2016-02-10 15:23:00

የጦርነት ገጽታ በጦርነት ውስጥ


የጦርነት ገጽታ ከጦርነት አውድማ በሚል ርእስ ሥር የተመራ የጦርነት አስከፊው ጸረ ሕይወት ገጽታውን የሚያጎላ የስእላዊ ዘገባ ትርኢት እ.ኤ.አ. የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የቅድስት መንበር ዜናና ኅትመት ክፍል ተጠሪ የቫቲካን ረዲዮ ዋና አሥተዳዳሪ አባ ፈደሪኮ ሎምባርዲ ባፍጋኒስታን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በሚመራው የሰላም አስከባሪ ኃይል በመታቀፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኘው ለኢጣሊያ አየር ወለድ ቆሞስ አባ ማርኮ ሚኒኒና በሮማ ቶር ቨርጋታ መንበረ ጥበብ አስተማሪ ፕሮፈሰር ማሲሞ ባልዱቺ በተገኙበት ዓውደ ጉባኤ በቫቲካን ረዲዮ ሕንጻ በሚገኘው ማርኮኒ የጉባኤ አዳራሽ በይፋ መከፈቱ የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ አመደዮ ሎሞናኮ ገለጡ።

ስእላዊው ዘገባ ስለ ጦርነት ስለ እኵይ ተግባር ስለ ሓጢኣት ከዚህ ጋር ተያይዞም የሚጋባው ስቃይ እንዲስተነተን ብቻ ሳይሆን ይኸንን ጸረ ሰብአዊ ባጠቃላይ ጸረ ተፈጥሮ የሆነው ሰው ሰራሽ አደጋ ወደ እምነትና ወደ ምኅረት የሚመራ መሆኑ አባ ሎምባርዲ ባስደመጡት ንግግር ጠቅሰው፦ ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእግዚአብሔር ምኅረት በጥልቀት ያስተነተኑትና የምኅረቱ ጸጋ በጥልቀት ልዩ ጥናት እንዲያካሂዱ ያነቃቃቸው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሆኑ ባንድ ወቅት የተናገሩትን ሃሳብ አባ ሎምባርዲ አስታውሰው በዚህ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ባወጁት የምህረት ዓመት በሚገባ ሊስተነተን የሚገባው ርእስም እርሱ ነው እንዳሉ ሎሞናኮ ገለጡ።

ይኽ በቫቲካን ረዲዮ ሕንጻ እ.ኤ.አ. እስከ የተካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ለትርኢት የሚቀርበው የጦርነት ገጽታ የሚያወሳ የስእላዊ ዘገባ ትርኢት እስከ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢጣሊያ ሮማ ከተማ የባህር ኃይል ዋና ሕንጻ የጉባኤ አዳራሽ በመቀጠልም በተለያዩ በኢጣሊያ ከተሞች ትራኢቱ ቀርቦ ከዛም ወደ ጀርመንና አውስትሪያ እንደሚዛወር ሎሞናኰ ይጠቁማሉ።

ጦርነት የማይደለዝ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ጸረ ሰብአዊ ተግባር ነው፣ ጦርነት ባለበት ክልል ስትገኝ እዛው መኖር በጣም የሚያስደነግጥ ልብን የሚያኮማትር ሁነት ፊት ለፊት ይደቅናል። መገዳደል፣ ሌላውን ከዚህ ዓለም በሞት በመለየት ገቢ የሚገኝበት ሁነት ነው። በቅድሚያ ጦርነት እንዳይኖር የሚመኘው የመከላከያ ኃይል አባላት ናቸው፣ ጦርነትን በጦርነት አውድማ ውስጥ በመኖር የሚያውቁት ጦርነት የሚቃወሙ ናቸው። የጦርነት ገጠመኝ አስተሳሰብን ሕይወትን ሁሉ ይቀይራል፣ ሆኖም ሞት የሚያስፋፋ ግጭትና አመጽ የሚያነቃቃ ተግባር መግታት ግድ መሆኑ አባ ማርኮ ሚኒኒ ባስደመጡት ንግግር ያመለከቱ ሲሆን፦ በመቀጠልም ፕሮፈሰር ባልዱቺ ይኽ ያፍጋኒስታን ሁኔታ በስፋት የሚያወሳው የስእላዊ ዘገባ ትርኢት አፍጋኒስታ የተከፋፈለች አደንዛዥ እጸዋት የሚመረትባት በጎሳና በቋንቋ የተከፋፈለች፣ ፍትህና ሥርዓት ከማንገስ ይልቅ ብሔርተኝነት የሚቀድምባት አገር ነች፣ ጸረ ማእከላዊ መንግሥት የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች ፖለቲካዊ እቅድ ያላቸው ሳይሆን የአደንዛዥ እጽዋት ምርት ባለ ንብረት በመሆናቸው የአደንዛዥ እጸዋት ንግድ ለመቆጣጣር ባላቸው ፍላጎት ላይ የጸና ነው። ስለዚህ ዓላማቸው አገር ሳይሆን የአደንዛዥ እጸዋት ንግድ ዋስትና መስጠት የሚል ነው እንዳሉ ሎሞናኮ አስታውቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.