Home Archivio
2015-01-23 18:51:28
ዘጥምቀት/ዘመነ አስተርዕዮ
ዛሬ የምናነበው ወንጌል (ዮሐ 2፡1-14) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ሰዎቹ ወይን ባለቀባቸው ጊዜ በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ውሃውን ወደ መልካም የወይን ጠጅ በመለወጥ ስላደረገው የመጀመሪያ ተዓምርና ራሱን ለዓለም እንደገለጠ እንዲሁም ሐዋርያቱ እንዴት በእርሱ እንዳመኑ ይናገራል፣፡ ይህ ወንጌል የሚያስተላልፍልንን ትምህርት በአጭሩ እንመለከተዋለን፣፡
በመጀመሪያ የምናገኘው ቃል “ግብዣ” የሚለውን ነው፤ ኢየሱስ፣ቅድስት ድንግል ማርያምና ሐዋርያቱ ወደ ሠርጉ ተጋብዘው ነበር (ዮሐ 2፡1-2)፤ ኢየሱስ በዚያ በመሮሩም በጊዜው ለደረሰው ችግር መፈትሔ ተገኘ፡፡ በሕይወታችን ለውጥ፣መንፈሳዊ ፍሬና ዕድገት ማየት ከፈለግን ከሁሉ በማስቀደም ኢየሱስን ወደ ነፍሳችን ማስገባት፣እሱን በልባችን ላይ መሾም ያስፈልጋል፡፡ ክርስቶስ በተገኘበት እና ከርሱ ጋር በተራመድንባቸው ጊዜያት በፍጹም አፍረን አናውቅም፤በእርግጥ በእምነታችን ምክንያት እንፈተን ይሆናል፣ተግዳሮትም አይጠፋም፣ነገር ግን ወድቀን አንቀርም ምክንያቱም እርሱን ስለያዝን፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ልመና” ማቅረብ ያስፈልጋል (ዮሐ 2፡3-4)፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ሆነን በእርሷ አማላጅነት ወደ አምላካችን የልባችንን መሻት ማቅረብ፣ለተቀበልነውም በረከትና ጸጋ ፈጣሪን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ክርስቲያናዊ የሆነ ትዕግስት ያስፈልጋል፤ልመናን ካቀረቡ በኋላ ከአምላካችን መልስ እስኪመጣልን ድረስ በጽናት መጠበቅ ልክ ፍርድ ፍለጋ ሳትታክት ወደ ዳኛ ትመላለስ እንደነበረችው መበለት (ሉቃ 18፡1-8)፡፡
ሦስተኛው ደገሞ “መታዘዝ” ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም “እሱ የሚላችሁን አድርጉ” ነው ያለችው (ዮሐ 2፡5)፡፡ በመጽሐፍ “መታዘዝ ከመስዋዕት፣ማዳመጥም ከአውራ በግ ስብ ይበልጣል” ይላል (1ሳሙ 15፡22)፡፡ ዛሬ የኢየሱስን እናት ቅድስና የምንዘምረው በሕይወቷ ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃደ ብቻ በመፈጸሟ ነው፡፡ በመጽሐፍ ለክርስቶስ ቃል የታዘዙ ፈውስን እና ጤናን እንዳገኙ ተጽፎልናል (ዮሐ 9፡7፤ ማቴ 12፤13)፡፡ ከዚህ የምንማረው ነገር ቢኖር ደግሞ «በሥጋና በደም ወይም በስሜት ብቻ መመራት ማለት ውድቀታችንንም መጥፊያችንንም ማፋጠን ማለት እንደሆነ ነው»፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ለመንፈሱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የመታዘዝ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡
በአራተኛ ደረጃ የምናገኘው መልዕክት ደግሞ በክርስቶስ ፊት “ያለንን ይዘን መቅረብ” ነው፤ ሰዎቹ ማቅረብ የቻሉት በዚያ የነበሩትን ባዶ ጋኖችና ውሃ ነበር (ዮሐ 2፡6-7)፡፡ ሰው ያለውን ነገር ይዞ የመቅረብ መንፈስ በውስጡ ካለ እግዚአብሔር ቀሪውን ያስተካክለዋል፡፡ ለእግዚአብሔር አሰራር በኛ ዘንድ «ትንሽ» ነው የምንለው ለርሱ ከበቂ በላይ ነው (ዮሐ 6፡1-14፤ ማር 6፡34-44) ፡፡ ሌላው ቢቀር ባዶነቱን ወይም ኃጢአቱን እንኳ ወደ ፈጣሪው ቢያቀርብ የምሕረት አባት የሆነው እርሱ በይቅርታው ነፍሳችንን ያረሰርሳታል፡፡ ስለዚህ ያለንን ይዘን በፊቱ እንቅረብ፣እርሱ በውስጣችን እንዲሰራ እንፍቀድለት፣ያን ጊዜ እኛነታችንን ሲለውጠውና ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው ሲያደርግ እናያለን፣በእምነትም በመንፈስም እናድጋለን፣
የቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን! አሜን!
ሠላም ወሰናይ!
አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን
All the contents on this site are copyrighted ©.