2012-12-05 16:34:47

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፤


ውድ ወንድሞችና እኅቶች፧ ሐዋርያ ጳውሎስ በኤፈውሶን ለሚገኙ ክርስትያኖች በጻፈው መልእክት መግቢያ ላይ (1፡3-14) የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር አብ የሚከተለውን የቡራኬ ጸሎት ያሳርጋል፣ “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።” ይህ ጸሎት በዚሁ በእምነት ዓመት በምንገኝበት ጊዜ ዘመነ ምጽአትን በሚገባ ለመኖር ይረዳናል፣ የዚሁ የምስጋና ጸሎት አንኳር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የድኅንነት ዕቅድ ሲሆን ይህም ደስታና ምስጋና በሞላቸው ቃላት እንደ “እግዚአብሔር የቸርነት ዕቅድ” የምሕረት እና የፍቅር ዕቅድ ተብሎ ተገልጠዋል፣ ለምንድር ነው ሐዋርያዊ ይህንን የምስጋና ጸሎት በኃያል ስሜት ከልቡ ለእግዚአብሔር የሚያሳርገው፧ ብለን የጠየቅን እንደሆነ በምሥጢረ ሥጋዌ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የተፈጸመው የሰው ልጅ የደኅንነት ታሪክ ውስጥ መሥራቱን ስለሚመለከትና ሰማያዊ አባታችን ገና ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመዋጀትና እኛም በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ማድረጉን ያስተነትናል (ሮሜ 8፡14፤ ገላ 4፡4 ተመልከት)፣ ስለዚህ እኛ ከዘለዓለም እግዚአብሔር በገዛ ራሱ በያዘው ጊዜው በደረሰ ግዜም ባከናወነውና በገለጠው በታላቁ ዕቅድ አማካንኝነት በእግዚአብሔር አሳብ እንኖራለን ማለት ነው፣ ቅዱስ ጳውሎስ ፍጥረት ሁሉ በተለይ ደግሞ የሰው ልጅ የአጋጣሚ ውጤት እንዳልሆኑ ነገር ግን በዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር አሳብ የቸርነት ዕቅድ ግብረ መልስ መሆኑና እግዚአብሔር በፈጣሪ እና አዳኝ ችሎታው በሆነው ቃሉ ግዜው በደረሰ ጊዜ የዓለም ፍጥረትን ጀመረ፣ ይህ የመጀመርያው እርግጠኝነት የሚያሳስበን ነገር የመጀመርያ ጥሪያችን ለመኖር ወይንም በታሪክ ውስጥ እንድንወያይ ወይንም የእግዚአብሔር ፍጡር ብቻ ለመሆን ሳይሆን ከዚህ ለላቀ ዕቅድ ነው የተፈጠርነው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር የተመረጥን መሆናችን ነው፣ ስለዚህ እኛ በእግዚአብሔር አሳብ ሁሌ ነበርን፣ እግዚአብሔር አብ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ጸጋ ልጆቹ ያስበናል፣ ሐዋርያ ጳውሎስ የእግዚአብሔር የቸርነት ዕቅድ የሚለውን የፍቅር ዕቅድ በማለት የመለኮታዊ ፈቃድ ምሥጢርም ይለዋል፣ ይህ ምሥጢር ስውር ነበር አሁን ግን በኢየሱስ ክርስቶስ አካልና ተግባር ተከሰተልን፣ መለኮታዊው ጅማሬ ማንኛውም የሰው ልጅ ግብረ መልስ ይቀድማል፣ በነጻ የተቀበልነው የፍቅሩ ስጦታ ሆኖ ይከድነናል ይለውጠናልም፣
ሆኖም ግን የዚሁ ምሥጢራዊ ዕቅድ የመጨረሻ ዓላማ ምንድር ነው፧ የእግዚአብሔር ፈቃድ ዋነኛ ነጥብ የትኛው ነው፧ ብለን የጠየቅን እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ “በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” (ኍ 10) የሚል መልስ ይሰጠናል፣ በዚህ መግለጫ የአዲስ ኪዳን ዋነኛ አንቀጸ ሃይማኖቶች ከሆኑት የእግዚአብሔር ዕቅዶች የአንዱን ማብራርያ እናገኛለን፣ ይህ ለመላው የሰው ልጆች የቀረበው የፍቅር ዕቅድ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የልዮኑ ቅዱስ ኤረኔዎስ ስለ ክርስቶስ ባቀረበው ትምህርት ማለት ክሪስቶሎጂ ሁሉንም ነገር በክርስቶስ መጠቅለል በሚል ሓረግ እናገኛለን፣ ምናልባት ከእናንተ መካከል ቅዱስ ፕዮስ 10ኛ ዓለምን ለጥቀ ቅዱስ ልበ ኢየሱስ ሲያማጥኑ ያሉትን አጭር ጸሎት ማለትም “ሁሉንም በክርስቶስ እንደገና እንዲታነጽ” የሚለውን ታስታውሱ ይሆናል፣ ይህ ጸሎት የቅዱስ ጳውሎስ መግለጫ ያስታውሳል፣ ቅዱስ ፕዮስ ር.ሊ.ጳ ሆነው በተመረጡበት የመረጡት መሪ ቃላቸውም ይህ ነበር፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ሁሉ አቀፋዊ በክርስቶስ ሥር የመሆኑና በእርሱ ስለ የመመራት ጉዳይ ይናገራል ስለዚ ስለጠቅላላው ታላቁ የፍጥረትና የታሪክ ዕቅድ ይናገራል፣ ከርስቶስም የዚህ ማእከል ሆኖ የመላው ዓለም ጉዞን በመያዝ ሁሉንም ፍጥረት ወደ እርሱ ይስበዋል፣ ይህንንም የሚያደርገው ደግሞ መበታተንን ውሱንነትን ለማሸነፍና ሁሉም እግዚአብሔር ወደ ፈቀደው ሙላት እንዲያደርስ ነው (ኤፈ 1:23 ተመልከት)፣
ይህ የእግዚአብሔር የቸርነት ዕቅድ በሰማየ ሰማያት በእግዚአብሔር ጸጥታ ተደብቆ አልቀረም ነገር ግን ከሰው ልጅ ጋር መገናኛ መንገድ በመፍጠር አሳወቀው፣ በዚሁ መገናኛ ራሱን ከመግለጥ በስተቀር ሌላ ምንም ያደረገው ነገር የለም፣ እርሱ የእውነት ዝርዝር አልገለጠልንም፤ ከእኛ አንድ እስከ መሆን ድረስ ራሱን ገለጠልን በዚሁም እንደኛ ሥጋ ለበሰ፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ደይ ቨርቡም ቃለ እግዚአብሔር በሚለው ሰነዱ ላይ “እግዚአብሔር በየዋህነቱና በጥበቡ ራሱን በመግለጥ የመለኮታዊ ፈቃዱ ምሥጢር ለመግለጥ ወደደ፣ የእርሱ ፈቃድ ደግሞ ሥጋ በለበሰው ቃሉና በመንፈስ ቅዱስ የሰው ልጆች ሁላቸው ከእግዚአብሔር አብ ጋር ግኑኝነት እንዲኖራቸውና ከአምላካዊው ባህርዩም ተካፋዮች እንዲሆኑ ነው” (ቍ 2) ይላል፣ እግዚአብሔር የሆነ ነገር አይነግረንም ራሱን ይገልጥለናል ወደ መለኮታዊ ባህርዩ ይስበናል በዚህም እኛ በመለኮታዊ ባህርዩ ተካፋይ ሁነናል መለኮታውያን ሆነናል፣ እግዚአብሔር ታላቁን የፍቅር ዕቅዱን ከሰው ልጆች ጋር በመገናኘት ራሱ ሰው እስከመሆን ድረስ በመቅረብ ይገልጠዋል፣ እላይ በተጠቀሰው ሰነዱ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ “የማይታየው እግዚአብሔር የሰው ልጆችን እንዲጠራና ከእርሱ ጋር ሱታፌ እንዲኖራቸው ለማድረግ በታላቅ ፍቅሩ ከሰው ልጆች እንደ ጓደኛ ይናገራቸዋል፤ በመካከላቸውም ይኖራል፤” ይላል፣ የሰው ልጅ በአ እምሮውና በችሎታው ብቻ ለዚሁ ዓይነት ብሩህ የእግዚአብሔር ፍቅር ግልጸት ሊደርስ አይችልም፣ እግዚአብሔር ራሱ ነው ሰማዩን የከፈተለትና የሰው ልጅን ወደር ለሌው ፍቅሩ እንዲመራው ራሱን ዝቅ ያደረገው እግዚአብሔር ራሱ ነው፣ (ይቀጥላል)








All the contents on this site are copyrighted ©.