2014-02-19 18:12:42

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ፣


RealAudioMP3 ውድ ወንድሞችና እኅቶች! እንደምን አደራችሁ! በክርስትና መባቻ ምሥጢራት ጥምቀት ሜሮንና ቅዱስ ቍርባን አማካኝነት የሰው ልጅ በክርስቶስ አዲስ ሕይወት ያገኛል፣ ይህንን ሕይወት ይዘን እንደምንጓዝ ሁላችን እናውቃለን ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው “ይህን ክቡር ነገር እንደ ሸክላ ዕቃ ሆነን ይዘነዋል” (2ቆሮ 4፡7) ብኃጢአት ምክንያትም ገና ለፈተና ለስቃይ እና ለሞት የተጋለጥን ነን! ይሰውረን እንጂ ይህንን አዲስ ሕይወት እስክመጥፋትም ልንፈተን እንችላለን፣ ስለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስትያኑ ለወገኖችዋም ሳይቀር የደህንነት ሥራን ለመቀጠል የወሰነው በተለይ ደግሞ የመፈወስ ምሥጢራት በማለት የሚታወቁትን ምሥጢረ ንስሓና ምሥጢረ ቀንዲል ለማስተዳደር ሥልጣን የሰጣት ለዚህ ነው፣ ምሥጢረ ንስሓ የመፈወስ ምሥጢር ነው፣ ልናዘዝ በምሄድበት ጊዜ ልፈውስ ነፍሴን ለመፈወስ ልቤን ካደረግሁት ጥፋት ለመዳን ነው የምሄደው፣ ይህንን በበለጠ የሚገልጠው በወንጌል የምናገኘው ቀዋሚ ምሳሌ የለምጻሙ ሥሬተ ኃጢአትና መፈወስ ነው፣ በዚህ ኢየሱስ የነፍስና የሥጋ ፈዋሽና ሓኪም መሆኑን ይገልጣል (ማር 2፡1-12 ማቴ 9፡1-8 እንዲሁም ሉቃ 5፡17-26 ተመልከት)፣
    ምሥጢረ ኑዛዜ ብለን የምንጠራው የንስሓና የዕርቅ ምሥጢር በቀጥታ ከምሥጢረ ፋሲካ ይመንጫል፣ ከትንሣኤ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሓዋርያት በጽርሓ ጽዮን በዝግ ቤት ሳሉ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ በራሳቸው ላይ እፍ ብሎ “መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ፤ እናንተ ኃጢአቶቻቸውን ይቅር ያላችሁት ሁሉ ኃጢአትታቸው ይቅር ይባልላቸዋል” (ዮሐ 20፡21) በማለት ሥልጣን ሰጣቸው፣ ይህ የቅዱስ መጽሓፍ ክፍል በዚህ ምሥጢር የተያዘውን ጥልቅ ሥራ ይገልጥልናል፣ ከሁሉ አስቀድመን ማወቅ ያለብን የኃጢአት ይቅርታ እኛ ልንሰጠው የምንችል ነገር አይደለም፣ ለምሳሌ ያህል እኔ ኃጢአትህን ይቅር እልሃለሁ ለማለት አልችልም፣ የኃጢአት ይቅርታ ሌላ ነገር ነው የሚጠይቀው ስለሆነም በምሥጢረ ንስሓ ከጌታ ኢየሱስ የኃጢአት ይቅርታን እንጠይቃለን፣ የኃጢአት ይቅርታ የሥራችን ውጤት አይደለም ነገር ግን ጸጋ ነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሆኖ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተና ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ ክርስቶስ ልብ የሚፈልቅ የምሕረትና የጸጋ መታጠብ ነው፣ ሌላ ነገር ደግሞ በጌታ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አባታችንና ከጓደኞቻችን ካልታረቅን በስተቀር እውነተኛ ሰላም ሊኖረን እንደማይቻል ያረጋግጥልናል፣ ይህንን ነገር በብዙ ኃዘንና በከባድ የመጨነቅ ስሜት ወደ ምሥጢረ ንስሓ ሂደን ይቅርታ አግኝተን በምንመለስበት ግዜ ሁላችን አጣጥመነዋል፣ የኢየሱስ ይቅርታን ካጣጣምን በኋላ በልባችን ውስጥ ሰላም ይሰማናል፣ በዚሁ ኢየሱስ ብቻ ሊሰጠን በሚችለው ሰላም ነፍሳችን ጥሩ ይሰማታል፣
    የዚህ ምሥጢር ሥርዓት በመጀመርያ ለሁሉም ሕዝበ ክርስትያን ግልጥ በሆነ ሕዝባዊ መንገድ ይደረግ ነበር፤ ቀስ በቀስ ግን ዛሬ በምንመለከተው ግላዊና ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ሊደረግ ጀመር፣ ይህ ግን የቤተ ክርስትያን ምሥጢር መሆኑንና በቤተ ክርስትያን እንደሚደረግ መዘንጋት የለብንም፣ ስለሆነም በእግዚአብሔር ፍቅር ልቦችን የሚያሳድስና ሁላችንንም ወድማሞች በማድረግ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ የሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ በክርስትያናዊ ማኅበር አማካኝነት ነው የሚኖረውና የሚሠራው፣ እየውላችሁ ለምን በግላችን በሓሳባችንና በልባችን ብቻ ጌታን ይቅርታ በመጠየቅ ንስሓ መግባት የማንችልበት ምክንያት ይህ ነው፣ በትሕትናና በእምነት ኃጢአቶቻችንን ለቤተ ክርስትያን መናዘዝ ያስፈልገናል፣ አንድ ካህን ምሥጢረ ኑዛዜ ሲስጥ እግዚአብሔርን ብቻ አይደለም የሚወክለው ነገር ግን የእያንዳንዱ አባልዋ ደካማነት የምታውቅና ንስሓውን በርኅራኄ የምትቀበለው መላው ቤተ ክርስትያንንም ይወክላል፣ በዚህም ልጅዋን ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ በመካከልዋ ተቀብላው ለለውጥ ጉዞ እንዲሁም ሰብ አዊና ክርስትያናዊ ብስለት እንዲያገኝ ትሸኘዋለች፣ ምናልባት አንዳንድ “እኔ በቀጥታ ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁኝ እንጂ ሌላ አያስፈልገኝም” ለማለት ይችላል፣ እርግጥ ነው እግዚአብሔርን ማረኛ ለማለትና ኃጢአትህን መንገር ይቻላል ነገር ኃጢአቶቻችን እግዚአብሔርን ብቻ አይደለም የሚያሳዝኑ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን በአጠቃላይ ቤተ ክርስትያንንም የሚያሳዝኑ ናቸው ስለዚህ ቤተ ክርስትያንንና ወንድሞቻችንን በካህን ፊት ይቅርታ መጠየቅ አለብን፣ ምናልባት አዎ አባ እውነት ነው ሆኖም ግን ኃፍረት ይሰማኛል ልትሉ ትችላላችሁ፣ እኔ ደግሞ ኃፍረት ሲሰማን ጥሩ ነገር ነው ትንሽ ኃፍረት ሲሰማን ወይንም ሲኖረን ጤንነት ነው፣ ምክንያቱም አንድ ሰው ኃፍረተ ቢስ ከሆነ ያሳዝናል፣ ኃፍረት ጥሩ ነገር ነው ያልኩበት ምክንያት ኃፍረት የሚሰማን ከሆነ ትሕትና ሊኖረን ይችላል ካህኑም የዚህ ዓይነት ኑዛዜን በፍቅርና በርኅራኄ ይቀበለዋል፣ በእግዚአብሔር ስምም ምሕረት ያስገኝለታል፣ በሰብአዊ አመለካከትም ቢሆን በልብህ ያመቅከውን ነገር ለማውጣት ከወንድማሞች ጋር መናገር እንደሚያስፈልገው በኑዛዜም ለካህኑ እነኚህ ነገሮች በልቤ ይከብዱኛል በሎ መናገር ጥሩ ነው፣ እንዲህ በማድረግም በእግዚአብሔር ፊት ከቤተ ክርስትያንና ከወንድሞቻችን ጋር እንታረቃለን፣ ንስሓ መግባትን ኑዛዜን አትፍሩት፣ ምናልባት ለመናዘዝ ሰልፍ ይዞ ሲጠባበቅ ይህ ስሜት ሁሉ ማለት ኃፍረትም ሳይቀር ሊሰማው ይችላል ነገር ግን ተናዝዞ በሚመለስበት ጊዜ ነጻነት አግኝቶ ምሕረት በማግኘቱ ታላቅነትና ፍሥሓ እንደሚሰማው አረጋግጥላችኋለሁ፣ የምሥጢረ ኑዛዜ መልካም ነገርም ይህ ነው፣ አሁን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ እወዳለሁ ግን መልሱ በልባችሁ ይሁን፣ መጨረሻ የተናዘዝክበት ቀን መቼ ነበር? እያንዳንዳችሁ አስተንትኑ! ሁለት ቀኖች ሁለት ሳምንታት ሁለት ዓመታት ሃያ ዓመታት አርባ ዓመታት? እያንዳንዳችሁ እሰቡ እና መጨረሻ የተናዘዝኩት መቼ ይሆን ብላችሁ ገዛ ራሳችሁን ጠይቁ፣ ብዙ ጊዜ ያሳለፋችሁ እንድሆነ አሁኑኑ ጊዜ ሳታባክኑ ወደ ካህን ሂዱ አይዞዋችሁ ካህኑም ትንሽ ርኅራኄ ይኖረው ይሆናል ኢየሱስ ስ እሱማ ከካህኑ ይበልጥ ርህሩኅ ስለሆነ ኢየሱስ በታልቅ ፍቅር ይቀበለሃል፣ ብርታት ይኑርህና ወደ ኑዛዜ ገስግሥ!
    ምሥጢረ ንስሓ ለቤተ ክርስትያን በአደራ የተሰጠ እውነተኛ ታላቅ መዝገብ ነው፣ አብዛኛው ግዜ ግን ይህንን በመዘንጋት እንረሰዋለን፣ አንዳንዴ በሃኬት ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ስለሚያሳፍረን ሊሆን ይችላል ሆኖም ግን ከሁሉ የባሰው ባለንበት ዘመን የኃጢአት ስሜት እጅግ ዝቅ ብለዋል፤ በግል ደረጃም ይሁን በማኅበረሰብ ደረጃ የኃጢአት ክብደትና ሊያስከትለው የሚችለው ጥፋት የተዘነጋ ይመስላል፣ የባሰውኑ ደግሞ በስተስሩ የእግዚአብሔር ስሜት የሌለህ መሆን አለ፣ እያንዳንዳችን ገዛ ራሳችንን ማእከል በማድረግ ሁሉን ለእኛ አገልግሎት ለእኛ በሚመቸን መንገድ ለማንም ተጠያቂ ሳንሆን ለመኖር እንሞክራለን፣ ነገር ግን ልባችንን ለእግዚአብሔርና ለጓደኞችን የዘጋነው እንደሆነ ኅልናችን ይጨልማል ሕይወታችን እንዲያው ዝም ብሎ እንዲጓዝ ይተወዋል፤ መጥፎ ነገርና እርሱ የሚያስከትለው ስቃይን እንኳ አንመለከትም! ስለእርሱም ለማሰብ አንሻም፣

ውዶቼ! ወደ ምሥጢረ ንስሓ መሄድና ኃጢአትን መናዘዝ ማለት የእግዚአብሔር አባታችን ወደር የለሽ ምሕረት በማግኘት በጋለ መንፈስ በእርሱ መታቀፍ ነው፣ በወንጌል ያለውን እጅግ ደስ የሚያሰኝና የሚያጽናና የጥፉ ልጅ ምሳሌን እናስታውስ፣ ልጁ በውርስ የሚገባውን ገንዘብ ይዞ የአባቱን ቤት ጥሎ ከሄደና ሁሉን አጥፍቶ ከጨነቀው በኋላ ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ይወስናል፣ እንደልጅ ሳይሆን እንደባርያ ሊሆን ይወስናል፣ በልቡ ውስጥ ብዙ በደል ይሰማው ነበር ብዙ ኃፍረትም! አስደናቂውና አስገራሚው ነገር የተፈጸመው ግን ገና ልጁ በሩቅ ሲመጣ ያየው አባቱ አላናገረውም አቀፈው ሳመው እንዲሁም ታላቅ ድግሥ እንዲደረግ አዘዘ፣ ልክ እንዲሁ ሁሌ በምንናዘዝበት ግዜ እግዚአብሔር ያቅፈናል ድግስም ያደርጋል፣ በዚሁ ጐዳና እንመላለስ፣ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! እንደገና ወደ እርሱ በመመለሳችሁ የሚገኘውን ደስታ ይስጣችሁ፣ ፍቅሩ እንደገና እንዲወልደን ከእርሱ ጋር እንዲሁም ከግዛ ራሳችንና ከወንድሞቻችን ጋር እንድንታረቅ ያድርገን፣ እግዚአብሔር ይስጥልን፣








All the contents on this site are copyrighted ©.