2015-10-30 19:11:00

የፅጌ 4 ኛ ሰንበት (01/11/2015)


« እነሱም ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ሌሎች
ገበሬዎች ይሰጣቸዋል» ማቴ፥21፥41


በዚህ የወንጌል ክፍል አንድ የወይን እርሻ ባለቤት ለወይኑ ተክል የሚያስፈልገውን ሁሉ ካመቻቸ በሁዋላ
ለገበሬዎች አከራይቶ ስለሄደ ሰው ይናገራል። ተከራዮቹ ገበሬዎች ግን በቃላቸው ታማኞች ሆነው
አልተገኙም። ለአከራያቸው ድርሻውን በመከልከል ብቻ አላቆሙም፥መልክተኞቹን ብቻ ሳይሆን ልጁን
ጭምር ገደሉበት ንብረቱን ለመውረስ ተመኝተው ነበርና። በዚህ ጊዜ የባለቤቱ ቁጣ ነደደች፥የነሱም
መጨረሻ ሞት ሆነ የወይኑ እርሻም ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡ ለሌሎች ተሰጠ። ከዚህ ምን
እንማራልን?
ለያንዳዳችን እግዚአብሔር አምላካችን ስጦታ ሲሰጥ፥አንድ አደራ በእጃችን ሲያኖር በመጨረሻ
ድርሻውን ይጠይቃል፤ፍሬውን ማየት ይፈልጋል። ክርስትናን ከተቀበልንበት ጊዜ ጀምሮ በምስጢራት እና
በተያዩ መንገዶች ፀጋንና በረከቶችን ከተቀደሱት የእግዚአብሔር እጆች ተቀብለናል። ታዲያ
እግዚአብሔር ፍሬውን ሲጠይቅ ምንድነው ምላሻችን? ከዓመታት የክርስትና ሕይወት በሁዋላስ
ለፈጣሪያችን ምንድን ነው የምናቀርብለት?
እግዚአብሔር አራጣ አበዳሪ አይደለም፥ያልሰጠውን አይጠይቅም፥ካቅማችን በላይም
አይጠብቅም፥በሰጠን መጠን ግን እንድናፈራ፥እንድናተርፍ ይፈልጋል።በተሰጠን ዕድል
የማንጠቀም፥የእግዚአብሔርን ትዕግስት የምንፈታተን፥የስራችንን ውጤት የምናቀርብበትን ወቅት
የማንጠብቅ የእግዚአብሔርን ቀጠሮ የማናከብር ከሆነ፥ ወይም ደግሞ በርሱ ላይ በአመፅ የምንነሳሳ ከሆነ
የመጨረሻ ዕጣችን እንደነዛ ውለታቢስ ገበሬዎች ይሆናል። እግዚአብሔር የሰው ድሃ አይደለምና ሌላ
አገልጋይ፥ሌላ ምዕመን ያስነሳል።የእሱ በረከት እና ማዳኑም ከተመረጠውና የመጀመሪያ ዕድል ከተሰጠው
ሰው ተወስዳ ለሌላ ትሰጣለች።
ስለዚህ በእጃችን ያለውን እና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የተቀበልነውን የእግዚአብሔር በረከት
እንይ። እሱ አሁንም መመለስ እና መንገዳቸውን ማስተካከል የሚፈልጉትን ሁሉ በትዕግስት ይጠብቃል።
ምድራዊ ጉዞአችንን ስናበቃና ቅን ፈራጅ በሆነው ፈጣሪ ፊት ስንቆም እንዳናፍር ዛሬ እግዚአብሔር
በሰጠን ፀጋ ለመኖርና መልካም ፍሬ ለማፍራት እንትጋ።በዚህ መልኩ የኖርን እንደሆነ እግዚአብሔር
ፍሬውን በጠየቀ ጊዜ ይዘን የምንቀርበው ነገር በእጃችን ይኖረናል ማለት ነው። እግዚአብሔር ለመዳናችን
የሚበጅ መንፈሳዊ ፍሬ የምናፈራበት ሐይል እና ማስትዋል የነፍስም ትዕግስት ይስጠን። አሜን!
ሠላም ወሰናይ
አባ ዳዊት ወቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.