2013-03-17 16:57:01

የአዲሱ ር.ሊ.ጳ ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮስ ምርጫ በተለያዩ ሰዎች ያሳደረው ስሜት፤


የአዲሱ ር.ሊ.ጳ ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮስ ምርጫ ለመላው ዓለም ያስደነቀና ያልተጠበቀ ደስታ የፈጠረ ሁኔታ ሲሆን ከምርጫው ይልቅ ደግሞ በዝናምና ብርድ እየተመታ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይና አከባቢው እርስ በእርስ ተጨናንቀው በብርቱ ጉጉት በሲስትን ቤተ መቅደስ ጣራ የነበረውን ጭስ ማውጫ አንጋጦው ሲመለከቱ ለረዥም ሰዓታት ከተጠባበቁ በኋላ አዲስ ር.ሊ.ጳ የመመርጥ ምሥራች የሚያመለክት ነጭ ጭስ በወጣ ጊዜ እና ተከታትሎም የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ደወሎች ሲደወሉ የተሰማው የደስታ ድምጽ አሰደናቂ ነበር፣ ጥቂት ቆየት ብሎም ቀዳሜ ዲያቆናት ብፁዕ ካርዲናል ቱራን ታላቅ ደስታ አበስራችዋለሁ ብለው አዲስ ጳጳስ እንዳገኘን እና አዲሱ ጳጳሳም የቅድስት ሮማዊት ቤተ ክርስትያን ል ዑልና ብፁዕ ካርዲናል በርጎልዮ መሆናቸውና የር.ሊ.ጵጵስና ስማቸው ፍራንቸስኮ እንዲሆን መምረጣቸውን ከገለጡና አዲሱ ር.ሊ.ጳ ሰላምታ አቅርበው ሐዋርያዊ ቡራኬ እንደሰጡ በአደባባዩ የተገኙ ሕዝብ ስሜት የመገረምና የመደነቅ እንደነበር በቦታው የተገኘት የቫቲካን ረድዮ ጋዜጠኛ ደቦራ ዶኒኒ ገለጠች፣
በእነኚሁ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ካህናት ደናግል እና ም እመናን የተለያዩ አገር ዜጎች እና ከአዛውንቶች እስከ ሕጻናት ነበሩ፣
አንዲት ሕጻን ልጅ ያቀፈች ወጣት እናት ታላቅ ደስታ እንደተሰማትና አዲሱ ር.ሊ.ጳ የዋህ እንደሆኑ ገልጣ ስለ እርሱ እንደምትጸልይ በብርቱ ስሜት ገለጠች፣
ሌላው ብዙዎችን ያስገረመና ያስደነቀ ከኤውሮጳ ውጭ ር.ሊ.ጳ ለመጀመርያ ጊዜ መመረጡ የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል ለመጀመርያ ጊዜ መመረጡ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ፍራንቸስኮስ የሚል ስም መምረጣቸው ነው፣
ከደቡብ አመሪካ እንደአጋጣሚ በቦታው የተገኘት የደስታ እንባ እየተናነቃት እጅግ ደስ ብሎኛል የደቡብ አመሪካ ሕዝቦችን የሚወክሉ ር.ሊ.ጳ በማግኘታችን ደግሞ እጅጉ ደስ ይለኛል በማለት በተደረገው ምርጫ እንደረካችና ደስ እንዳላት ገልጣለች፣
በእንዲህ ዓይነት አስተያየታቸውን ለጋዜጠኛችን የሰጡ የተለያዩ ሰዎች አንድ ዓይነት ስሜትና አስተሳሰብ እንደነበራቸው ይህም የደስታ የመደነቅና የመገረም ሆኖ ሁላቸው እርካታ እንደተሰማቸውና ስለ አዲሱ ር.ሊ.ጳ እንደሚጸልዩ አመልክተዋል፣
ከሁሉ በላይ ሁላቸውን ያደነቀውና እንደ የመደንገጥ ስሜትም የፈጠረባቸው ሁኔታ ብዙ ሰዎች በላቀ እምነትና ስሜት የገለጡት አዲሱ ር.ሊ.ጳ ለሕዝቡ ሐዋርያዊ ቡራኬ ከመስጠታቸው በፊት መጀመርያ ሕዝቡ እሳቸውን እንዲባርክ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ሁላቸው ስለ ር.ሊ.ጳ እንዲጸልዩ በጠየቁ ጊዜ መሆኑ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሕዝብ ሲቀርቡ ጠቅላላውን በቅዱስ ጴጥሮስ የነበረውንና በብዙኃን መጋነኛ ሲከታተልዋቸው ለነበሩ በመላው ዓለም የሚገኙ አማንያንንን በኅብረት እንዲጸልዩ ማድረጋቸው ይህም እጅግ ገር በሆነ መንገድ ማድረጋቸው እንደነበረ ገልጠዋል፣

የቅድስት መንበር የዜናና ኅትመት አላፊና ዋና የቫቲካን ረድዮ አስተዳዳሪ ትናንትና ለጛዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ር.ሊ.ጳ ሆነው መመረጣቸው ለሁላችን አስገረመን” ሲሉ ፍጻሜው ብዙ ሰዎች ያልጠበቁት በመኖሩ ብርቱ አድናቆት እንዳተረፈ ገልጠዋል፣
አባ ሎምባርዲ በመግለጫቸው አዲሱ ር.ሊ.ጳ እውነተኛ መነኵሴ ገርና ትሑት መሆናቸውን የሚያመለክቱ ገና ከመመረጣቸው ጀምረው ድሮ ይደረግ የነበረውን የሥልጣነ ጴጥሮስ አመለካከትና አኗኗር እየቀሩት መሆናቸው ገልጠዋል፣ መጀመርያ ር.ሊ.ጳ ተመርጠው ወንድሞቻቸው ካርዲናሎች በሲስቲን ቤተ መቅደስ ሰላምታ ሲያቀርቡላቸው በዘልማድ በመንበር ተቀምጦ ይደረግ ከነበረው ልማድ አንጻር ቅዱስነታቸው ወንድሞቻቸውን ካርድናሎች ቆመው እያንዳንዱን ተቀብለው ሰላም በማለት ታማኝነታቸውና ታዛዥነታቸውን ተቀብለዋል፣ ሁሉን ጨርሰው ወደ ማደርያቸው ለመመለስ ልዩ የር.ሊ.ጳ ማኪና ባቀረቡላቸውም አይሆንም ብለው ከሌሎቹ ካርዲናሎች ጋር በአውቶቡስ ሄደዋል፣ ትናንትና ጥዋት እመቤታችን ድንግል ማርያምን ሊማጠኑ ወደ ሳንታ ማርያ ማጆረ ባዚሊካ ሲሄዱም ምንም አያስፈልገኝም በማለት በቫትካን ጥበቃ ወታደሮች ማኪና ሄደዋል፣ ከዛም እንደማንኛው ወደ ዝግ ጉባኤው እስኪገቡ ወደ ነበሩበት ሆቴል በመሄድ ሂሳባቸውን ከፍለው የሆቴሉ ሰራተኞችን እያንዳንቸው በስማቸው እየጠሩ ሰላም ብለው ተመልሰዋል፣ የጵጵስና ምልክታቸው የአንገት ኃብልና መስቀልም ገና እንደ ካርዲናል ይጠቀሙት የነበሩት ነው፣ ሲሉ ምንኛ ያህል ለጵጵስና ስማቸው የመረጡት ቅ.ፍራቸስኮስ ድኃና ትሑት ቤተ ክርስትያንን በየዋህነትና በኅበረት ሊመሩ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጠዋል፣

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቦነስ አየረስ ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ከአንድ ወር በፊት ለሃገረ ስብከቶቻቸው በጻፉት መልእክት “መለወጥ ይቻላል” ብለው ነበር፣
በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ጾመ ነነዌን የሚያሳስብ የአመድ ሮብ በሚለው ዝክረ ዕለት እንደ ጾመ አርባ መባቻ ይጠቀሙታል፣ እንደአጋጣሚ ደግሞ ለር.ሊ.ጵጵስና ከተመረጡት ካለፈው ዕለት ልክ ከአንድ ወር በፊት “ልብሶቻችሁ ሳይሆን ልቦቻችሁን ቅደዱ” በሚል ርእስ የጾመ አርባ ጽፈው እንደነበር ተመልክተዋል፣
ያኔ የቦነስ አየርስ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው በየዕለቱ በሃገሪቱ በሚከናወኑ አሳዛኝ ድራማዎችና የክርስትያኖች ግድየለሽነት አመልክተው “እነኚሁ ድራማዎች በየጉዳናዊ በየቀበሌው በየቤቶቻችን የባሰው ደግሞ በየልቦቻችን እየተካሄዱ መሆናቸውና ሕይወት ከሚያጠፋና ቤተሰብ በሚያወድም ዓመጽ ጋር አብረን እንደምንኖርና በመላው ዓለም ውግ ያና ጸብ እየጫረ ባለው ቅናት ጥላቻና ንጹሓንንና ሰላማውያን ሰዎችን በማሰቃየት ገላብጦ እየገረፈን ካለ ዓመጽ ጋር እንኖራለን፣ ራስ ወዳድነትና የሁሉ ክፋት ሥር የሆነ የገንዘብ ግዛት እንዲሁም ይህ ግዛት በሚያስከትለው እንደ ሙስና ዕጸ ፋርስ እና የሰው ልጅ ንግድ ከበውን ቍሳዊና ሞራላዊ ድህነት ያጠቃን ሰዎች ሆነናል፣ ስለዚህ በዚሁ የጾም ጊዜ ልባችን ተነክቶ ነቢዩ እንዳለው የልቦቻችን ልብሶች ቀደን እንታደስ ብለው ነበር፣








All the contents on this site are copyrighted ©.