2013-03-13 22:18:21

ንዜንወክሙ ዜና ሠናየ!


ንዜንወክሙ ዜና ሠናየ! መልካም ዜና እናበሥራችሁዋለን! ር.ሊ.ጳ አለን (አግኝተናል)፣
ልዑልና ጥቀ ክቡር የሮማዊት ቅድስት ቤተ ክርስትያን ካርዲናል የሆኑ ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ ማርዮ ቦርጎልዮ ናቸው፣
የጵጵስና ስማቸውም ፍራንቸስኮ እንዲሆን መርጠዋል፣

ብፁዓን አበው ለሳምንታት ያህል በጸሎትና በአስተንትኖ እንዲሁም በውይይት ከሰነበቱ በኋላ ትናንትና ከትናንትና ወዲያ ማምሻውን ዝግ የር.ሊ.ጳ ምርጫ ጉባኤ ማለትም ኮንክላቨ እንደጀመሩና ሁለቴ ባካሄዱት ምርጫ የተፈለገው ቍጥር ባለመገኘቱ በጥቁር ጭስ ምልክት እንዳሳወቁ በትናንትናው ዜናችን መነገሩ የሚታወስ ሲሆን፤
ትናንትና ማታ በብዙ የሚቆጠሩ ቤተ ክህነትና ም እመናን ዝናብም ይሁን ብርድ ሳየሸንፋቸው ለሰዓታት ሲጸልዩና ሲጠባበቁ አምሽተው በሮም ሰዓት አቆጣጠር ልክ 19፡06 ማለትም ከቀትር 7 ሰዓት ላይ ነጭ ጭስ ባዩ ጊዜ በጭብጨባና በምስጋና መዝሙር አደባባዩን አናወጡት፤ ወዲያውኑ የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ደወሎችና የመላ የሮማ ከተማ አብያተ ክርስትያን ደወሎች የምሥራች ዜናን ለማብሰር ለረዥም ጊዜ ተደወሉ፣
ይህ ዝግ ጉባኤ ወይንም ኮንክላቨ ዛሬ እንደምናውቀው ሆኖ ሲካሄድ ለ75ኛ ጊዜው ነው፣ በካፐላ ሲስቲና ወይንም በሲስቲን ቤተ መቅደስ በመንበረ ጴጥሮስ መካሄድ ከተጀመረበትም 25ኛ ነው፣ በትናንትናው ዕለት የተካሄደው ምርጫ
በአምስተኛው ዙርያ ነው፣
እነኚህ ዛሬ የተመረጡ ር.ሊ.ጳ ከቅዱስ ጴጥሮስ በኋላ 266ኛ ነው፣
በትናንትናው ዜና እንደተገለጠው ጉባኤ የተጀመረው 12 መጋቢት ሲሆን የመጀመርያው ጭስ የተላከው ማክሰኞ ዕለት በሮም ሰዓት አቆጣጠር 19፤42 ሁለተኛ ደግሞ ሮብ ዕለት 13 መጋቢት 11፡40 ነበር፣

የሕይወት ታሪካቸው
ቅዱስነታቸው ር.ሊ.ጳ ሆነው ከመመርጣቸው በፊት እስከ ትናንትና የቦነስ አየርስ አርጀንቲና ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል፣ የተወለዱበትም እዛው ቦነስ አየርስ ሆኖ እ.አ.አ ታሕሳስ 17 ቀን 1936 ዓም ነው፣
ትምህርታቸው በመጀመርያ በተክኒካል ከሚስትሪ ተመርቀዋል ሆኖም ግን የክህነት ሕይወት ስለመረጡ በቪላ ደቮቶ ዘር አ ክህነት ገብተዋል መጋቢት 11 ቀን 1958 ዓም በኢየሱሳውያን ማኅበር ተመካሪ በመሆን የጀመሩት ረዥም የትምህርትና አገልግሎት ጉዞ ካሳለፉ በኋላ በታሕሳስ ወር 13 ቀን 1969 ዓም ክህነት ተቀብለው እንደ ኢየሱሳዊ ደግሞ በስፐይን አልካላ ደ ሄናረስ ሚያዝያ 22 ቀን 1973 ዓም የመጨረሻ መሓላቸውን አድርገዋል፣ ግንቦት 20 ቀን 1992 ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቦነስ አየርስ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብለው ሲሾሙዋቸው የካቲት 28 ቀን 1998 ዓም ምሕረት ደግሞ የቦነስ አየርስ ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ የካቲት 21 ቀን 2001 ዓም ደግሞ ብፁዕ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካርዲናል እንደሾሙዋቸው ይነገራል፣.








All the contents on this site are copyrighted ©.