2015-11-04 16:20:00

ካላብሪያ፦ የስደተኞች ዓለም አቀፋዊ መካነ መቃብር ሥፍራ


በኢጣሊያ የካላብሪያ ክፍለ ሃገር በሚገኘው የታርሲያ ከተማ ምክር ቤት ከተለያዩ አገሮች በተለያየ ምክንያት ተገደው በሜዲትራኒያ የባህር በር በኩል በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱት በባህር ጉዞ እያሉ በሚያጋጥማቸው የሞት አደጋ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ለሚለዩት ለተለያዩ አገር ዜጎች ማረፊያ ዓለም አቀፍ የመካነ መቃብር ሥፍራ ለመገንባት ያጸደቀው የውሳኔ ስምምነት የካላብሪያ ክፍለ ሃገርና የኢጣሊያ የውስጥ ጉዳይ ሚኒ እንደተስማሙበት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ፋቢዮ ኮላግራንደ ገለጡ።

ወደ ኤውሮጳ በሕገ ወጥ ለመግባት በሜዲትራኒያን የባህር በር በኩሉ ጉዞ እያሉ የሞት አደጋ የሚያጋጥማቸው ብቻ የሚቀበሩበት የመካነ መቃብር ሥፍራ እንዲገነባ ሃሳቡን ያቀረቡት የሰብአዊ መብት ተንከባካቢ እንቅስቃሴ ሊቀ መንበር ፍራንኮ ኮርበሊ መሆናቸው የገለጡት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ኮላግራንደ አክለው የተገባ የመቃብር ሥፍራ የሰው ልጅ የተቀደሰና የተባረከ ሰብአዊ መብትና ክብር መሆኑ በካላብሪያ የኮሰንዛ ቢሲኛኖ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳልቫቶረ ኑናሪ የቀረበው ሃሳብና የተደረሰው ውሳኔ የሚመሰገን ተግባር ነው እንዳሉ አስታውቀዋል።

ብፁዕነታቸው ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፦ ሰላማችን በሰማያዊ ቤት ነው። በምድር የሚታየው ልዩነት የማይኖርበት ለሁሉም በእግዚአብሔር ምሕረት የተገባ ሥፍራ ነው። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተገደው የገዛ እራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው ብሩህ መጻኢ ለመገንባት ከአፍሪቃና ከተለያዩ አገሮች በሜዲትራኒያን የባህር በር በኩል የሚሰደዱት የሚያጋጥማቸው የሞት አደጋ አሁንም እየታየ ነው፣ በእውነቱ የመቃብሩ ሥፍራ መገንባቱ የተቀደሰ ተግባር ነው፣ ሆኖም በዚህ ብቻ ሳይቆም በእውነቱ የሚያጋጥመው የሞት አደጋ እንዳይኖር ለማረግ የሚያበቃ የሰው ልጅ ልክነት ያለው ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ሥርዓት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው። ለስደት የሚዳርገው ችግር መፍትሔ ማፈላለጉ ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ብለው ሆኖም እነዚህ በባህር ጉዞ የሞት አደጋ የሚያጋጥማቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልጆቻችን ለሁሉም የኅሊና ጥያቄ ናቸው፣ የመካነ መቃብር ሥፍራ ግንባታውም የእነርሱ ለሞት አደጋ መጋለጠ ለእኛ ትልቅ ሓዘን መሆኑ የሚመሰክር ተግባር፣ አለ ምንም የዘር የቋንቋ የባህል የሃይማኖት ልዩነት ሁላችን የአንድ አግዚአብሔር ልጆች መሆናችን የሚመሰክር ነው በማለት ያካሄዱት ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.