2012-02-27 18:52:37

3 ሰንበት ዘአስተምህሮ (ዘምኵራብ) ኅዳር 24 2004 ዓ.ም. (12/4/2011)


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና በብፁዓን አዲስ ካርዲናሎች ተሸኝተው በመንበረ ጴጥሮስ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲልካ ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ ባደረጉት ስብከትና እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሰጡት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ “ዛሬ ዓለማችን በገዛ ራስዋ ተዘግታ በምትገኝበት ግዜ ቤተ ክርስትያን የእውነትና የፍቅር ተልእኮ የሆነውን የክርስቶስ ብርሃን ለሁሉም ለማድረስ የተጠራች” መሆንዋን አስምረውበታል፣ አያይዘውም ስለ መንበረ ጴጥሮስ መሪነትና ቀዳምነት በሰፊው ገልጠዋል። በመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮም ቤተ ክርስትያንና ተቀዳሚ ተባባሪዎችዋ ይህን ተልእኮ ለመዋጣት የጸሎት ድጋፍ እጅጉን ስለሚያስፈልጋት ሁላችን በጸሎት እንድንደግፋት ተማጥነዋል።።
ቅዱስነታቸው ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ ሥልጣንና ማንነት ሲያተምሩ፣ “ቅዱስ ጴጥሮስ በክርስቶስ አደራ የተሰጠችውን ቤተ ክርስትያን በሥጋና በደም ሊደግፋትና ሊያራምዳት ባልቻለም ነበር፣ ለዚህም ነው፣ እግዚአብሔር ጴጥሮስ ያልሆነውን እንዲሆን ፈቃዱ ስለሆነ ጴጥሮስን “አለት” እንዲሆን ቤተ ክርስትያኑን በእርሱ ላይ እንድትመሠረት አደረገ፣ ምክንያቱም ያኔ ለተወለደችው አዲስ ቤተ ክርስትያን የዚህ ዓይነት ጽናት ያስፈልጋት ነበርና”፣ ሲሉ እግዚአብሔር ድካማችንን እንዴት እንደሚያበረታ ከገለጡ በኋላ ለብፁዓን አዲስ ካርዲናሎች ደግሞ የተሰጣቸው ኃላፊነት ለአገልግሎት እንጂ ለክብርና ሥልጣን አለመሆኑን አሳስበው፣ ለቤተ ክርስትያናችን ለሁለት ሺ ዓመታት ያኖራት ደግሞ ይህ አገልግሎት ስለሆነ አዲስ ካርዲናሎች እምነትና ፍቅርን ለመመስከር አንደኛ የመሆን ግዴታ እንዳለባቸው ገልጠዋል፣
በቅዳሴ ስብከት መሃከል ብፁዓን አዲስ ካርድናሎችን ወክለው ብፁዕ ካርዲናል ፈርዲናንዶ ፊሎኒ የስብከተ ወንጌል ማኅበር ኃላፊ ለቅዱስነታቸው ቃለ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ፣ ቅዱስነታቸው የመንበረ ጴጥሮስ መንበረታቦትና የተለያዩ የጥበብ ሥራዎች እንደምሳሌ በመጠቀም ሁሉ በአንድነት የጴጥሮስ ሥልጣናዊ ትምህርትና የቤተ ክርስትያን ሁለመናዊ ምንነት እንደሚያንጸባርቁ አመልክተዋል፣ ከመንበረ ታቦቱ በላይ የሚገኘውን መስኮት በማመልከት እዛ ላይ በእርግብ ሥእል የሚመንጨው ብርሃን እግዚአብሔር የብርሃን ምንጭ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጠዋል፣
ቤተ ክርስትያን ገዛ ራስዋ እንደ መስኮት ናት፣ እግዚአብሔርን ወደ እኛ የሚያቀርብና ከዓለማችን ጋር የሚገናኝበት ሥፍራ ነው፣ ቤተ ክርስትያን የምትኖረው ለገዛ ራስዋ አይደለም፣ መድረሻ ነጥብም አይደለችም፣ ከእርስዋ ወዲያና ከእርስዋ በላይ ወደ ሆነው ወደ ከፍተኛ፣ ከእኛ በላይ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ታመልክታለች፣ ገዛ ራስዋን ሳይሆን እግዚአብሔርን ያንጸባረቀች እንደሆነ እውነተኛ ማንነትዋ ጎልቶና በርቶ ይታያል፣ ምክንያቱም ከእርሱ ስለመጣችን ወደ እርሱ ስለምትመራ መነሻዋና መድረሻዋ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው፣
ቅዱስነታቸው የጠቀሱት ሌላ የሥነ ጥበብ ሥራ የታላላቅ የቤተ ክርስትያን አበው ሓውልቶች የሚመለከት ነበር፣ የምሥራቃዊት ቤተ ክርስትያን ታላላቅ አስተማሪዎች ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲሁም የላቲን ቤተ ክርስትያን ታላላቅ አስተማሪዎች ቅዱስ አምብሮዝዮስና ቅዱስ አጎስጢኖስ የቤተ ክርስትያን መዝገበ አሚን ምሉነት እንደሚያመልክቱ በዚህም የአንዲት እምነትና የአንዲት ቤተ ክርስትያን ሃብት መግለጫ ነው፣ ብለዋል፣
እነኚህ የመንበረ ታቦት ምልክቶች የሚያስተምሩት ፍቅር በእምነት እንደሚደገፍ ነው፣ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ካላመነና ለእርሱ ያልታዘዘ እንደሆነ ፍቅር ተንዶ ይፈረካከሳል፣ በቤተ ክርስትያን ሁሉም ነገር በእምነት ይደገፋል፣ ቅዱሳት ምሥጢራት ሥርዓተ አምልኮ ስብከተ ወንጌልና ግብረ ሠናይ ሁሉ በእምነት ይደገፋሉ፣ ሕገ ቀኖናም ይሁን በቤተ ክርስትያን ያለው ሥልጣንም ሳይቀር ሁሉ በእምነት ይደገፋል፣ ቤተ ክርስትያን ለገዛ ራስዋ ትእዛዝ አትሰጥም ነገር ከእግዚአብሔር ቃል ትቀበለዋለች፣ ይህንን ቃል በእምነት አዳምጣ ልትረዳው ትጥራለች በእርሱም ትኖራለች፣ ቅዱስ እግናጽዮስ ዘአንጾክያ ሮማዊት ቤተ ክርስትያንን ሲገልጽ፣ “ሠራዒተ ፍቅር ማለት በፍቅር የምትመራ” ብሎ ይጠራት ነበር፣ ቅዱስነታቸው የዚህ ፍቅር ትርጓሜ ሲያስተምሩ “ይህ ፍቅር እንደ ፍቅር ብቻ አይደለም የሚተረጐመው የክርስቶስ የፍቅር ምሥጢር የሆነው ቅዱስ ቍርባንንም ያመለክታል” ብለዋል፣
ስለዚህ በፍቅር መምራት ማለት የሰው ልጆችን በቅዱስ ቁርባን ማእድ የክርስቶስ ማእድ ማንኛውም ድንበርና እንግዳነት ባሻገር ከብዙ ልዩነቶች ውኅደት ሱታፌና አንድነት ይፈጥራል፣ የመንበረ ጴጥሮስ ተልእኮ እንታድያ በፍቅር ቀዳሚ መሆን በፍቅር መምራት በቅዱስ ቁርባን ወይንም የኩላዊት የክርስቶስ ቤተ ክርስትያንን ለአንድነት መጥራት ነው፣
ሌላ ምልክት ደግሞ በመንበረታቦቱ የሚታየው የመውርድና የመውጣት ምልክቶች ናቸው፣ እነኚህ ምልክቶች በፍቅርና በእምነት መካከል ያለውን መደጋገፍ ያመልክታሉ፣ እምነት ፍቅርን አቅጣጫ ያስይዘዋል፣
በግል ጥቅም የተገዛ እምነት እውነተኛ እምነት ሊሆን አይችልም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምንና በፍቅር ማእድ በሆነው ምሥጢረ ቅዱስ ቍርባን የሚሳተፍ ሁሉ ምንጩን ያገኛል እውነተኛ ደስታን ያጣጥማል በልግሥና መንገድ እየተመላለሰም ይኖራል፣ ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣
የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ባቀረቡት አስተምህሮም፣ የመንበረ ጴጥሮስ በዓልን አስመልክተው ካስተማሩ በኋላ ቤተ ክርስትያንን የመምራት ኃላፊነት በካርዲናሎች እየተረዳ የሮማዊ ጳጳስ መሆኑን ገልጠዋል፣ይህ ልዩ የአገልግሎት ኃላፊነት ለሮማዊት ቤተክርትስያንና ለጳጳስዋ የተሰጠበት ዋና ምክንያት በዚህ ከተማ ከሌሎች ብዙ ሰማዕታት ጋር ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ ደማቸውን ስላፈሰሱ ነው፣ በዚህም ወደ የደምና የፍቅር ምስክርነት እንመለሳለን፣ ስለዚህ መንበረ ጴጥሮስ የኃላፊነት ምልክት ነው፣ ነገር ግን ይህ ሥልጣን በእምነትና በፍቅር የተመሠረተው የክርስቶስ ሥልጣን ነው፣ በማለት ካስተማሩ ከምእመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳረጉ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታ አቅርበውም መልካም እሁድ በመመኘት ሐዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል፣







All the contents on this site are copyrighted ©.