2013-06-27 10:11:22

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ፣


RealAudioMP3 ውድ ወንድሞችና እኅቶች! መልካም ቀን ይሁንላችሁ! ዛሬ የቤተ ክርስትያን ምሥጢርን ለመግለጥ የሚረዳን ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ያቀረበልን መግለጫ ማለትም ቤተ መቅደስ የሚለውን ቃል አጠር ያለ ትምህርት ለመስጠት እሻለሁ (ብርሃነ አሕዛብ ቍ.6)፣
ቤተ መቅደስ የሚለው ቃል ምን ያሳስበናል? ስለሕንጻ እንድናስብ ያደርገናል፣ ለየት ባለ መንገድ ደግሞ የብዙ ሰዎች አሳብ በብሉይ ኪዳን ስለሚነገረው የሕዝበ እስራኤል ታሪክ ይሄዳል፣ በኢየሩሳሌም የሰሎሞን ታላቁ ቤተ መቅደስ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ በቤተ መቅደሱ ውስጥም የእግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መኖሩን የሚያመለክት ታቦተ ኪዳን እንደነበር በዚሁ ታቦተ ኪዳንም የዐሠርቱ ቃላት ጽላት ከሰማይ የወረደው መና እና በትረ አሮን ነበሩ፣ ይህም የሚያመለክተው እግዚአብሔር ሁሌ በሕዝቡ የታሪክ ጉዞ እንደነበረና በጉዞውም እንደሸኛቸውና እንደመራቸው ነው፣ ቤተ መቅደስ ይህንን ታሪክ ያስታውሳል፣ እኛም ወደ ቤተ መቅደስ በምንሄድበት ጊዜ ይህንን ታሪክ ማስታወስ አለብን፣ ማለትም እያንዳንዳችን ኢየሱስ እንዴት እንዳገኘን እንዴት ከእኛ ጋር እንደተጓዘ እንዴት አድርጎ እንደሚያፈቅረንና እንደሚባርከን ታርኬን እያንዳንዳችን ደግሞ ታሪካችን ማስታወስ አለብን፣
በኦሪት በቤተ መቅደስ የተመሰለው በአዲሱ ኪዳን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በቤተ ክርስትያን እውን ሆነ፣ ቤተ ክርስትያን እግዚአብሔር የሚገኝበት ቦታ ጌታን ለማግኘት የምንችልበት ቦታ የእግዚአብሔር ቤት ናት፣ ሕይወት የሚሰጣት የሚመራትና የሚደግፋት መንፈስ ቅዱስት የሚኖርባት ቤተ ክርስትያን ናት፣ እግዚአብሔርን የት ልናገኘው እንችላለን? በኢየሱስ ክርስቶስ አማኝነት ከእርሱ ጋር አንድ ለመሆን የምንችልበት የት ይሁን? ሕይወታችንን የሚያበራ የመንፈስ ቅዱስት ብርሃን የት ልናገኘው እንችላለን? ብለን የጠየቅን እንደሆነ! መልሱ በእግዚአብሔር ሕዝብ በሆነችው ቤተ ክርስትያን በመካከላችን ልናገኘው እንችላለን፣ በእግዚአብሔር ሕዝብ ውስጥ በመካከላችን በቤተ ክርስትያን! በዚሁ ቦታ ኢየሱስ እናገኛለን መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን እግዚአብሔር አብን እናገኛለን፣
በኦሪት እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል እንዳለ የሚገልጥ ተጨባጭ ምልክት ለመስጠጥ ለእግዚአብሔር ቤት ለመስጠት በሰው እጅ የተሠራ መቅደስ ታነጸ፣ በእግዚአብሔር ልጅ ምሥጢረ ሥጋዌ ናታን ለዳዊት በትንቢት የነገረው ተፈጸመ (2ሳሙ 7፤1-29 ተመልከት) ንጉሡ ወይንም እኛ አይደለንም ለእግዚአብሔር ቤት የምንሰጠው ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ቤቱን ያንጻል ይህንንም በመካከላችን በመገኘት ቅዱስ ዮሓንስ በወንጌሉ መግቢያ እንደሚለው ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ (ዮሐ 1፤14)፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ሕያው ቤተ መቅደስ ነው፣ መንፈሳዊ ቤቱ የሆነችው ቤተ ክርትያንንም ራሱ ክርስቶስ ያንጻታል፣ ይህች ቤት በድንጋይ የታነጸ ቤት ሳይሆን ቅ.ጴጥሮስ በመል እክቱ እንደሚለው ሕያው ድንጋዮች በሆንን በእኛ ናት የታነጸችው፣ ቅዱስ ጳውሎስ በኤሬውሶን ለሚገኙ ክርስትያን በጻፈው መል እክቱ፤ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም-በኢየሱስ- ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።”(2፡20-22) ይላል፣ ይህ ደስ የሚያሰኝ ነው! የመዓዝን ድንጋይ ሆኖ ቤቱን ከሚደግፍ ከክርስቶስ ጋር በጥልቅ የተገናኘን እኛ የእግዚአብሔር ቤት ሕያዋን አለቶች፣ ምን ማለት ይሆን? ቤተ መቅደሱ እኛ ነን ማለት ነው፣ ቤተ ክርስትያኑ እኛ ነን፣ ሕይወት ያለን እኛ ቤተ ክርስትያን ነን ሕያው ቤተ መቅደስ ነን፣ አብረን በአንድነት ስንጓዝ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አለ እንደ ቤተ ክርስትያን ለማደግም ይረዳናል፣ በተናጠል የምንኖር አይደለንም፣ ሁላችን በአንድነት የእግዚአብሔር ሕዝብ ነን፣ ቤተ ክርስትያንም ይህች ናት፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣
ነን
መንፈስ ቅዱስም በተለያዩ ስጦታዎቹ ልዩነቶቻችን በኅብረት ያቀናጃል፤ ይህ አስፈላጊ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ በእኛ መካከል ሆኖ ምን ያደርጋል? ብለን የጠየቅን እንደሆነ፣ ልዩ ልዩ ዓይነቶች ሆነን በአንድነት እንድንራመድ ዕቅድ ያወጣል፣ ይህም በቤተ ክርስትያን ሃብት ሆኖ ሁላንና ሁላችንን አንድ ያደርጋል እንዲህ በማድረግም መንፈሳዊ ቤተ መቅደስን ያንጻል፣ በዚሁ መንፈሳዊ መቅደስ ቍሳዊ መስዋዕት ሳይሆን ገዛ ራሳችንን ሕይወታችንን መስዋዕት እናቀርባለን (1ኛ ጴጥ 2፤4-5 ተመልከት)፣ ቤተ ክርስትያን የነገሮች ክምችት አይደለችም ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ናት፣ በዚሁ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ይሠራል፣ በዚሁ ቤተ መቅደስ እያንዳንዳችን በምሥጢረ ጥምቀት ሕያው አለት እንሆናለን፣ ይህ የሚያረጋግጥልን ነገር ደግሞ የማይረባ ማንም እንደሌለ ነው፣ በቤተ ክርስትያን ውስጥ የማይረባ ማንም የለም፣ ምናልባት አንድ ክርስትያን ለሌላው አንተ ምንም አትጠቅምም ወደ ቤትህ ሂድ ያለ እንደሆነ ይህ ስህተት ነው፣ እኛ ሁላችን ቤቤተ ክርስትያን አስፈላጊዎች ነን፣ ሁላችን በእግዚአብሔር ዓይን ፊት እኩል ነን፣ ነገር ግን ምናልባት ከእናንተ መካከል አንድ ሰው “ሆኖም ግን እርስዎ ር.ሊ.ጳ ከእኛ ጋር እኩል አይደላችሁም” ማለት ይችላል፣ እንደማንኛው ሰው እንደናንተ ነኝ ሁላችን እኩል ነን ሁላችን ወንድማሞች ነን፣ ከዚህ የሚወጣ ማንም የለም፣ ሁላችን አብረን ቤተ ክርስትያንን እናቋቁማለን እናንጻነልም፣ ይህ የሚያሳስበን ነገር ደግሞ ከቤተ ክርስትያን አንድ ድንጋያችን የጐደለ እንደሆነ የቤተ ክርስትያናችን ውበት አንድ ነገር ይጐድለዋል፣ ሌሎች ደግሞ እኔ ከቤተ ክርስትያን ጋር የሚያገናኘን ምንም የለኝም የሚሉም አሉ፣ ሆኖም ግን በዚሁ መልካም ሕንጻ አንተ የምትሸፍነው ቦታ ባዶ የቀረ እንደሆነ ችግር ነው፣ ስለዚህ ማንም ሊሄድ ሊያንፈግፍግ አይችልም፣ ሁላችን ለዚች ቤተ ክርስትያን ሕይወታችን ልባችን ፍቅራችን ሃሳባችን ሥራችን ወዘተ መስጠት አለብን፣
ቤተ ክርስትያናችንን እንዴት እንኖራታለን? ሕያው አለቶች ነን ወይስ የደከሙ የሰለቹ ወላዋዮች ነን? ይሁንና! አንድ የደከመ የሰለቸው ወላዋይ ክርስትያን እንዴት መጥፎ መሆኑን አይታችህዋል ወይ? እንዲህ ዓይነት ክርስትያን እጅግ መጥፎ ነው! አያስኬድምም! ክርስትያን ሕያው መሆን አለበት! ክርስትያን በመሆኑ ደስተኛ መሆን አለበት! ይህንን መልካም ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ እንደቤተ ክርስትያን መኖር አለበት፣ በማኅበሮቻችን ሕይወት ተካፋዮች እንድንሆን ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ልቦቻችንን እንክፈት፣ መፈጸም ያለብን ብዙ ነገሮች አሉኝ የሌሎች ጉዳይ አይመለከተኝም በማለት በገዛ ራሶቻችን ተዘግተን እንዳንቀር አደራ፣
ከመዓዝን ድንጋይ የሆነው ክርስቶስ እንዲሁም የሕይወታችንና የቤተ ክርስትያን ሕይወት ደጋፊ ከሆነው ክርስቶስ ጋር አንድ እንድንሆን ጌታ ጸጋውና ኃይሉን ይስጠን፣ በመንፈስ ቅዱስ ተንቀሳቅሰን የቤተ ክርስትያን ሕያው አለቶች እንድሆን ጌታን እንለምነው፣








All the contents on this site are copyrighted ©.