2016-03-21 18:48:00

ለብዙ ሰዎች የስደተኞች ጉዳይ ኣያሳዝናቸውም


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ትናንትና  የላቲን ስርዓት በሚከተሉ የተከበረው በዓለ ሆሳዕና ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ባቀረቡት ስብከት ‘ኢየሱስ በጊዜው የግድ የለሽነት ሰለባ ሆኖ እንደነበር ዛሬም በዓለማችን የሚገኙ ብዙ ስደተኞችና የተገለሉ ሰዎች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ በማይፈልጉ ግድየለሾች ሰለባ ሆነው ይገኛሉ’ ሲሉ ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ምእመናንና ነጋድያን እንዲሁም ቤተክህነት በተገኙበት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ሰብከዋል።

ከቅዳሴ ኣስቀድሞ በተፈጸመው የሆሳዕናና የወይራ ቅርንጫፎች ቡራኬ ሲሆን ቅዱስነታቸው የመሩት ዑደተ ሆሳዕና ሲፈጸም ለሁሉም የተባረከውን የሆሳዕና ዘንባባ ኣድለዋል፣ በዕለቱ የተነበበው ቃለ ወንጌል ስለ የኢየሱስ ሕማማት የሚናገር ነበር፣ ቅዱስነታቸውም ‘እግዚኣብሔር የሆነው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፣ ንጉስ የሆነው ጌታ የባርያ መልክ ለብሶ ባርያ ሆነ። የባሰውኑ ደግሞ ይህ የውርደት ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲመጣ እጅግ ኣሰቃቂ በሆነ መንገድ ሲሸት ሲክዱት በውሸት ሲከሱት ሲሰድቡት ሲገርፉት ከእርሱ ይልቅ ኣንድ ሽፍታና ነፍሰ ገዳይን ሲመርጡ በሚስማር በመስቀል ላይ ሲጨነክሩት፣ ያ የመላው ዘመደ ኣዳም ኣዳኝ የሆነው ይህ ሁሉ ግፍ ሲወርድበት እጅግ የሚያሳዝን ነው፣ የኢየሱስ ውርደት መጨረሻው ይህ ነው ለማለት የማይቻል ወደ ኢምንትነት የሚቀይር ነው፣ ወደ ኢየሩሳሌም በኣህያ ላይ ተጭኖ ሲገባ ሆሳዕናን እያወዛወዙ ንጉሳችን እንዳላሉት ሁሉ ወዲያውኑ ስቀለው ሲሉ መስማት ይገርማል፣

‘ያኔ ልክ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባው ዛሬም በከተሞቻችንና በሕይወቶቻችን ለመግባት ይፈልጋል፣ እውነተኛውን የደስታ ምንጭና እውነተኛ ደስታ የሆነውን ጌታ ኢየሱስን በከተሞቻችንና በሕይወቶቻችን ለመንግባት የሚከለክል ነገር ሁሉ እናስወግድ፣ ከሓጢኣት መታሰር ከሞትና ከፍርሓት እንዲሁም ከሓዘን ሊያድነን የሚችል ኢየሱስ ብቻ ነው` ሲሉም ልቦቻችን ለእርሱ እንድንከፍት ኣሳስበዋል፣

ሶሙነ ሕማማት የእግዚኣብሔር ልጅ ክብሩን ትቶ ኢምንት ሆነ ከሓጢኣት በስተቀር በሁሉ እኛን መሰለ፣ የሓዋርያት እግር በማጠብም የባርያ ስራ በመስራት እስከ መጨረሻ እንደሚያፈቅረን ኣሳየ፣ በፈጸመው ድርጊት ያስተማረን ምሳሌ እኛ የሱ ፍቅር እንደሚያስፈልገን ነው ለኛ ሲል ዝቅ ማለቱና ያለሱ ፍቅር መኖር አንደማንችል ነው እኛ በመጀመሪያ ክርስቶስ እንዲያፈቅረን ካላደረግን ሌላውን ልናፈቅር ኣንችልም። የክርስቶስን ኣስደናቂ ፍቅርና ርህራሄን ካልተለማመድን እውነተኛ ፍቅር ሌሎችን በተጨባጭ ድርጊት ማገልገል ማለት መሆኑን አንረዳም።

ኣያይዘውም ክርስቶስ ከጸሎተ ሐሙስ እራት በኋላ የተቀሩት ግዜያት በጣም አስቸጋሪ አንደነበሩ በማስታወስ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስጋው የመስቀል ስቃይ ውርደት ግርፋት ሰቆቃ ባሻገር  በውስጡ መሰቃየቱንና መዋረዱን እንዲሁም የሞት ፍርድ እንዲፈረድበት የወሰኑት ባለስልጣናትም ትክክለኛው ፍትሕ ለመስጠት ሳይሆን የገዛ ራሳቸው ጥቅም በመመልከት የነበረ ሲሆን ዛሬም እንዲሁ  በምንኖርበት ሕብረተሰብ ውስጥ ስደተኞችን በተመለከተ  እየተከሰተና ከፍተኛ ችግር መሆኑን  አመልክተዋል።

‘ጌታችን ኢየሱስ ግድየለሽነት የሚያስከትለውን በገዛ ራሱ ኣየው፣ ይህም የእርሱን ሁኔታና መጨረሻ ማንም ሃላፊነት ሊወስድለት ኣልፈለገምና፣ ዛሬም ብዙ ተፈናቃዮችና ስደተኞችን ሳስብ ልክ እንደዚያው ስለሁኔታቸው መጻኢ ዕድላቸው ሃላፊነት የሚወስድ የለም፣ ሲሉ ካሳሰቡ በኋላ ስለመስቀሉ ጉዳይም ‘ከስቃዩ የባሰ ደግሞ በመስቀል መሰቀሉ ሲሆን ሁለመናውን በኣባቱ እጅ በመተው እንደ ኢምንት ሆነ፣ ይህን በሙሉ እምነትና መተማመን እንዲሁም ሁሉንም እያፈቀረ ቅርብ ያሉትም ይሁን ሩቅም ላሉት እንዲያው የሚገድልቱን ሳይቀር ኣፍቅረዋል፣ በመስቀል ተንጠልጥሎም የኣባቱን ገጽታ የምሕረት ገጽታን ያሳያል የሰቀሉትን ይምራል፣ በቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረው ሌባ የመንግስተ ሰማያት በርን ይከፍታል የሞተ ኣለቃው ልብን ይነካል፣ እስከ ሲኦል በመውረድም ለጨለማ ብርሃን ለሞት ሕይወት ለጥላቻ ፍቅር ሰጠ፣ የእግዚኣብሔር ኣስራር እጅግ ሩቅ ሆኖ ሊሰማን  ከባድም ሊመስለን ይችላል፣ ነገር ግን መንገዱን እንድንከተል የተጠራን ነው ይህም የኣግልግሎትና ገዛ ራስን ትቶ ለሌሎች የማገልገል መንገድ ነው፣ በዚሁ ሶሙነ ሕማማት ታላቁ የእግዚኣብሔር ቤት ትምህርት ቤት የሆነውን መስቀሉን በመመልከት ይህንን የኣግልግሎት መንገድ ዛሬውኑ መጀመር እንችላለን፣ ኣዳኝና ሕይወት ሰጪ የሆነውን ትሕትና የሞላበት ፍቅር እንድንማር ይሁን’ ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣ 








All the contents on this site are copyrighted ©.