2016-01-07 10:36:00

የሰማዩ አባታችሁ መሃሪ እንደሆነ እናንተም መሃሪዎች ሁኑ (ሉቃ.6፡36)


† ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን

የምህረት ኢዮቤልዩ ዓመት  እንዲከበር ምክንያት የሆኑም ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ናቸው፡፡  እ.ኤ.አ በ2015 አጋማሽ ላይ የምህረት ልዩ ኢዮቤልዩ ብለው ያወጁት ካወጁት በኋላ ጽሑፍም ወጥቷል፡፡  ባለፈው በታህሳሳ ወር በእመቤታችን ያለአዳም ኃጢያትየ ተፀነሰችቅድስት ድንግል ማርያም  በዓል በሚከበረው ቀን ይህ አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ባዘዙት መሠረት በመላው ዓለም የምህረት ዓመት ካቶሊካውያን ሁሉ ተቀብለው ጳጳሳቱም በሉበት ሀገረስብከት የሚገኙ የካቴድራሎችና የተመረጡ ገዳማት በሮች በመክፈት ሥርዓቱ እንዲጀመር ሆንዋል፡፡ ይህ ለአንድ ዓመት በሚቆየው በምህረት ጸጋ መላው አማንያን እንዲጠቀሙበት  መንፈሳዊ ጥሪ ቅዱስ አባታችን አቅርበዋል፡፡

ይህንም የምህረት አዋጅ በሚያውጁበት ጊዜ በዓለም ላይ ለየት ያለ ሁኔታ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያንም ውስጥ እንደዚሁ፡፡ እሳቸው በእውነቱ ፀልየውበት፣ተማክረውበት  እንዲሁም በዓለም ላይ በሚጓዙበት ጊዜ በአዩት ሁኔታ ላይ ተመስርተው እስቲ ወደ እግዚብሔር ቃል እንመለስ በማለት ነው ያወጁት፡፡ ልዩ የተባለው ደግሞ ኢዮቤልዩ የሚያደርጉት ብዙ ጊዜ ኢዮቤልዩ በ25፣ 50፣ በ75፣ በ100 ዓመት እየተባለ ነው የሚደረገውና የሚከበረው፡፡

ይሄ ግን ልዩ ብለው እሳቸው የወሰኑት የዓለምን ሁኔታ ብናይ እሳቸው የሚሉት በአሁኑ ጊዜ ባይታወጅም 3ኛ የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ነው ብለው ብዙ ጊዜ ይናገራሉ፤ እንዴት ቢባል እንደ ድሮ ጦርነቱ እዚህም እዚያ ተቧድኖ ሳይሆን አልፎ አልፎ በሚደረጉ ግጭቶችና አልፎ በሚደረጉ ጦርነቶች እየተባባሰ ነው፡፡ በቤተሰብ ላይ ያለ ተግዳሮት፣ በጎረቤት መካከል ፣በሀገር መካከል  ያለው ሁሉ አሳሳቢ ነው፡፡ በዚያ ላይ የተፈጥሮ ተግድሮቶች ሁሉ አሉ፡፡  በዚህ ላይ ጉዳት የሚደርሰው በሕዝብ ላይ ነው፡፡ በተለይ በአቅመ ደካሞች፣ በእናቶች፣ በልጆች ላይ ነው፡፡ ክቡሩ ሰው በከንቱ እየሞተና እየተፈናቀለ ነው በማለት ይሄ በጸሎት የእግዚአብሔርን ምህረት በመለመን የምንቁቋመው ነው ወደእግዚአብሔር እንመለስ ነው መልዕክቱ ጥሪው ፡፡ በሌላም ስደትን አይተናል በተለይ ሁል ጊዜ መላው ዓለም የሚያስታውሰው በስደት ላይ እያሉ አንድ አባት ከቤተሰብ መሃል አንድ ሕፃን ስለጠፋ ሲፈልጉ ቆይተው በመጨረሻ የተገኘው ባሕሩ ሲተፋው ባሕሩ አጠገብ በአሳዛኝ ሁኔታ ተደፍቶ ነበር፡፡ ያም መላውን ዓለም ልብ የነካ ሃዘን ፈጥሮዋል፡፡ በተለይም አውሮፓ የሰባዊ መብት የሚከበርበትና ለሰው ልጅ ክቡርነት የሚቆረቆሩ በሚባልበት  አገር ይሄ መድረሱ ያሳዝናል፡፡

በየባሕር ውስጥ ሰምጠው የሚቀሩ ስደተኞች ሁኔታም ልባቸውን ያቆስለዋል፤ ይከነክናቸዋል ስለእነርሱም ይናገራሉ፡፡  ከዚያ አልፎ ስለ ሽብርተኝነት ወይም የራስን እምነት አመለካከት በሌሎች ላይ በግድ ይሁን ብሎ ማስገደድና ካልሆነም የመግደል ሁኔታ  ቅዱስነታቸው ያሳዝናቸዋል፡፡ እንዲሁም የአየር ጸባይ መለዋወጥ በየቦታው ስናይ ሚጐዳው በድህነት ውሰጥ የሚገኘው ክፍልና ተፈጥሮ ነው፤ ዓለም እኮ የጋራችን ናት የሁላችን ናት ሁላችን ልንከባከባት ይገባል በሚልም መልዕክት አውጥተው ነበር፡፡ ይህንን ተመርኩዘው መታዘዝንና መደጋገፍ ያሻል ስለዚህም ሁኔታ  በተባበሩ መንግሥታት ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ይሄ ሁኔታ የእግዚብሔር ምሕረት ያሻዋል ወደ እግዚአብሔር ልቦናችን እናቅርብ ነው ጥሪው፡፡ ስለዚህ ይህች ዓለም ሆነች እኛ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንዲሁም እያንዳንዳችን ግለሰቦች የእግዚአብሔር ምህረት ያስፈልገናል ከእያንዳንዳችን እንጀምር ነው ጥሪው፡፡

በካቴድራል በሮች መግባቱ ወይም የካቴድራል በር መክፈቱ እሱ ተምሳሌት ነው፡፡ ዋናው ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደእኔ ኑ ተመለሱ ንስሃ ግቡ እያለን እጁን ዘርግቶልናል፡፡  በሰራነው ኃጢያት ተጸጸተንና ንሰሐ ገብተን ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እግዚበሔር እየጠራን ነው የሚለውን መንፈስ ለመግለጽ የልባችን በር ከፍተን ወደ መቅደስ እንግባ ነው ተምሳሌነቱ፡፡

እግዚአብሔር እኛን ሊቀበል እጁን ዘርግቷል ዝግጁ ነው፡፡ እንቢ የምንል እኛ ነን የእግዚአብሔር ምህረት የማንጠይቅ እኛ ነን፡፡ እግዚአብሔር ግን ደጋግማችሁ ጠይቁን ባለን መሠረት ምሕረቱን ከለመን ምህረቱ ይወርዳል፡፡

ስለዚህ የሰማዩ አባታችሁ መሃሪ እንደሆነ እናንተም መሃሪዎች ሁኑ; እንዳልው /ሉቃ.6፡36/፡፡  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን አዝሎ የሚያሳይ ስዕል በዚህ ኢዮቤልዩ ዓመት ቀርቧል ጌታ አሁንም እኛ ለመሸከም ዝገጁ ነው፡፡ እኛ ግን ወደ እርሱ መቅረብ አለብን የሚል ነው አጠቃላይ የምህረት ዓመት ዓላማውና ግብ፡፡

በሀገራችን ይህንን የቅዱስ አባታችንን ቃል ሰምተን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ የቤተክርስቲያን ሀብት ነው፡፡ የእግዚብሔር ምህረት ትልቅ ሃብት ነው፡፡ ከእርሱ በላይም ምንም የለም፡፡ በምሕረቱ የሚገኘው ጸጋ ደግሞ እኛ የእርሱ ልጅ ሆነን ተደስተን እንድንኖር ነው፡፡ ስለዚህ ጸጋ ለማግኘት ሁላችን የምንሯሯጥበት ዕድል ነው፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ንሰሐ በማዘውተር በመቁረብ ለቤተክርስቲያን ጸሎት በማድረግ ለር. ሊ. ጳ. ጸሎት በማድረግ ለሃይማኖታችን በመቆርቆር ጠንካሮች ታማኝ ካቶሊክ ሆነን እነድንገኝ እስገነዝባሁ፡፡

እግዚአብሔር ባለበት ፍቅር አለ፣ ፍቅር ባለበት ሰላም አለ፡፡ አገራችን የዓለም  አካል ናት፡፡ በሌላ ቦታ ያለ ፈተናዎች ችግሮች መጠኑ ይለያይ እንጂ እኛም ዘንድ አለ፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ምህረት የምንለምንበት ነው፡፡ በዘወትር ፀሎታችን ጌታ ሆይ እንደምህረትህ እንጂ እንደ ኃጢያተቻን አይሁንብን በማለት ምህረትን ስንለምን እርስ በእርስ የመተዛዘን የመደጋገፍ ነገር  እናሳድጋለን፡፡ምሕረት ባለበት ሰላም አለ፡፡ በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን፣ተከባብረንና ተደጋግፈን እንድንኖር መፀለይ ብቸኛ መፍቴ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ያለንን ፈሪሃ   እግዚአብሔር ባሕላችንን አንተው፡፡ የእግዚአብሔር ምህረት ከቀደመ እሱ ወንድሜ ነው አሷ እህቴ ናት በማለት ተፈቃቅረን ለመኖር እግዚአብሔር ይህችን የተባረከች ምድር  ሰጥቶናል፡፡

እኛም ካቶሊካውያን በዚህ ላይ ትልቅ ድረሻ አለን፡፡ ሁልጊዜ የሰላም ጸሎት የሆነውን የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ጸሎት መፀለያችን አናቋርጥ፡፡ ከዚያም አልፎ የምህረት ዓመት ጸሎትም በቤተክርስቲያን ተዘጋጅቶ ቀርቦልናል፡፡ በዚህ መሠረት በየቤተሰባችን፣ በየቁምስናችን፣ በየገዳማት፣ ይህ ጸሎት በመፀይ የእግዚአብሔር የምህረት እጅ በእኛ ላይ እንዲሰራ ራሳችን መስጠታችን አንዘንጋ  ያኔ እኛም የምህረት ጥቅም የበለጠ እንረዳለን፡፡ስለዚህ በምህረቱ ዓመት ይቅርታውን፣ ሰላሙንና ፍቅሩን አግኝተን ሕይወታችን ለምህረት መንፈሳችንን ለማትጋት ተጋድሎዋችንን እንቀጥል፡፡ ለእኛ የመዳን ቀን ዛሬ ነው፡፡ የምህረት ኢዮቤልዩ ዓመት የተባረከ የተቀደሰ እንዲሆንልን የሃያሉ እግዚአብሔር ፀጋ አይለየን፡፡

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.