2015-10-05 19:01:00

ሲኖዶስ እንደ ፓርላመንት ሳይሆን በጸሎትና በጽሞና ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት መሆን ነው! ር.ሊ.ጳ


 

ለአንድ ዓመት ያህል ብዙ ያናገረና የብዙ ውይይቶችና ጥያቄዎች ምክንያት ሆኖ እስከ ዋዜማው ድረስ ከቤተክርስትያን ውስጥም ይሁን ውጭ ደጋፊና ነቃፊ የበዛበት አሥራ አራተኛው መደበኛ የጳጳሳት ሲኖዶስ ትናንትና በቅዳሴ ተከፍቶ ዛሬ ጥዋት እንደ ሮም ሰዓት አቆጣጠር ልክ ዘጠኝ ሰዓት በጳውሎስ ስድስተኛ አደራሽ በሚገኘው የሲኖዶስ አዳራሽ ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስና ጠቅላላይ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች አበውና ሌሎች በተገኙበት ዛሬ ጸሎተ ሰዓታት ዘሰለስቱ በመድገም ተጀመረ፣

በሲኖዶሱ የሚሳተፉ በአኃዝ ሲመለከት 270 የሲኖዶስ አባቶች 45 ር.ሊ.ጳ ልዩ ጥሪ ያቀረቡላቸው ጳጳሳት ሲሆኑ በአህጉር ደረጃ ሲመለከት 54 ከአፍሪቃ 64 ከአሜሪካ ካናዳ ሰሜን አሜሪካና ደቡብ አሜርካ ለማለት ያህል 36 ከኤስያ 107 ከኤውሮጳ 9 ከኦሽያንያ በመዓርግ ደረጃ ሲመለከት ደግሞ 74 ካርዲናሎች 181 ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳትና ፓትርያርኮች 13 ገዳማውያን 2 ቆሞሶች እንዲሁም 18 የቤተሰብ ጥንዶች እንደ ታዛቢዎችና 24 የልዩ ጽሕፈት ቤት ተባባሪ ሊቃውንት ናቸው፣

ከኢትዮጵያ ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ ቀነኔ ከኤርትራ ደግሞ ብፁዕ ሊቀጳጳስ አቡነ መንግሥተአብ ተስፋማርያም በመሳተፍ ይገኛሉ።

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለሲኖዶስ አባቶች በሰጡት መምርያ “ሲኖዶስ ሲባል እንደ ፓርላመንት ሳይሆን በጸሎትና በጽሞና ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት ሆኖ መንፈስ ቅዱስ ያበራውንና የመራውን በማዳመጥ ሁኔታዎችን ከእግዚአብሔር ልብ ጋር የሚያስተሳስር እንጂ የግልግልና የመስማማት ጉዳይ አይደለም” ሲሉ የሲኖዶስ አበው በሓዋርያዊ አገልግሎት ብርታትና ወንጌላዊ ትሕትና እንዲሁም እምነት በተሞላበት ጸሎት መንፈስ ቅዱስ በልቦቻቸው እንዲሠራ እንዲፈቅዱለት አደራ ሲሉ መግብያ ቃል ሰጥተዋል፣

አያይዘውም ሲኖዶስ ስጥራ በአንድነትና በሲኖዶሳዊ መንፈስ አብረን ለመራመድ ይህንም የቤተክርስትያንና የቤተሰብ መልካም ነገርንና የነፍሳት ደህንነትን በልቦናችን በማስቀመጥ ነው፣ ሲሉ የሲኖዶስን መንፈስ አጠር ባለ መንገድ ከገለጡ በኋላ ባለፈው ዓመት እንዳሉትም አበው የልባቸውን በቅንነት እንዲናገሩ የሚሰማቸውን የሓዋርያዊ አገልግሎትና የእምነት ጉዳይ ያላቸውን እውቀትና ተመኵሮ እንዲገልጡ ብርታት እንዲኖራቸው አሳስበዋል፣

ስለ መዝገበ እምነትና የእምነት አንቀጾች በተናገሩት ወቅትም እነኚህ ነገሮች የቤተ መዘክር ጉዳዮች አይደሉም፤ መዝገበ እምነት ሕያው ምንጭ ነው፣ ሕይወት ያለው ነገርም እየታደሰና እያሳደሰ ይጓዛል፣ የዚህ መግለጫም በኅብረት እየተጓዘች ያለችው ቤተ ክርስትያን በዚህ ሲኖዶስ ያለነውን ሁኔታና ነገሮች በእምነት ዓይንና በእግዚአብሔር ልብ እንድታነብና ሕያው በሆነው መዝገበ እምነትዋ አማካኝነት ሁነኛ መልስ እንድታገኝ በጸሎትና በሱባኤ ከጴጥሮስና በጴጥሮስ ሆና በቅዱስ ሕዝብ መካከል ትጓዛለች፣

ሲኖዶስ ሲባል ተነጥሎ ብቻውን የሚጓዝ ሳይሆን በቤተክርስትያን ሕጽንና እኛ እረኞችና አገልጋዮቹ በሆነው በቅዱሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ነው እየተጓዘ ያለው፣ ሲኖዶስ ቤተ ክርስትያን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የምታጣጥምበት ልዩ ሥፍራና ጊዜ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ በሲኖዶስ በእግዚአብሔር ሊመሩ በሚፈልጉ ሰዎች አፍ ይናገራል፣ ይህም ለትናንሽ በሚገለጠው ለአዋቂዎችና ብልኆች ግን ከሚደበቅ እግዚአብሔር ነው የሚሆነው፣ ሕግንና ሰንበትን የፈጠረ እግዚአብሔር ሕግና ሰንበት ለሰው ልጅ እንጂ የተገላቢጦሽ አይደለም በማለት 99 ትቶ አንዲት የጠፋቸውን በግ ፍለጋ የሚሄድ ከእውቀታችንና ሓሳባችን በላይ የሆነው እግዚአብሔር ነው፣ ስለዚህ ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት በመሆን አለምንም ፍርሓት የእረኝነት ብርታትና ወንጌላዊ ትሕትና እንዲሁም የእምነት ጸሎት በመታጠቅ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ብርሃን በማጥፋት በግዝያዊና ትንሽ ብርሃን ለመተካት በሚሞክሩ የዓለም ፈተናዎች እንዳትታለሉ በመጠንቀቅ እንዲሁም ምንም እንኳ ብዙ ጥሩ ሓሳብ ቢኖራቸው እንደ አለት በደረቀው ልቦቻቸው ሰዎችን ከእግዚአብሔር ለሚያርቁም በማወቅ እውነቱን ለመናገር ቅንነት ይኑራችሁ፣ የክርስትና ሕይወት የትውስታዎች ቤተ መዘክር እንዳታደርጉት አደራ፣ የሓዋርያዊ አገልግሎት ብርታት የሚባለውም ይህ ነው፣ ወንጌላዊ ትሕትና ማለትም እኔነትንና በአንድ ሓሳብ መድረቅን ትቶ ወንድሞችን ማዳመጥና በእግዚአብሔር መሞላት የሚያስከትል ጣትን ሌሎችን ለመፍረድ ከመቀሰር ይልቅ እንድትረዳቸው እጅህን ለመዘርጋት የሚያስችል ትሕትና ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ሊመራን ካልተውነው ውሳኔዎቻችንና አዋጆቻችን ለመልክና ለእዩልኝ ስሙልኝ ሆነው ሊቀሩ ስለሚቻል እምነት የሞላበት ጸሎት ያስፈልጋል፣ እውነትም ልባችን ለእግዚአብሔር ከተከፈተና የእግዚአብሔርን አዳኝ ድምጽ በቃሉ ለመሳት ጸጥ ካልን ቃሎቻችን የማይረቡና የማያገለግሉ ከመሆን ይድናሉ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን ያልፈቅድነው እንደሆነ ውሳኔዋቻችን ወንጌልን ከፍ ከማድረግና ከመስበክ ይልቅ ይደብቁታል፣ በማለት ከእያንዳንዱ አባት ምን እንደሚጠበቅ የልባቸውን ከተናገሩ በኋላ ይህ ሲኖዶስ እውን ለመሆን ላበረከቱት ሁሉ አመስግነው በቦታው ለነበሩ ጋዘጠኞችንም በጥልቅ ስሜት ሲኖዶሱን በመከታተላቸው አመስግነው ያ ደጋግመው ያሉትን ቃል “ሲኖዶስ ሲባል እንደ ፓርላመንት ሳይሆን በጸሎትና በጽሞና ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት ሆኖ መንፈስ ቅዱስ ያበራውንና የመራውን በማዳመጥ ሁኔታዎችን ከእግዚአብሔር ልብ ጋር የሚያስተሳስር እንጂ የግልግልና የመስማማት ጉዳይ አይደለም” በማለት እንደገና ለመጨርሻ አደራ በማለት መግብያውን ደምድመዋል፣  

ቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳናቸውን ከፈጸሙ በኋላ የጉባኤው ጠቅላይ አፈ ጉባኤ ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል ፐተር ኤርዶ የሲኖዶሱ ሥራ በሶስት ነጥቦች ማለትም የቤተሰብ ተግዳሮች ጥሪ እና ተልእኮ ላይ ማትኮሩንና ሰነዱ እንደሚያመለክተው በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ ቤተሰቦችን ብምሕረት ዓይን ተመልክቶ መሸኘት ነገር ግን በእውነት መሆን አለበት፣ ስለሆነም ድኃ ቤተሰቦችን መደገፍ ሕይወትን ከጽንስ እስከ ባህርያዊ ሞት መከላከል ነው፣ ሲሉ ከሲኖዶስ የሚጠበቀውን ገልጠዋል፣

አያይዘውም የቤተሰብ ተግዳሮች በሚለው ነጥብ ስደት ማኅበራዊ የፍትሕ መጕደል የአንዳንድ ሥራ ሰጪዎች እጅ ያለበት እጅግ ዝቅ ያለ ደሞዝ ሥራ ለማግኘት ከቤተሰብ ተለይቶ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ የመውለድ መቀነስ በሴት ልጆች የሚደርሰው ዓመጽ ጽንስ ለማስወረድ መገደድ አስገድዶ ማምከን የማኅጸን ማከራየት ወዘተ ናቸው፣ ዋስትና ለመስጠትና ለመከላከል የቆሙ ተቅዋሞች ደካማ ከመሆናቸውም በላይ ወንዶች ወሳኝ ኃላፊነት የመውሰት ፍራቻ አላቸው፤ የባሰውኑ በግዝያዊ ነገሮችና ግላዊ ፍላጎቶች ላይ ብቻ በማትኰር እነኚህን ነገሮች እንደ እውነትና የግል መብቶቻቸው ሆኖ ይሰማቸዋል፣ ዋነኛው ችግር ግላዊነት የሚለው የዘመናችን ፍልስፍና ሲሆን ይህ ደግሞ የትዳርና የቤተሰብን ድንበሮችን ይደባላቃል፣ ቃል ኪዳን የማይፈታ ነው ሲባል ጫና ሳይሆን ስጦታ ነው፣ ግለሰቦችን ብቻቸው የማይተው ቤተሰቦችና ባለትዳሮች ናቸው፣ ዕሴቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ለእያንዳንዱ መተኪያ የሌለው ሰብ አዊ ብልጽግና ያወርሳሉ፣ ይህም ዋስትና ሊያገኝ የሚችለው ቃል ኪዳን የማይፈታ ነው ከሚለው ጥሪ ያገኛል፣ ሲሉ ወደ ሁለተኛ ክፍል ማለትም የቤተሰብ ጥሪ ወደ ሚለው ነጥብ በመሻገር ቤተሰብ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና ምስል መፈጠሩና ለአንድነትና ለትውልድ ሴት ልጅና ወንድ ልጅ አድርጎ በመፍጠራቸው ቃልኪዳን አንድ ሥጋ የሚያደርግ የማይፈታ ነው ሲባል ስጦታ እንጂ ጫና አይደለም፣ ቤተሰብ የሕይወትና የማኅበረሰብ መጀመርያ ነው፣ በዚህም የጋራ በጎ ነገር ምን መሆኑ እንማራለን፣ በሁለት ክርስትያኖች የቃልኪዳን ምሥጢር የቆመች ቤተሰብ የቤት ቤተክርስትያን ወይንም ትንሽ ቤተ ክርስትያን በመሆን የማኅበረሰብ ሕይወት መጀመርያ በመሆን የጋር በጎ ነገርን ለማጣጣም ትምህርት የምናገኝበት ቦታ ነው ሲል ሰነዱ ቤተሰብን ይገልጣል፣ በማለት የቤተሰብ ጥሪን ባጭሩ ከገለጡ በኋላ የእረኝነት አስፈላጊነት የግድ መሆኑን በመገንዘብ ለዚሁ ሓዋርያዊ አገልግሎ ብቁ ሆነው እንዲገኙ ቤተሰቦችን የሚሸኙ ካህናት መኰትኰት አስፈላጊነት ወደሚመለከተው ወደ ሶስተኛ ነጥብ ተሸጋግረዋል፣

ይህ አገልግሎት የቤተሰብ ተል እኮን የሚመለከት ስለሆነ አዳዲስ ሙሽሮችም ይሁኑ እነርሱን የሚሸኙ ካህናት ልዩ ሥልጠናና ዝግጅት እንደሚያስፈልጋቸው ብሩህ ነው፣ በተለይ ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ለቤተሰብ ሓዋርያዊ አገልግሎት የሚመደበው ካህን ሰብአዊና ሥነ አእምሮአዊ ብስለት ያስፈልገዋል እንዲሁም አግልግሎቱ ትርጉም እንዲኖረው በተለይ አስቸጋሪና ከባድ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙትን ቤተሰቦች በምሕረትና በፍትሕ ለመርዳትና ለመወያየትም  በክርስቶስ ቃል ላይ በተመረኮዘ ጥልቅ የአገላለጥ የትምህርተ ክርስቶስም የቋንቋ ችሎታም ያስፈልጋል። ይህ ለካህናትም ይሁን ለጳጳሳት እንዲሁም ለማንኛውም ሐዋሪያዊ ተልዕኮ አገልጋይ አዲስ ተመኩሮ ነው።

ቤተሰብን በማኅበረሰብ ውስጥ ማስቀደም።

 በማኅበረ ሰብ ውስጥ የቤተሰብ ተልዕኮ በመጀመሪያ ደረጃ ከመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር  መስራት ሲሆን ይህም በተለይ የቤተሰብ ትርጉሙ ከተፈጥሮአዊና ከክርስቲያናዊ አመለካከት እንዳይርቅ ነው ሲሉ ካርዲናል ኤርዶን ገልጠዋል። ቤተክርስቲያንና ክርስቲያኖች በተለያዩ የኤኮኖሚ ችግር ጦርነት ስደትና ስቃይ ለሚገኙና ለደረሰባችው ክርስቲያን ወገኖች መርዳት አስፋላጊነትና ለመርዳትም የሚቻልበት መንገድ ማዘጋጀት አስፋላጊነቱን ገልጠዋል።

ሌላው አንገብጋቢና በቋፍ የሚገኘው የቤተሰብ ሁኔታ የተለያዩ ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦችን እውነተኛ ምህረትና አቀባበል ያስፈልጋል። ትክክለኛውና እውነተኛውን ትዳር መግለጥና ማስተማርም አስፈላጊ ነው። እውነተኛ ምህረት ማለት ይቅር በመባባል ለለውጥና ለአንድነት የሚያደርስ እውነተኛ ፍቅር ነው።

ካርዲናል ኤርዶ በማያያዝ፡ ያለ ቃል ኪዳን አብሮ የሚኖሩትን ልዩ ትምህርት በእግዚብሔር ዕቅድና ሃሳብ ቃል መኮትኮት አስፈላጊነቱን በማተኮር ከቃል ኪዳናቸው ለተለያዩና በትዳራቸውም ችግር ላለባቸው በሚኖሩበት ቁምስናዎች ልዩ ማዕከል በመክፈት ለደረሰባቸውና ለገጠማቸው ፈተናዎች በማዳመጥ በሃሳብ የሚረዳቸውን ማዘጋጀት ጠቀሜታ አመልክተዋል።፡ምህረት ይቅር ባይነት የሐጢአተኛ ልብ መቀየር ሲጠይቅ በተለይም ቤተሰቦች በሚያደርጉት ለሰላምና የጥምረት ጉዞ ልዩ ትኩረት መሰጠት ያለበት ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ችግር ጫና ነፃ መሆን ነው። ቃል ኪዳናቸውን በማፍረስ ሌላ ትዳር ለመሰረቱ ቢቻል ጥልቅና መሰረታዊ በሆነው ቃል ኪዳን ላይ ማሰላሰሉ አስፈላጊነቱን መዘንጋት እንደሌለበት ነው።

የሓዋርያዊ አገልግሎት ኩትኮታና ምህረት አስፈላጊ ቢሆኑም ክርስቶስ ካስተማረን እውነተኛ ቃል ኪዳን ማፍረስ አይቻልም። የእግዚአብሔር ምሕረት ሐጢዓታችንን ይቅር ቢልም የልባችንን መቀየር ይፈልጋል። ሲሉ ስለሶስቱም የሰነዱ ዋና ዋና ነጥቦች ከተናገሩ በኋላ ሲኖዶሱ እንዴት እንደሚካሄድ ባጠቃላይ እያንዳንዱ የሲኖዶስ አባት የሶስት ደቂቃ የመናገር ዕድል እንዳለው ከዛም በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍለው ከተወያዩና ከተነጋገሩ በኋላ ሁሉ ተሰብስቦ በአጠቃላይ ጉባኤ ይወያዩበታል፣ በመጨረሻም የሲኖዶሱ መርሓ ግብር እንደሚያመለክተው ለእያንዳንዱ አንቀጽ ድምጽ ተሰጥቶበት እንደ ምክር ለቅዱስነታቸው እንደሚቀርብ በሰፊው በመዘርዘር ገልጠዋል፣

ብፁዕነታቸው አጠቃላይ የሲኖዶሱ አካሄድ ከገለጡ በኋላ ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል ቫጝትርዋ የዕለቱ የጉባኤው መሪ በመሆን መንበሩን ተረክበው ሲኖዶስ የኃይል ማሳያ ሜዳ ሳይሆን የውህደት ጉዞ መሆኑን በመግለጥ ቃል ኪዳን የማይፈታ ጽኑ መተሳሰርያ ነው የሚለው አንቀጸ እምነት በምንም ምክንያት እንደማይነካ ነገር ግን ምእመናንን እንዴት አድርጎ ለንስሓና ለምሕረት እንዲቀርቡ መርዳት እንዳለብን እንሥራ፣ በማለት መደበኛውን ጉባኤ ከከፈቱ በኋላ የሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ብፁዕ እምብፁ ዓን ካርዲናል ለረንዞ ባልዲሰሪ ደግሞ ሲኖዶሱ ቤተሰቦችን በርኅራኄና በምሕረት ዓይን እንዲመለከት እማጠናለሁ ሲሉ አደራ ካሉ በኋላ የአበው ዝግ ውይይት ተጀምረዋል፣

የጥዋቱ ክፍለ ግዜ ከተፈጸመ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዲሰጡ የሲኖዶሱ የመገናኛ ብዙኃን ኮሚቴ የዕለቱ የጉባኤው ፕረሲደንት ከነበሩ ካርዲናል አንድረ ቫጝትርዋ ጠቅላይ አፈጉባኤ ካርዲናል ፐተር አርዶ የሲኖዶሱ ዋና ጸሓፊ አቡነ ፎርተ የሲኖዶስ ልዩ ጸሓፊ አባ ሎምባርዲ በኅብረት ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፣

 








All the contents on this site are copyrighted ©.