥርዐቶችን ሳትጠብቁ ብትቀሩ፣ ሂዳችሁ ሌሎች አማልዕክቶችን ብታመለኩ እና ብትሰግዱላቸው እኔም እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላቸኋለው ስለ ስሜ የቀደስኩትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለው” ብሎ ለሰለሞን እና ለእስራኤል ሕዝብ አሳስቡኋቸው እንደ ነበረ ይታወቃል።

የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ቤተ መቅደስ  ሊከበር እና ልክ ሙሴ “የመገናኛ ድንኳን” ብሎ እንደ ሰየመው ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበት፣ የምንወያይበት፣ ለችግሮቻችን ጥያቄን የምናቀርብበት፣ ለሰላም እና ለብልጽግና ይምንፀልይበት በተጨማሪም ለተደረጉልን ነገሮች ሁሉ ለእግዚኣብሔር ምስጋና እና ውዳሴ የምናቀርብበት ስፋራ ሊሆን ይገባል።

ዳዊት በመዝሙሩ “በሌላ ሥፍራ ሺ ቀን ከመኖር፣ በቤትህ አንድ ቀን መዋል ይሻላል” ማለቱ የምያሳየን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መቆየት ከየተኛውም ሥፍራ በተሻለ  ሰላምን፣ ደስታን እና በረከትን ያጎናጽፋል።

በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 1:17 እና 2:27-32 እንደ ተገለጸው የታላቁ የአዲስ ኪዳን ነብይ የሆነው የመጥምቁ ዩሓንስ መወለድ  የተበሰርው በቤተ መቅደስ መሆኑን፣ አዳኛችን የሆነው ኢየሱስ ከተወለደ ቡኋላ በሙሴ ሕግ መሰረት የመንጻት ስነ-ስረዓት ለመፈጸም ወደ ቤተ መቅደስ መወሰዱ እና “ጌታ ሆይ ቃል በገባኸው መሰረት አሁን ባርያህን አሰናብተው ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይቱዋልና” ብሎ ስምሆን ስለ ህጻኑ ኢየሱስ ምስክርነት የሰጠውም በዚሁ ቤተ መቅደስ መሆኑ ይታወቃል።

ያለምክንያት አይደለም ኢየሱስ በተደጋጋሚ በቤተ መቅደስ በመገኘት ሕዝቡን ስያስተምር የነበረው። ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ቃል መስምያ እና መማሪያ ቦታ መሆኑን ልያስገነዝበን ስለፈለገ እንጂ።

ያለምክንያት አይደለም ኢየሱስ በቤተ መቅድስ ሆኖ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደኔ ይምጣና ይጠጣ ያለው፣ ቤተ መቅደስ የሕይወት ውሀ የሚፈልቅበት የእግዚአብሔር ፀጋ የሚታፈስበት ሰላም እና ጤና የሚገኝበት ሥፍራ መሆኑን ልያስረዳን ፈልጎ ነው እንጂ።

ያለምክንያት አይደለም በዩሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 8: 1-11 እንደተጠቀሰው ኢየሱስ በቤተ መቅደስ በነበረበት ወቅት ስታመነዝር የተገኘችውን ሴት አይሁዳዊያን ባመጡለት ጊዜ “እኔም አልፈርድብሽም በይ ሂጅ፣ ከእንግድህ ግን ሐጥያት አትስሪ” ያላት ቤተ መቅደስ ለሐጥያታችን ይቅርታን የምናገኝበት ቅዱስ ስፍራ መሆኑን ልያስረዳን ፈልጎ ነው እንጂ።

በአጠቃላይ ቤተ መቅደስ ይቅርታ እና ፀጋ የሚገኝበት ሥፍራ በመሆኑ ሊከበር የሚገባው ሥፍራ ነው። የመልካም ነገር ምንጭ የሆነው የእግዚአብሔር ማደሪያም ጭምር ነው ቤተ መቅደስ።

ለዚህም ነው እንግዲህ በዛሬ ወንጌል እንደሰማነው ለዘመናት ተጠብቆ የነብው የቤተ መቅድስ ህልውና ተቀትሮ እና ተለውጦ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የመልካም ነገር መፍለቂያ፣ ይቅርታ የምናገኝበት ሥፍራ መሆኑ ተረስቶ፣ የሰላም እና የደስታ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ እንድሚገኝ ተዘንግቶ፣ በተቃራኒው መነገጃ እና የዓለማዊ ተጋብራት የሚፈጸሙበት ቦታ ሆኖ መገኘቱ ነው ኢየሱስን ያስቆጣው እና “ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ  የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” በማለት በዚያ ይነግዱ የነበሩትን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ያስወጣቸው።

የቤተ መቅደስ ህልውናን መጻረር ኢየሱስን እንደ መጻረር ይቆጠራል የተከበራችሁ ወዳጆቼ። በዩሓንስ ወንጌል 2: 21 “ኢየሱስ ቤተ መቅደስ ሲል ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር” ይለናል። በማንኛውም መልኩ ቤተ መቅደስን ስናረክስ፣ ያልተገቡ ተጋባራትን ስንፈጽም፣ የመፀለያ ቦታ መሆኑ ተረስቶ በአንጻሩ ደግሞ የጥል እና የክርክር ቦታ ስናደርገው፣ አሁን ባለንበት ወቅት  በተለያዩ የዓለማች ክፍሎች እንደምናየው እና እንደ ምንሰማው ዓብያተ ክርስቲያናት እና የጸሎት ቤቶች ሲፈርሱ እና ሲቃጠሉ፣ የተቀደሱ እግዚአብሔር የሚወደስበት ቁሳቁሶች እና የተቀደሱ ምስሎች ሲወድሙ ስናይ እና ስንሰማ በእግዚኣብሔር እና በክርስትያኖች ላይ የተቃጣ ጥቃት በመሆኑ አትብቀን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ልንቃወም እና በተለይም በሰይጣን አነሳሽነት የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ የክርስቲያኖች መሳሪያ በሆነው ጸሎት ልንዋጋው ያስፈላጋል።

ሐዋሪያው ጳውሎስ 1 ቆሮ 6: 19 ላይ “ሰውነታችሁ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆኑን ታውቃላችሁ?”ይለናል። በመቀጠልም ወደ ሮሜ ሰዎች 12: 1 ላይ “እንግድህ ወንድሞቼ ሆይ ሰውነታችሁ ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚኣብሔር ርህራሄ እለምናችኋለው” ይለናል።

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እና እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ

እንደ ቤተ መቅደስ የሆነውን እና በውድ ዋጋ የተገዛውን እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችን ማርከስ ማለት በውድ ዋጋ የገዛንን ኢየሱስን ማሳዘን ማለት ነው። በቤተ መቅድስ ውስጥ ሲነግዱ ለነበሩትን ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ “የአባቴን ቤት አታርክሱ” እንዳለው እኛም ያልተገባ ነገር በሰውነታችን በምንፈጽምበት ወቅት ሁሉ፣ ኢየሱስን እንደ ምናሳዝን አውቀን እነዚህን ተጋባራት ልናስወግድ ይገባል። ሰውነታችንን ማክበር ማለት ኢየሱስን ማክበር ስለሆነ፣ በተጨማሪም እግዚአብሔር ሊገኝ የሚችለው በተቀደስ ሥፍራ ብቻ መሆኑንም በመረዳት እራሳችንን ከእርክሰት ልንጠብቅ ይገባል።

“ሰውነታችሁ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው” ይለናል ሓዋሪያው ጳውሎስ፣ በሰውነታችን እግዚኣብሔርን ላናከብረው ያስፈልጋል። በተለይም አሁን በያዝነው ሦስተኛ የጾም ሳምንት እግዚኣብሔርን ልንለምነው እና ልንጠይቀው  የሚገባን ዋንኛ ጉዳይ፣ ሰውነታችን ከምያረክሱት ተግባራ በመቆጠብ፣ በምትኩም ለእግዚኣብሔር ክብር ያደረ እና የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ሊሆን የሚችል ሰውነት ይሰጠን ዘንድ ልንጸልይ ያስፈልጋል።

የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነውን የሰውነታችንን  ክብር ጠብቀን መጓዝ እንድንችል እግዚአብሔር ሁላችንንም በፀጋው ይሙላን።  አሜን።

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.