2016-02-08 09:11:00

እኛም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር አደራ አለብን፤


ሉቃስ 2፡41-52 - ኢየሱስን መፈለግ

ይህ የወንጌል ክፍል ሕጻኑ ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከወላጆቹ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል እንደሔደ እና ከበዓሉም በኋላ እሱ በቤተ መቅደስ እንደቀረ፣ወላጆቹም ከሦሰት ቀናት ፍለጋ በኋላ እንዳገኙት የሚተርክ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ማርያም ይህ የእግአብሔር አደራ አለባቸውና እንደገና ወደኋላ ተመልሰው መፈለግና ማገኘት ግድ ሆኖባቸው ነበር፡፡

እኛም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር አደራ አለብን፤ ልጁን ልኮልናል፣ብዙ በረከትን በእቅፋችን ውስጥ አስቀምጧል፣ጸጋን ሰጥቶናል፤ ይህን ክቡር የሆነውን የአምላክ ስጦታ እንዴት ነው የያዝነው? ኢየሱስ ከሕይወታችን የራቀ ሲመስለንስ እንዴት ነው ወደፍለጋ የምንወጣው? የት ነው ኢየሱስን የምንፈልገው?

ለኢየሱስ ያለን ፍቅር እሱን ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት እና በምንደክመው ድካም ይለካል፡፡ ከሁሉ በማስቀደም ኢየሱስን ለመፈለግ ስንነሳ ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል ምክንያቱም ይህ ጉዞ ተጀምሮ ግማሽ መንገድ ላይ የሚተው አይደለም፡፡ ከኢየሱስ ወላጆች ይህን ጽናት ነው እንደ አብነት መውሰድ የሚገባን፡፡ እነሱ እንደሚያገኙት አምነው ነው የወጡት፡፡ በመጨረሻም የፈለጉትን አገኙ፡፡ እግዚአብሔር በቅን ልብ ለሚፈልጉት ጊዜውን ጠብቆ ይገለጣል፣በልባቸውም በመገኘት ደስ ያሰኛቸዋል፤ይህን አምላክ በተረጋጋ ልብ እና መንፈስ መፈለግ፣ፍለጋውም በእምነት እና በተስፋ የታገዝ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በትንሹም በትልቁም ማጉረምረም እና ማማረር ሳይሆን እንደነዚህ ሁለት ቅዱሳኖች በትዕግስት በመጽናት መጓዝ ነው፣ክርስቶስን የራስ እስከ ማድረግ ድረስ መትጋት፣ለጸሎት እና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚያገናኙን መንፈሳዊ ሰዓታትና መንፈሳዊ ተግባራት  ታማኝ መሆን፡፡

ቀላልና የተመቻቸ ሕይወት የለመደች ነፍስ ግን በመንፈስ እንቅልፋም ትሆናለች፤ ድካምን፣ተጋድሎን፣ መስዋዕትነትን የምትጠላ፣መስቀልንም የምትጸየፍ ከሆነ  ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው ማጉረምረም ብቻ የሚቀናት ነፍስ ኢየሱስን ማግኘት አትችልም፣የክርስትናው መንገድ ይከብዳታል፡፡

አምላካችን ግን ራሱንም ሆነ በእኛ ላይ ያለውን ዕቅድ፣ፍቃዱንም የሚገልጽልን ተግዳሮቶችን በትዕግስት መቀበልና ማስተናገድ ስንችል ነው፤ እሳት ሸክላን እንደሚያጠነክር ፈተናም ነፍስን፣እምነትን፣ክርስትናን ያጠነክራል፤ በዚህ በእምነት ጉዞ፣በየዕለቱ ክርስቶስን የበለጠ ለማግኘትና የራሳችን ለማደረግ በምንደክመው ድካም ፈተና እንዳይገጥመን የምንሻና የምንመኝ ከሆነ መንገድም ምርጫም ተሳስተናል፤ ይህን ስላወቁ ነው ዮሴፍና ማርያም እነዚያን ፈታኝ ቀናት በትዕግስትና በእምነት የኖሯቸው፤በዚህ በፈተና መንገድ በመራመዳቸው የበለጠ በእምነት ጠንካሮች ሆኑ፡፡ ስለዚህ ማንም ሳይፈተን አይቀርም፤ እንኳን እኛ ክርስቶስ ራሱ መስቀልና ፈተና በበዛበት መንገድ ነው የተጓዘው፤ «ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ» እስከማለት ደረሶ ነበር፤ ጌታችን ግን እዚያ ላይ አላቆመም፣ጉዞውን አላቋረጠም  «ያንተ ፍቃድ ይሁን» ብሎ እስከ መጨረሻው የመስቀል መስዋዕትነት ራሱን አቅርቧል፡፡ ምክንያቱም የመጣው በአባቱ ቤት ለመገኘትና የአባቱን ፍቃድ ለመፈጸም ነው፡፡

ስለዚህ ኢየሱስን ስንፈልግ እንደ ዮሴፍና ማርያም እምነትንና ትዕግስትን ስንቅ አድርገን ነው፡፡ ተራ እና ቀላል መንገድንማ እምነት የሌላቸውም ሰዎች ሊጓዙት ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን  ሕይወት መኖር ለማን ያዳግተዋለ? ይህ ተራና ቀላል መንገድ ግን ክስትናውን አያጣፍጠውም፡፡ እነዚህ የኢየሱስ ወላጆች ባለፉበት መንገድ ማለፍና ወደ ቅድስና ለመድረስ ግን አድካሚውንና ተራራማውን መንገድ በትዕግስት፣በእምነትና በተስፋ መጓዝ የግድ ነው - ክርስቶስን ለማግኘትና ከእርሱ ጋር ለመወገን፤

ከኢየሱስ መልስም የምንማረው ትልቅ ትምሕርት አለ፡፡ እርሱ ከወላጆቹ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ «ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አታወቁምን?» ነበር ያላቸው ከአባቱ የተቀበለውን ተልዕኮ ሲያመለክት፤ በወንጌልም «አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ፈልጉ» ነውና የተባለው (ማቴ 6፡33)፡፡ በእንዲህ ያለ መንፈስ፣በየዋህ ልብና በክርስቲያናዊ ፍቅር የሚመላለስ አማኝ እንደ ብላቴናው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በጥበብና በጸጋ እንዲሁም በሞገስ ያድጋል፣ ጣፋጭ የሆነ የክርስትና ሕይወትን መኖር ይችላል፣ከእግዚአብሔርም ጋር በቅርብ ይተዋወቃል፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእከቱ «ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል የሚለን» (ያዕ 4፡8).








All the contents on this site are copyrighted ©.