2012-10-31 17:04:36

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፧ በካቶሊካዊ እምነት ዙርያ የጀመርነውን አስተንትኖ እንቀጥላለን፣ ባለፈው ሳምት እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር የመጀመርያ ተነሳሽነት በማድረግ ሊያገኘን እንደሚመጣ፤ እምነትም ይህንን የሕይወታችን የማይነቃነቅ መሠረት በመቀበል ለእርሱ የምንሰጠው መልስ መሆኑን አመልክቼ ነበር፣ ኑሮአችንን የሚቀይር ስጦታ ነው ምክንያቱም በኢየሱስ አስተሳሰብ እንድንገባ ያደርገናል ይህ አስተሳሰብም በልባችን እየሠራ ለእግዚአብሔርና ለጓደኛ ፍቅር ክፍት ያደርገናል፣
ዛሬ በዚሁ አስተንትኖአችን እንደወትረው ከአንድ ጥያዌ በመነሣት አንድ እርምጃ ለመራመድ እወዳለሁ፣ የእምነት ባህርይ የግል ወይንም ተናጠላዊ ብቻ ነውን፧ እኔን በግሌ ብቻ ይመለከታልን፧ እምነቴን ብቻየን ነው የምኖረው፧ እርግጥ ነው እምነት እጅግ ጥልቅ በሆነ መንገድ በግል ከእግዚአብሔር የምንገናኝበትና በግል ሕይወቴ ሥርነቀል ለውጥ በማድረግ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጅማሬ የማገኝበት ጥብቅ የግል ጉዳይ ነው፣ በምስጢረ ጥምቀት ሥርዓተ አምልኮ ሥርዓቱን የሚፈጽመው ልኡክ ጥምቀት ፈላጊውን ካትሊካዊ እምነቱን ለመግለጥ በሚደረገው የመሐላ ጊዜ ሶስት ጥያቄዎች ያቀርባል፣ ሁሉ ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር አብ ታማላችሁን፧ አንድያ ልጁ በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ታምላችሁን፧ በመንፈስ ቅዱስ ታምናላችሁን፤ ብሎ ይጠይቃል፣ በጥንቱ ጊዜ እነኚህ ጥያቄዎች ተጠማቂው ሶስቴ በውኃ ውስጥ ከመጥለቁ በፊት በቀጥታ ለተጠማቂው ነበር የሚቀርቡት፣ ዛሬም ቢሆን ለጥያቄው የሚሰጠው መልስ የግል ሆኖ “አምናለሁ” የሚል ነው፣ ይህ እምነቴ ግን የግል መመራመር ውጤት አይደለም ነገር ግን የአንድ ግኑኝነት የአንድ ውይይት ፍሬ፣ በዚሁ ግኑኝነት ጸጥ ብሎ ማዳመጥ መቀበልና መልስ መስጠት አለ፣ ይህም ከተዘጋው እኔነት አውጥቶ ከኢየሱስ ጋር በመገናኘ ለእግዚአብሔር አብ ፍቅር ክፍት የሚያደርገኝ ነው፣ ይህም እንደግነና በአዲስ እንደመወለድና ከኢየሱስ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር ከተራመዱና ገናም በዛኛው መንገድ ጋር በመጓዝ ካሉ ምእመናን ጋር አንድ መሆኔን የምረዳበት ደረጃ ነው፣ ይህ ከጥምቀት ጋር የሚጀምረው አዲስ ሕይወት ከመላው የሕይወት ዘመኔ ጋር ይጓዛል፣ እምነቴን ከኢየሱስ ጋር በማደርገው የግል ውይይት ብቻ መመስረት ስለማልችልና ማዕበላዊ በሆነው ማኅበረሰባዊ ሱታፌ ብቻም መጓዝ ባልችልበት መንገድ በአማንያን ማኅበር ውስጥ ማለትም ቤተ ክርስትያን በምትባል ብዙ ኅብረ ቀለማት ባሉባት በዘለአለማዊ የእግዚአብሔር አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሱታፌ ባለው የቅድስት ሥላሴ ፍቅር የተመሠረተች በአማኙ ማኅበረ ክርስትያን አማካኝነት በሚሰጠኝ እምነት እሰጥማለሁ፣ እምነታችን የግል ነው ሆኖም ግን ይህ እውን የሚሆነው እምነቱ ማኅበራዊ በሆነ ቍጥር ነው ማለትም “እኛ” በሚለው የቤተክርስትያን የእምነት ትርጉም ጋር በሚተባበርበትና ይህ አንዲት በሆነች ቤተ ክርስትያን የሚመሰከረው እምነት የሚቀበል ማኅበራዊ እምነት ጋር የሚሳተፍ በሆነ ቍጥር ነው፣
እሁድ ዕለት በምናሳርገው መሥዋዕተ ቅዳሴ ዲያቆኑ ንበል ኩልነ በጥበበ እግዚብሔር ጸሎተ ሃይማኖት ብሎ ትእዛዝ በሚያቀርብበት ጊዜ እያንዳንዳችን በአካል ጸሎተ ሃይማኖት ስንደግም የቤተ ክርስትያን አንድያ እምነትን በማኅበር እንመሰክራለን፣ “እአምን በእግዚአብሔር አብ” ብለን እያንዳንዳችን በግል የምንመስከረው እምነት ግዜና ቦታ በማይወስነው በብዙ ቋንቋ የሚገለጠው የእምነት ምስክርነት ሱታፌአችን እንገልጣለን፣ አዲሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ በቍ.181 ይህንን የእምነት ምስክርነት የመላዋ ቤተ ክርስትያን ምስክርነት መሆኑን ያብራራርል፣ የቤተ ክርስትያን እምነት እምነታችንን ይቀድማል ይወልደዋል ይደግፈዋል እንዲሁም ይመግበዋል ይላል፣ ቤተ ክርስትያን የአማኞች ሁሉ እናት ናትም ይላል፣ ቅዱስ ሲፕሪያኖስ እንደሚለውም “ቤተ ክርስትያንን እንደ እናት ያልተቀበለ እግዚአብሔርን እንደ አባት ሊቀበል አይችልም” ይላል፣ ስለዚህ እምነት በቤተ ክርስትያን ውስጥ ይወለዳል በእርስዋም ወደ እርስዋ ይመራል፣ ይህ ነገር ማስታወስ ያለብን አስፈላጊ ነገር ነው፣
በሐዋርያት ሥራ (2፡1-13) እንደሚተረከው በመጀመርያዎቹ የቤተ ክርስትያን ዘመናት በጴንጠቆስጠ ቀን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ በኃይል በወረደበት ጊዜ፤ አዲስትዋ ቤተ ክርስትያን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጌታ የተሰጣትን ተልእኮ ለማሳካት ኃይል አገኘች፣ ይህም በሁሉም የምድር ዳርቻ የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ዜና የሆነውን ወንጌልን ለመስበክ፤ በዚህም እያንዳንዱ የሰው ልጅ ወድ ድኅነት ለሚያደርሰው እምነት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ለመምራት ነበር፣ ሐዋርያት የሰሙት ያዩትንና ከኢየሱስ ጋር በመኖር በአካል ያጣጣሙትን ለማውጅ ሁሉም ዓይነት ፍራቻ አሸንፈዋል፣ ምስክር ለመሆን የበቁትን ምሥጢር በግልጽ ለማወጅ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በአዲስ ቋንቋዎች መንገር ጀምረዋል፣ በሐዋርያት ሥራ ተያይዞ የሚተረከው በጴንጠቆስጠ ቀን ቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር ነው፣ እርሱ ከዮኤል ትንቢት በመጥቀስ ኢየሱስን በማመልከትና ኢየሱስ የክርስትና እምነት ማእከል መሆኑን በመግለጥ ይጀምራል (3፡1-5) ኢየሱስ ሁሉን ያዳነ እግዚአብሔር በተአምሮችና ታላላቅ ትእምርቶች የመሰከረለት ሲሆን በመስቀል ተቸንክሮ ተገደለ እግዚአብሔር ግን የሁሉ ጌታና አዳኝ በመሾም ከሙታን አነሣው፣ በነቢያት ስሙን የጠራ ሁሉ ይድናል ተብሎ የተነገረን እውን ሆኖ በኢየሱስ በወሳኙ ድኅነት ገብተናል (የሐ ሥ 2፤17-24) በማለት ይናገራል፣ እነኚህን የቅዱስ ጴጥሮስ ቃላት በሰሙ ጊዜ ብዙዎች ልባቸው ስለተነካ በሓጢአታቸው ተጸጸተው በመጠመቅ የመንፍስ ቅዱስ ስጦታዎች ተቀበሉ፣ (የሐሥ 2፡37-41)፣ የቤተ ክርስትያን ጉዞ እንዲህ ባለ ሁኔታ ይጀምራል፣ ይህንን የምሥራች በጊዜና በቦታ ይዛ የምታጓዝ ማኅበር ሆነች፣ ይህች ማኅበር ምስጋና ለኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይሁን በአዲስ ኪዳን የተመሠረተ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው፣ አባሎቿም የተለየ ማኅበራዊ ቡድን ወይም ወገን አይደሉም፣ ነገር ግን ከሁሉም አገሮችና ወገኖች የሚመጡ ወንዶችና ሴቶች ናቸው፣ ካቶሊካዊ ሕዝብ ነው፣ ማለትም በሰው ልጆች መካከል ያለውን ድንበር ሁሉ አውድሞና አለምንም ድንበር በኩላውነት ለሁሉም ክፍት የሆነና ሁሉንም የሚቀበል አዲስ ቋንቋ የሚያገር ማኅበር ነው፣ ቅዱስ ጳውሎት “በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።” (ቆላ 3፤11) ይላል፣
ስለዚህ ቤተ ክርስትያን ከመጀመርያ ጀምሮ የእምነት ቦታ ነው፤ የእምነት ማስተላለፊያ ቦታ ሆኖ በምሥጢረ ጥምቀት ከአባታችን አዳም ሓጢአት ነጻ በሚያደርገው ከኃጢአት እስር ቤት ነጻ በሚያወጣን እና የእግዚአብሔር ልጆች ነጻነት በመስጠት በሥሉስ ቅዱስ በሆነ እግዚአብሔር ጋር ሱታፌ በሚሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንሰጥማለን፣ በሌላ ብኩል ደግሞ ይህን በሚመስል አኳሃን ከግላዊ ብቸኝነት ወጥተን በእምነት ወንድሞቻችንና እኅቶቻቸን ከሆኑ ማኅበረ ክርስትያን ሱታፌ እንሰጥማለን ይህም መላው የክርስቶስ አካል ነው፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በሰንዶቹ “እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ለማዳንና ለመቅደስ የሚፈልገው በተናጠልና አለምንም መተሳሰር ሳይሆን በእውነት እርሱን በሚያውቅና በታማኝነት በሚያገለግለው አንድ ሕዝብ የሆነ ማኅበር ያቋቍም ይፍለጋል” ይላል፣ የምሥጢረ ጥምቀት ሥርዓተ አምልኮን እንደገና በመጥቀስ በዚሁ ሥርዓት ላይ ተጠማቂው መጥፎ ነገርን በመካድ የእምነት ዋና እውነተችን ደጋግመን “አምናለሁ” ባልን ጊዜ ሠራዔኢ ምሥጢሩ “እምነታችን ይህ ነው፣ የቤተ ክርስትያን እምነት ይህ ነው፣ እኛም ይህንን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን እምነት መመስከር ክብር ይሰጠናል” ይላል፣ እምነት መለኮታዊ ኃይል ነው ማለትም ከእግዚአብሔር የሚሰጠን ነው ሆኖም ግን የሚተላለፈው በቤተ ክርስትያን ነው ይህም ብታሪክ ሁሉ ነው፣ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮጦስ ሰዎች በጻፈው አንደኛ መልእክቱ (15፡3) “እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ” ሲል የተቀበለውን ወንጌል እንደሰጣቸው ይናገራል፣
በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ የቃለ እግዚአብሔር ስብከት የምሥጢራት ማደል ሥርዓተ አምልኮ እስከ ወደኛ የደረሰ ልማድ ወይም ባህል የምንለው ያልተቈራረጠ የሕይወት ሰንሰለት አለ፣ ቤተ ክርስትያን በዚህ ተግባር እኛ የምናምነው የኢየሱስ እውነተኛ መልእክቱ መሆኑና ሕዋርያት የሰበኩት መሆኑን ዋስትና ትሰጠናለች፣ የምስራቹ አንኳር የእምነት ውርሻችን ከእርሱ የሚፈልቀው የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ነው፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ቃለ እግዚአብሔር በሚለው ሰንድ (ቍ.8) ላይ “የሐዋርያት ስብከት ልዩ በሆነ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ አስተንፍሶ በተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠው እስከ የዓለም መጨረሻ አለማቋረጥ በተከታታይ መተላለፍ አለበት” ይላል፣ በዚሁ መንገድ ቅዱስ መጽሐፍ ቃለ እግዚአብሔር የያዘ ከሆነ የቤተ ክርስትያን ልማድ ወይም ባህል ደግሞ ይህንን ይጠብቀዋል በታማኝነትም ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፈዋል፣ ምክንያቱም የሁሉ ዘመን ሰዎች ከዚሁ ወደር የለሽ ሃብት እንዲሳተፉና የጸጋ መዝገቦቹን ለማካበት እንዲችሉ ዘንድ ይረዳልና፣ እንዲህ ባለ ሁኔታም የቫቲካን ጉባኤ ሰነድን እንደገና በመጥቀስ “ቤተ ክርስትያን በአንቀጸ እምነትዋ በሕይወትዋና በሥርዓተ አምልኮዋ ለሁሉም ትውልድ እርሷ የምታምነውን ያላትንና የሆነችውን ታወርሳለች” ይላል፣
በመጨረሻ ለማስመር የምወደው፤ የግል እምነታችን የሚያድገውና የሚበስለው በማኅበረ ቤተ ክርስትያን ነው፣ በአዲስ ኪዳን “ቅዱሳን” የሚለው ቃል ክርስትያኖችን በአጠቃላይ የሚያመለክት ሲሆን ሁላቸው ክርስትያኖች ደግሞ ይህንን ሊወክሉ በአጠቃላይ ቅዱሳን እንዳልነበሩ እውነት ቢሆንም ይህንን ቃል ብንመለከተው አስፈላጊ ነው፣ በዚሁ ቅዱሳን የሚል ቃል ምን ለማመልከት ፈልጎ ነው፧ በክርስቶስ እምነት የነበራቸውና ከሞት በተነሣ ክርስቶስ እምነት የሚኖሩ ሁላቸው ለሌሎች ሕያው ምሳሌ ለመሆን የተጠሩ መሆናቸውን ለማመልከት ነው፣ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ የሕያው እግዚአብሔር ገጽታን ከሚገልጠው ከክርስቶስና ከመልእክቱ ጋር ጥብቅ ግኑኝነት በማድረግ ነበር፣ ይህ ጥሪ ለእኛም ይመለከታል፣ ቀስ በቀስ በቤተ ክርስትያን እምነት ሊመራና ሊነቃቃ የሚፈቅድ ክርስትያን ደካማነት ቢኖረውም የተወሰነ ቢሆንም ችግሮች ቢኖሩትም የእግዚአብሔር ብርሃን ተቅብሎ ለዓለም የሚያስተላልፍ ለእግዚአብሔር ብርሃን ክፍት የሆነ መስኮት ይሆናል፣ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ረደምቶሪስ ሚስዮ በሚለው ሓዋርያዊ መልእክታቸው “የቤተ ክርስትያን ተልእኮ ቤተ ክርስትያንን ያሳድሳል የክርስትያን እምነትንና ማንነትን አዲስ ኃይል ይሰጣል አዲስ ስሜትና መነሳሳትንም ይሰጣል፣ እምነት በመስጠት ትበረታለች” ይላል፣
ባለነው ዘመን እምነትን በግል ብቻ መወሰን ባህርይዋን ይቋወማል፣ የእምነት ጽናት እንዲኖረንና የእግዚአብሔር ስጦታዎች የሆኑትን ቃሉ ምሥጢራቱ የጸጋ ስጦታ የፍቅር ምስክርትን ለማጣጣም ቤተ ክርስትያን ታስፈልገናለች፣ እንዲህ ባለመንገድ “እኔ” የሚለው “እኛ” በሚለው ቤተ ክርስትያን መስጠም አለበት፣ ይህ የቤተ ክርስትያን “እኛ” ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሱታፌ በመጣጣም ይህ ሱታፌ በሰው ልጆች መካከል እንዲፈጸም ይረዳል፣ ባለነው ዘመን ግላዊነት እንደ ደንብ በሚታየው ጊዜ እምነታችን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንድንሆን ይጠራናል፣ በዚህም ቤተ ክርስትያንን አቁመን ለሁሉም የሰው ዘር የፍቅርና ከእግዚአብሔር ጋር ሱታፌ ማምጣት እንችላለን፣









All the contents on this site are copyrighted ©.