2015-02-09 18:05:05

ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር የኅብረተሰባችን አሳፋሪ ሰለባ ነው፣


RealAudioMP3 ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና እኩለ ቀን ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመመርኰዝ እንዲሁም በዕለቱ የተስታወሰው ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወርን ለመቋወም የጸሎትና የአስተንትኖ ቀን ምክንያት በማድረግ “ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር የኅብረተሰባችን አሳፋሪ ሰለባ ነው፣” ሲሉ በዘመናችን እየታየ ያለውን የሰው ልጅ እንደ ዕቃ ሲሸጥና ሲለወጥ እንዲሁም እንደየማኪና ዕቃ መለዋወጫ የሰው ልጅ አካላት ሲሸጥና ሲለወጥ መስማት እጅግ የሚቀፍና የሚያስፍር መሆኑን ገልጠዋል፣
በላቲኑ ሥር ዓተ አምልኮ ግጻዌ መሠረት ትናንትና እሁድ የተነበበው ወንጌል የቅዱስ ማርቆስ 1፡29-39 ሲሆን ኢየሱስ በቅርናናሆም በቤተመቅደስ ማስተማሩ እንዲሁም ብዙ ሕመምተኞችን እንደፈወሰና በገሊላም እንዳስተማረ የሚገልጥ ነበር፣ የፈወሳቸውም ሰዎች በትኵሳት ትሰቃይ ከነበረችው የጴጥሮስ ዐማት እስከ በብርቱ አጋንንት ተይዘው ለዘመናት ይሰቃዩ የነበሩና በኢየሱስ ነጻ የወጡ ነበር፣
ቅዱስነታቸውም የሕመም ጉዳይና የሚያስከትለው ስቃይ ዛሬም ቢሆን ብዙ የሳይንስ ጥናትና ምርምር ቢደረግም ገና በሰው ልጅ ላይ ብርቱ ሥቃይ የሚያስከትሉ ሕመሞች ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ አስተምረዋል፣
በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መለስ ብለውም እያንዳንዳችን የዚሁ ኢሰብአዊ ተግባር ሰለባ በመሆን መብታቸውን አጥተው በታላቅ ውርደት ለሚገኙ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ድምጽ የመሆን ግዴታ እንዳለን በመግለጥ በዘመናችን ይህንን ለማድረግና በዚሁ ችግር ለሚሰቃዩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ለመርዳት የሚሰሩ በተለይ ደግሞ በባርነት ለሚሸጡና ለሚለወጡ ለሚጨዎኑ ሴቶች ሕጻናት ለሚረዱትም አመስግነው በብርታት እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፣ ይህንን ግፍ ለመዋጋት በሥልጣን የሚገኙ መርዎችና መንግሥታት ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ በፍትሕና በእውነት ይህንን ሰለባ ከኅብረሰባችን እንዲያስወግዱ አደራ ብለዋል፣
በላቲኑ ግጻዌ ከነገ ወዲያ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ዘሉርድ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሚዘከርበት እ.አ.አ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓም ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ስለሆነ ስለሁሉም ሕመምተኞች መጸለይ እንዳለብን በማሳሰብ ነገ ማክሰኞ ማታ በሮም ለዚሁ ዓላማ ተብሎ ተዘጋጅቶ ባለው የጸሎት ዝግጅት እንዲሳተፉም ገለጠዋል፣ በቅድስት መንበር የጤና ጥበቃ ሠራተኞች ሓዋርያዊ ግብረ ተልእኮ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ኃላፊ የሆኑ ብፁዕ አቡነ ዚግሙንት ዚሞውስኪ በጽኑ ታመው ወደ ትውልድ አገራቸው ፖላንድ ተመልሰው ስለሚገኙ እንድንጸልይ አደራ ብለዋል፣
በዕለቱ ቃለ ወንጌል ኢየሱስ ከፈወሳቸው ብዙ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሥጋዊ ሌሎቹ ሥነአእምሮ አዊ ሌሎች ደግሞ መንፈሳዊ ሕመም እንደነበራቸው ይህንንም በመንገድ ሲሄድና ሲያስተምር ያደርገው እንደነበረ ከገለጡ በኋላ ይህ ፍጻሜ ለአንዴ ለመጨረሻ በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን ዛሬም በየዕለቱ በተለያየ መልኩ እየተፈጸመ ነው፣ በየጎዳናው ሕመምተኞችን እየተቀበለና እየተንከባከበ ነው፣ አንድ የታመመ ሰውን ተቀብሎ ማገልግል ክርስቶስን ማገልገል ነውና፣ ስለዚህ በቃለ ወንጌል ብርሃን የተሰቀለው ክርስቶስን እየተመለከተ ለሚሰቃዩት ማጽናንትና ሕይወታቸውን ማብራት የእያንዳንዱ ክርስትያን ተልእኮ ነው ሲሉ በበሽታም ይሁን በሌላ ምክንያት ለሚሰቃዩት ሁሉ ትኵረታቸውን በተሰቀለው ክርስቶስ ላይ በማኖር በቃለ ወንጌል እንድናበራላቸው አደራ ብለዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.