2013-11-01 16:00:22

ብፁዕ ካርዲናል ፊሎኒ፦ ክርስቲያንና ፓኪስታናዊ መሆኑ አይጋጭም


RealAudioMP3 የአስፍሆተ ወንጌል ለአሕዛብ ተንከባካቢ ቅዱስ ማኅበር ኅየንተ ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዶ ፊሎኒ በአገረ ፓኪስታን ሐዋርያዊ ጉብኝት እያካሄዱ መሆናቸው ቀደም ተብሎ መገለጡ የሚታወስ ሲሆን፣ ብፁዕነታቸው እ.ኤ.አ. ጥቅምት 31 ቀን 2013 ዓ.ም. ላሆር በሚገኘው ካቴድራል በአገሪቱ ብፁዓን ጳጳሳት ካህናት ገዳማውያን ካህናት ታጅበው የአገሪቱ ካቶሊካውያን ምእመናን የትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎች ደናግል ያሳተፈ በመሩት መሥዋዕተ ቅዳሴ ባሰሙት ስብከት አስቀድመው፦ “እናንተንና በእናንተ አማካኝነት በፓኪስታን ከምትገኘው ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ስገናኝ አቢይና ጥልቅ ደስታ ይሰማኛል” እንዳሉ የገለጠው ፊደስ የዜና አገልግሎት፣ እ.ኤ.አ. ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የፋይሳላባድ ጳጳስ እንዲሆኑ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ለሰየሙዋቸው ለክቡር ካህን ጆሰፍ አርሻድ የጵጵስና ማዕርግ መሰጠታቸው ያመለክታል።
እ.ኤ.አ. ጥቅምት 31 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ብፁዕ ካርዲናል ፊሎኒ ከፓኪስታን ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ጋር በመገናኘት የኵላዊት ቤተ ክርስቲያን ቅርበት ለመመስከር በእምነት ወንድሞችና እህቶች ለሆኑት ሁሉ ቀርበው የኵላዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት ልጆች መሆናቸው ለመመስከር ያለመ ነው በማለት እንደገለጡ ፊደስ የዜና አገልግሎት ያሰራጨው ዜና ይጠቁማል።
ብፁዕ ካርዲናል ፊሎኒ በቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ባሰሙት ስብከት፣ የዚያች አገር ዜጎች እምነታቸው ዕለት በዕለት በሚያጋጥማቸው ፈተና ሳይሸነፉ በእግዚአብሔር ፍቅር ተሞልተውና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንክብካቤና ቅርበት መሠረት የሚኖሩት መሆኑ ገልጠው፣ ቅዱስ ጳውሎስ በሁሉም በማንኛው ሁነትና ወቅት አርአያችን ክርስቶስ መሆኑና የፓኪስታን ምእመናን በእምነታቸው ጸንተው ተበራተው በመልካምና በሰላም መንገድ እንዲመላለሱ አሳስበው፣ ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን መሆንና ፓኪስታንዊ መሆን የሚጋጭ ወይንም ሁለት ተቃራኒ ሕይወት እንዳልሆነ ገልጠው፣ የምስልምና እምነት አብላጫ በሆኑባቸው አገሮች እንዲሁም በኅብረ ጎሳ በኅብረ ባህልና በኅብረ ቋንቋ ሃብታም በሆነው ዓለም ዘንድ ክርስቲያን መጤ አንግዳ እንዳልሆነ እንዳውም ክርስትያን ውሁዳን የኅብረተሰብ ክፍል አባል መሆን የሚኖረው ክርስትያናዊ እምነት ብርታት መሆን አለበት እንዳሉ ፊደስ የዜና አገልግሎት አስታወቀ።
ማኅበረ ክርስቲያን በሁሉም ሥፍራ በሁሉም ወቅት ጨውና መብራት እንዲሆን የተጠራ መሆኑ ብፁዕ ካርዲናል ፊሎኒ ባሰሙት ስብከት አበክረው ጨው ምግብን የሚተካ ሳይሆን ምግቡን ያጣፍጣል መብራት መሆን ማለት ደግሞ ተጨባጩ ሁኔታ ለመቀየር ሳይሆን እንዲበራ የሚያደርግ ነው። ክርስቲያን የመሆን ጥሪ ትርጉምም እርሱ ነው ማለትም የእግዚአብሔር አሳቢነት በቃልና በሕይወት መስካሪ መሆን የሚል ጭምር መሆኑ እንዳሰመሩበት የገለጠው ፊደስ የዜና አገልግልቶ አክሎ ክርስቲያን በማኅበራዊ ሕይወት ተልእኮውም ሰላም መግባባት ታማኝነት ውይይት የሚሰዋ ፍቅር ይቅር መባባል ምኅረትና ድኅነት የሚል ነው እንዳሉ አስታውቀዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.