2015-04-27 19:48:00

እረኞች፤ አደራ ለተሰጣችሁ መንጋ አገልጋዮች እንጂ አስተዳዳሪዎች አይሁኑ፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ዘወትር እኁድ እኩለ ቀን ላይ እንደሚያደጉት ትናንትና እሁድም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናንና ነጋድያን ጋር የንግሥተ ሰማያት ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱ ቃለ ወንጌል መሠረት በማድረግ እውነተኛ እረኛ ኢየሱስ ሲሆን ዱኳውን በመከተል የእረኝነት አደራ የተሰጣቸው ጳጳሳትና ካህናትም ምሳሌውን በመከተል አገልጋዮች እንጂ እንደ አስተዳዳሪዎች የጌትነት ባህርይ ማሳየት እንደሌለባቸው አሳስበዋል፣

በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ትናንትና አራተኛ የትንሣኤ እሁድ ሲሆን ለዕለቱ የቀረበው ቃለ ወንጌል ከዮሐንስ ወንጌል የተወሰድ ስለ መልካሙ እረኛ የሚናገር ነበር፣

ቅዱስነታቸውም ጌታ ኢየሱስ ለምን መልካም እረኛ ተባለ ሲሉ ይጠይቁና ጥያቄው በየዓመቱ በዚሁ እሁድ ተደጋግሞ የሚጠየቅ ሲሆን ይህም የሚሆንበት ምክንያት ሁሌ በአዲስ መንፈስ የዚህ ትርጉም ለማግኘት ነው፣ ሕይወቱን ለመንጋው አሳልፎ የመስጠቱ ምሥጢር ስለ ሕማማቱ ስለ ሞቱ እና ስለ ትንሣኤው ሲሆን የመልካም እረኛ ትርጉምም በዚህ ፍጻሜ ይገለጣል፣ ሕይወቱን ለእኛ ሁላችን ሲል አሳልፎ ሰጠ፤ ለእኔ ላንተ ላንቺ ለሁላችን! መልካም እረኛ ማለት ደግሞ ይህ ነው፣ ክርስቶስ እውነተኛ መልካም እረኛ ነው፣ በውሸት እረኞች አንጻር ሲመለከት ኢየሱስ ለሕዝቡ ብቸኛው አንድያ እረኛ ነው፣ መልካም እረኛ ያልሆነው መጥፎው እረኛ ለገዛ ራሱ ብቻ ያስባል፣ በጎቹን ይጨቁናል ለጥቅሙ ሲልም ለማትረፍ ይሞክራል፣ እውነተኛ መልካም እረኛ ግን ገዛ ራሱን ቤዛ አሳልፎ ይሰጣል፣ የገዛ ራሱ ጥቅም ሳይፈልግ መንጋውን ለማሰማራት ለመምራት ለመመገብ ለመከላከል ይታገላል፣ ከሁሉ የላቀ ዋጋ ግን ገዛ ራሱን መሥዋዕት የማድረግ ነው፣ ይህንን ማስተንተን ማለት እግዚአብሔር እረኛችን መሆኑን በመገንዘብ ለእያንዳንዳችን አሳቢ አባት በመሆን እንደሚያስብልን ነው፣ በዚሁ የእግዚአብሔር ፍቅር እኛ ሁላችን ታላቅ ደስታ እናጣጥማለን በነጻ የተቀበልነው ይህ ጸጋን ደግሞ ከሌሎች ጋር ለመካፈል ልባችንና አንጎላችንን እንከፍታለን፣ ይህንን ማስተንትንና ስለዚህ ማመስገን ያስፈልጋል፣ ሲሉ ካሳሰቡ በኋላ በዕለቱ መዓርገ ክህነት ወደ ሰጥዋቸው አዳዲስ ካህናት ዞር በማለት “ነገር ግን ይህንን ማስተንተንና ማመስገን ብቻ በቂ አይደለም፤ መልካሙ እረኛ መከተል ያስፈልጋል፣ በተለይ ጳጳሳትና ካህናት ር.ሊ.ጳጳሳትም ሳይቀር ይህንን የመልካም እረኛ አደራ የተቀበሉ ስለሆኑ ልክ ጌታ ኢየሱስ እንዳደረገው መንጋውን ማገልግለ እንጂ የበላይነት ማሳየት የለባቸውም፣ ጌታ ኢየሱስ አምላክ ሳለ ሁሉን ትቶ ትሕትና ተላብሶ እስከ መስቀል ሞት በመታዘዝ ደህንነትና ምሕረት ያስገኘልን ምሳሌውን እንድንከተል ነው የጠራን” ሲሉ አደራ ብለዋል፣

ለዚህ ሁሉ እመቤታችን እንድትረዳን በመማጠን የንግሥተ ሰማያት ጸሎት አሳርገዋል፣

በትናንትናው ዕለት በካናዳ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ዘሮዛርዩም ደናግል ማኅበር መሥራች የሆነ እናት ማርያ ኤሊሳ ቱርጎን ሥርዓተ ብፅዕና የተካሄደ ሲሆን ቅዱስነታቸውም ይህንን በማስታወስ ብፅዕት ማርያ ኤሊዛ በመንፈሳውነትዋ አብነት የሆነች ለጸሎትና ትናንሾችን ለማስተማር በተለያዩ የሃገረ ስብከትዋ ማእከሎች የሠራችና ብዙ ምግባረ ሠናይ ያበረከተች እንደነበርች በመግለጥ ሐዋርያዊ ቡራኬ በመቸርና መልካም ምሳ በመመኘት ሕዝቡን ሲያሰናብቱ ዘወትር እንደሚያደርጉትም ሕዝቡ በጸሎት እንዲያስባቸው አደራ ብለዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.