2012-12-03 15:02:46

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ከመናብርተ ጥበብ ተማሪዎች ጋር ለጸሎተ ሠርክ


RealAudioMP3 እ.ኤ.አ. ቅዳሜ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በላቲን ሥርዓት የዘመነ መጽአት መግቢያ ቀዳሜ ሰንበት ምክንያት ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ከሮማ መናብርተ ጥበብና ሮማ ከሚገኙት ከጳጳሳዊ መናብርተ ጥበብ ተመሪዎች ጋር በመሆን አንደኛ ጸሎተ ሠርክ መድገማቸው የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ አመደዮ ሎሞናኮ አስታወቁ።
ቅዱስ አባታችን የመናብርተ ጥበብ ተማሪዎች በተገኙበት ጸሎተ ሠርክ መርተው በሰጡት ሥልጣናዊ መሪ ቃል፦ በእውነተኛ መንፈስ የሚኖር ሊጡርጊያዊ ሱታፌ ዘወትር ለቤተ ክርስትያን ግንባታ ኅያው ድንጋዮችና ለአዲስ አስፍሆተ ወንጌል ተባባሪዎች ለመሆን የሚያበቃ የሕንጸት መሠረት ነው” በማለት በዚህ የዓመቱ ሊጡርጊያ የእምነት ጉዞ ሲያመልክቱም፦ “ይኸንን የእምነት ጉዞ ከቤት ክርስትያን ጋር ስናከብርና ስንኖረውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ የቆስሞስና የታሪክ ጌታ መሆኑ በመታመን አለ እርሱ ማንኛውም ሰብአዊ ጥረትና ሰብአዊ ሕንጸት ወደ ባዶነት የሚያመራ ትርጉም አልቦ መሆኑ የምናረጋግጥበት ሂደት ነው” ብለዋል።
በቅዱስ ቁርባን ኅያው እግዚአብሔር በጉዞአችን እኛን ለመደገፍ ገዛ እራሱን ለሰው ልጅ ቅርብ እንዳደረገ ሲታወቅ፣ በዚህ በምንኖርበት ዘመን እግዚአብሔርን ቸል የማለቱ አዝማሚያ በስፋት ይታያል። “ሆኖም ብዙዎች ከእግዚአብሔር ርቆ መኖርን የተያያዙት ምርጫ ቢሆንም ቅሉ በውስጣቸው የፍጹም ወሰን አልቦ እና ዳር ማዶነትን መናፈቅ እንዳለ ነው።” ካሉ በኋላ፦ “ስለዚህ እናንተ የመናብርተ ጥበብ ተማሪዎች ቅርባችን የሆነውን የእግዚአብሔር እውነትን ለማወቅ በሚደረገው ጥናት እንዲሁም በሚደረገው ምርምር ሁሉ የሚገለጥ መሆኑ ለሚያረጋግጥ የምስክርነት ተልእኮ ተጠርታችኋል” እንዳሉ ልኡክ ጋዜጠኛ ሎሞናኮ አስታወቁ።
እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ቅርብ፣ ለፍቅሩ ታማኝ በመሆኑም፣ አይኖቹን በላያችን ላይ በማኖር የሰውን ዘር ወደ ሰላምና ብልጽግና የሚመራ ሕዝቡን ፈጽሞ የማይረሳ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ እግዚአብሔር ቅርብና ታማኝ መሆኑ ቅዱስ አባታችን ሲያብራሩ፦ “እግዚአብሔር በመንግሥቱ ተዘግቶ የሚቀር ሳይሆን የሰው ልጅ ተስፋ ከሚያኖርበትና ከሚጠባበቀው ሁሉ በላይ ልቆ ገዛ እራሱ ለሰው ልጅ ሁኔታ ዝቅ በማድረግ ‘በትስብእቱ ለሰው ልጅ ቅርብ በመሆን የሰውን ልጅ ወደ እግዚአብሔር ታላቅነት ከፍ ያደረገ አምላክ ነው” እንዳሉ የገለጡት የቫቲካን ረዲዮ ልኡክ ጋዜጠኛ ሎሞናኮ አያይዘውም፣ “የክርስትና እምነት ለአንድ ተራ የሆነ ወይንም ለማይገለጥ እግዚአብሔር መከተል ማለት ሳይሆን፣ ሥጋ የሆነው ቃል በሰው ልጅ ታሪክ በመግባት የሰው ልጅ አዳኝ መሆኑ ገዛ እራሱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገለጠው ኅያው እግዚአብሔር ማመን ማለት ነው። ስለዚህ ማመን ማለት የገዛ እራስን ሕይወት ምልአት ለሚሰጠው፣ ጊዜ ከሚገምተው በላይ ለሆነው ተስፋ ክፍት እንዲሆ ለሚያደርገው እግዚአብሔር መታመን ማለት ነው።” ሲሉ ያሰሙትን ሥልጣናዊ ቃል እንዳጠናቀቁ አስታውቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.