2015-08-03 19:15:00

የር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸስኮስ ትናንትና እሁድ እኩለ ቀን ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙ ምእመናን ጋር የመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱ ቃለ ወንጌል ተመርኵዘው ይህንን አስተምህሮ አቅርበዋል፣ "ውድ ውንድሞችና እኅቶች! እንደምን አደራችሁ!

በዛሬው እሁድ ቃለ ወንጌል የዮሓንስ ወንጌል ስድስተኛ ምዕራፍ ተከታታይ ክፍል ሲሆን ጌታ ኢየሱስ በጥቂት እንጀራና ዓሣ ብዙ ሕዝብ ከመገበ በኋላ ሕዝቡ ኢየሱስን ሲፈልግና ሲከታተለው ኖሮ በመጨረሻ በቅርፍርናሆም እንዳገኙት ሲገልጥ ጌታ ግን ሕዝቡ ሊያገኘው እንዲህ የጓጓበትን ምክንያት ጥርት ባለ መንገድ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።” (ዮሐ 6፡26) ሲል ይገልጥላቸዋል፣ እውነትም ሕዝቡ የተከተለው ከጥቂት ቀናት በፊት ረኃባቸውን ስለቆጨላቸው እንጂ የዚያኛው እንጀራ ትርጉም ስለተረዳቸው አልነበረም፣ ያ ኢየሱስ ከሐዋርያት ተቀብሎ ባርኮና ቈርሶ የሰጣቸው የምን ምልክት መሆኑን አልተገነዘቡትም፣ ይህ ለብዙ ሰዎች ተቈርሶ የቀረበው እንጀራ የኢየሱስ የፍቅር ምልክት መሆኑን ጌታ ራሱ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ገና አልተረዱትም፣ እንጀራውን ከሰጣቸው ይልቅ በግዝያዊ እርካታ ተሸንፈው ቀልባቸው በግዝያዊ እንጀራ ብቻ አኖሩ፣ በዚሁ መንፈሳዊ መታወር ለሚገኘው ሕዝብ ነው ኢየሱስ ከሥጋዊ እንጀራ ወደ መንፈሳዊው እንጀራና ምንጩ ወደሆነው እንዲያተኵሩ የሚማጸናቸው፣ ስጦታውም ይሁን የስጦታው ምንጭ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑንም ይገልጥላቸዋል፣ ዓይነ ልቦናቸውን እንዲከፍቱና ስለዕለታዊ እንጀራ ብቻ ከመቸገር ይልቅ የማያልፈውንና ዘለዓለማዊ ስለሆነው እንጀራ እንዲያስቡ እንጂ ምን እንመገባለን ምንስ እንለብሳለን እንዴትስ ስኬታም ኑሮ እንኖራለን ብለው እንዳይቸገሩ ያሳስባቸዋል፣ በሚቀጥለው ቍጥርም “ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” (ዮሐ 6፤27) ሲል ስለደህንነታቸው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበትን መንገድ እንዲፈልጉ ይነግራቸዋል፣

በእነዚህ ቃላት የሰው ልጅ ከሥጋዊ ረሃብ ባሻገር መንፈሳዊ ረኃብም እንዳለው ይገልጣል፣ እኛ ሁላችን ይህ መንፈሳዊ ረሃብ አለን፣ ይህ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ረሃብ በማንኛው ምግብ ሊረካ አይችልም፣ ይህ ረሃብ የሕይወት ረሃብ የዘለዋለማዊነት ረሃብ ሆኖ ሊያረካው የሚችል እርሱ ብቻ ነው፣ ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ገዛ ራሱን “የሕይወት እንጀራ” (ዮሐ 6፡35) በማለት የሚገልጠው፣ ጌታ ኢየሱስ ስለዕለታዊ እንጀራ መጨነቅን አያስወግድም ነገር ግን ሰው በዚህ ብቻ እንዳማኖርና በዚህ ምድር የሕወታችን ጉዞ ዓላማ ዘለዓለማዊው ሕይወት እንደሆነ ይህም ስጦታውና ሰጪ ከሆነው ከጊታ ጋር በመገናኘት እንደሚፈጸም በመረዳት የሰው ልጆች ታሪክ በደስታም ይሁን በሓዘን በዚሁ አመለካከት ማለት ዘለዓለማዊ ሕይወት ላይ በማትኮር ጌታን ለማግኘት በመጣር መሆን አለበት፣ ጌታን ያገኝን እንደሆነ ደግሞ የሕይወት ዘመናችን ሁሉ ይበራል፣ ስለዚሁ ግኑኝነት ያሰላሰልን እንደሆነ ትናንሽ የሕይወት ስጦታዎችስ ይሁኑ መቸገርና መሰቃየት በዚሁ ተስፋ ሊበሩ ይችላሉ፣ ጌታ ኢየሱስ “ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።”(ዮሐ 6፡35) ሲል ያ ነፍስንና ሥጋን የሚያረካ ታላቁ ስጦታ የሆነው ቅዱስ ቍርባንን ያመልክታል፣ ይህንን የሕይወት እንጀራ የሆነውን ኢየሱስ ስንቀበለውና ስንገናኘው ሁሌ ከባድ ለሆነው ለሕይወታችን ጉዞ ትርጉም ሰጥሮ የማያልቅ ተስፋ ይሆንልናል፣ ነገር ግን ይህ የሕይወት እንጀራ የተሰጠን አለምንም ዕዳ አይደለም በልተን በጠገብንበት ጊዜ የወንድሞቻችንና የእኅቶቻችን መንፈሳዊና ሥጋዊ ረሃብ ለማርካት ማለት ወንጌልን ለሁሉም መስበክ እንዳለብን ነው፣ በሕይወታችን ኑሮ ወንድሞቻችን ያፈቀርንና ሁሉንም ለመርዳት ዝግጁ በመሆን ምስክርነታችን መስጠት እንዳለብን ሲሆን እንዲህ በማድረግ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስንና ፍቅሩን ለሁሉም እናሳያለን ማለት ነው፣

እመቤታችን ድንግል ማርያም እውነተኛውና ሕያው የሆነው ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያገልግል እንጀራ የሆነውን ልጅዋ ኢየሱስን ለመፈልግና አግኝቶት ለመከተል ትርዳን፣ ሲሉ ካስተማሩ በኋላ የመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት ከሕዝቡ ጋር አሳርገዋል፣

ከጸሎቱ በኋላ ለሁሉም ሰላምታ ካቀረቡ በተለይ ደግሞ ከእስፐይን የመጡ ወጣቶችንና ከተለያዩ የጣልያን ከተማዎች ለመጡ ነጋድያን ልዩ ሰላምታ አቅርበዋል፣ አያይዘውም በዕለቱ ለተዘከረው በአሲዙ ምሕረት የሚታወቀው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ስለመለኮታዊ ምሕረት ያቀረበው መንፈሳዊ ተግባር አመልክተው እንዲህ ብለዋል፣

“ዛሬ የአሲዚው ምሕረትን እንዘክራለን፣ በመለኮታዊ ምሕረት የሚያስገኝ ምሥጢረ ንስሓና በቅዱስ ቍርባን ወደ ጌታ ለመቅረብ የሚቀርብልን ኃያል ጥሪ ነው፣ ወደ ምሥጢረ ንስሓ ለመቅረብ የሚፈሩ ሰዎች አሉ፤ በመንበረ ኑዛዜ የሚያገኙት ጨካኝ ዳኛ ሳይሆን ወደር የሌለው ምሕረት የሚያቀርብልን አባት መሆኑን የዘነጉ ይመስለኛል፣ እውነት ነው ወደ መንበረ ኑዛዜ ስንሄድ ትንሽ ኃፍረት ይሰማናል፣ ይህ ለሁላችን የሚያጋጥም ነው ነገር ግን ይህ የኃፍረት ስሜት ራሱ ጸጋ ሆነ ሁሉንም ሁሌ በሚምር መለኮታዊ አባታችን እቅፍ ለመቅረብ የሚረዳን መሆኑንም መዘንጋት የለብንም ሲሉ ካሳሰቡ በኋላ መልካም እሁድና ምሳ በመመኘትና በጸሎት እንዲያስብዋቸው አደራ በማለት ተሰናብተዋቸዋል፣ 








All the contents on this site are copyrighted ©.