2015-03-16 19:15:00

የእግዚአብሔር ፍቅር በነጻ የሚሰጠንና ወደር የለሽ ነው፣


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍርናቸኮስ ትናንትና እኩለ ቀን ላይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ስለ የእግዚአብሔር ፍቅር በዮሐንስ ወንጌል “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና።“ (3፤16) የሚለውን ቃል በመመርኰዝ እግዚአብሔር በእውነት እንደሚያፈቅረን ገልጠዋል፣

የእግዚአብሔር ፍቅር ታላቅነት ለማስተንተን እላይ የተጠቀሰውን ቃለ ወንጌል ስንሰማና ስናስተነትን የተሰቀውለውን ኢየሱስ የተመለከትን እንደሆነ ምንኛ ያህል እንደወደደን በልባችን ይሰማናል፣ ይህ ታላቅ ፍቅር በነጻ የተሰጠንና ወደር የለሽ መሆኑን መርሳት የለብንም፣ እንዲሁም እግዚአብሔር በምሕረትና ይቅር ባይነት ሃብታም መሆኑን መዘንጋት የለብንም ብለዋል፣

አያይዘውም እግዚብሔር ሕዝቡን የሚመርጠው የሚገባው ሆኖ በታታሪነቱ ሳይሆን በፍቅሩ መሆኑን ሲገልጹ የሰው ልጅን ከመፍጥሩ ጀምሩ መላው የድህንነት ታሪኩን የተመለከትን እንደሆነ ታናሹን የእስራኤል ሕዝብ በመረጠበት ጊዜ “ከሁሉም ሕዝብ ያነስክ በመሆንህ ነው የመረጥኩህ” በማለት ፍቅሩንና ርኅራኄውን ሲገልጥ ጊዜ በደረሰ ጊዜ ደግሞ ምንም እንኳ የሰው ልጆች ኪዳኑን ደጋግመው ቢያፈርሱት አንድያ ልጅን ከሴት እንዲወለድ በማድረግ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለአንዴና ለመጨረሻ አዲስ ኪዳን ተከለ፣ ይህ ኪዳን በንጹሕ ልጁ ደም የተደረገ ስለሆነ ማንም ሊበግረው አይችልም፣ ይህን የአባት ፍቅር እስከ መጨረሻ ያሳየን ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ነው፣ ይህንንም በመስቀል ስለ እኛ በመሞት ገለጠው፣

በወንጌለ ዮሓንስ “የእርሱ የሆኑትን እስከ መጨረሻ አፈቀራቸው” (13፤1) የሚለው ሓረግ የዚሁ ወደር የለሽ ፍቅር መግለጫ ሲሆን ይህም በዚህ ምድር በሥጋው ሕይወቱ እስካለ ለማለት ሳይሆን በሰማያዊና መለኮታዊ ባህርዩ ስንመለከተው ማለት ሲሆን ለዘለዓለም አለምንም ገደብ መሆኑን ለመግለጥ ነው፣ እግዚአብሔር አብ ሲፈጥረን የሕይወት ጸጋ በመስጠት የፍቅሩን ታላቅነት ሲያሳየን በአንድያ ልጁ ሕማማት ሞትና ትንሣኤ ደግሞ ለእኛ ሲል ምንኛ ያህል እንደተሳቀየና ስለ እኛ መሞቱ ምንኛ ያህል እንደሚያፈቅረንና ምንኛ ያህል መሃሪና ርኅሩኅ መሆኑን ያመልክታል ሲሉ ካስተማሩ በኋላ እመቤታችን ድንግል ማርያም የዚህ ፍቅር እርግጠኛነት በልባችን ውስጥ እንድታኖርልን በመመኘት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገው ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.