2012-01-27 13:36:12

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ.፦ “ኢፍትኃዊነት ጥላቻ እና ቀቢጸ ተስፋ ባለበት ሁሉ ሥፍራ ተስፋ አድርሱ”


ከትላንትና በስትያ ሮማ ፎሪ ለ ሙራ ክልል በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ባሲሊካ ቅዱስ አባታችን እ.ኤ.አ. ጥር 25 ቀን በሚከበረው ዓመታዊ የቅዱስ ጳውሎስ መለወጥ በዓል ምክንያት በመሩት ሁለተኛ ጸሎተ ሰርክ እና ባሰሙት ሥልጣናዊ አስተምህሮ አማካኝነት የክርስትያን አንድነት የጸሎት ሳምንት RealAudioMP3 መጠናቀቁ የቅድስት መንበር መግለጫ አመለከተ።
የ 2012 ዓ.ም. የክርስትያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት መሪ ቃል “ሁሉም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል መሠረት ይለወጣሉ” የሚል መሆኑ የሚዘከር ሲሆን፣ “በክርስቶስ ኅብረት አማካኝነት የእርሱ በሆነው ተልእኮ ለመሳተፍ ተጠርተናል፣ ይኽ ማለትም ኢፍትኃዊነት ቀቢጸ ተስፋነት እና ጥላቻ በነገሠበት ሥፍራ ተስፋን ማድረስ ማለት መሆኑ ቅዱስ አባታችን ባሰሙት ሥልጣናዊ አስተምህሮ ገልጠው”፣ ይኽ የክርስትያኖች የተሟላ ውህደት ላይ እይታውን ያኖረው የቅዱስ አባታችን አስተምህሮ፣ ር.ሊ.ጳ. ብፁዕ ዮሐንስ 23ኛ በዚህ በቅዱስ ጳውሎስ ባሲሊካ እ.ኤ.አ. ጥር 25 ቀን 1959 ዓ.ም. የቅዱስ ጳውሎስ መለወጥ በዓል ምክንያት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ጅማሬ ያወጁበት 50ኛው ዓመት ያስታወሰም ሲሆን፣ “የሁሉም ተመክሮ የሆነው በዚህ በምንኖርበት ዘመን የሚታየው የክርስትያኖች መከፋፈል በሚያስከትለው ሥቃይ ሳንታጠር ክርስትያኖች የክርስቶስ ድል የሚሰጠው የሕይወት ሙላት ከእርሱ ጋር እና ከሌሎች ጋር ተካፋዮች የሚያደርገን በመሆኑ በዚህ ታምነን፣ መጻኢ በተስፋ እንመለከት ዘንድ አደራ ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የእግዚአብሔር ቸርነት በክፋት ላይ ድል አድራጊነቱን ያረጋግጥልናል። እርሱ መላውን ሰው ዘር እና በጠቅላላ የግዚአብሔር ፍጥረት የሚያወድም አፍራሽ ኃይል የሆነው ኃጢአት ለመዋጋት በምናደርገው ትግል ይሸኘናል፦ የተነሣው ክርስቶስ ኅላዌ እኛን ክርስትያኖች ለመልካም ዓላማ በጋራ እንድንሠራ ይጠራናል። በክርስቶስ ተዋህደን ኢፍትኃዊነት ጥላቻ እና ቀቢጸ ተስፋ በነገሠበት ሥፍራ ሁሉ ተስፋን ማድረስ በሚለው በእርሱ ተልእኮ እንድንካፈል ተጠርተናንል። መከፋፈላችን ስለ ክርስቶስ የምንሰጠው ምስክርነት ያለው ቦግታ ያደበዝዛል። በተስፈኛ ጥረት እና በተማመነ ጸሎት አማካኝነት የምንጠባበቀው ሙሉ ውህደት ፍጻሜ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ሳይሆን ለመላ ሰው ዘር ቤተሰብ የላቀና እጅግ አስፈላጊ ዓላማ ነው” እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።
“የመጨረሻው ድል እኛ በሙሉ ተስፋ የምንጠባበቀው በጌታችን ሁለተኛው ምጽአት የሚጨበጥ ነው፣ ስለዚህ የምንጠባበቀው ተጨባጭ የቤተ ክርስትያን አንድነት/ውህደት ታጋሽ እና የተማመነ መሆን አለበት፣ በዚህ ቅድመ አኳኋን ብቻ ነው ስለ ክርስትያኖች አንድነት የምናደረገው ዕለታዊ ጸሎት እና ጥረት ሙሉ ትርጉም የሚኖረው። በትዕግሥት የመጠባበቁ ተግባር፣ ተካፋይነት አልቦ ሆኖ እጅን አጣምሮና እጅን ሰጥቶ መጠበቅ ማለት ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ለሚሰጠው የአንድነት ጸጋ የተገባ መልስ ለመስጠት ልባምና ዝግጁ መሆን ማለት ነው” ብለዋል።
“ቅዱስ ጳውሎስ በኅልውናው ያጣጣመው፣ ተመክሮ ያደረገበት መለወጥ በሥነ ምግባር ደረጃ የሚታጠር እርሱም ከኢግብረ ገባዊነት ተግባር ወደ ግብረ ገባዊነት ተግባር መለወጥ ወይንም በእውቀት ደረጃ እርሱም ተጨባጩ ጉዳይ ለመገንዘብ የምትከተለው የአመለካከት ዘይቤ መለወጥ ማለት ሳይሆን የመሆናዊ ሥር ነቀላዊ ተኃድሶ የሚለውን ዳግም መወለድ ጋር የተጣመረ ለውጥ የሚያመለክት ነው። የዚህ ዓይነቱ ለውጥ መሠረት፣ ከክርስቶስ ጋር ደረጃ በደረጃ በሚጸናው ጉዞ ሥር የሚገለጥና በሞት እና በትንሣኤ ምሥጢር ሱታፌ ነው” ካሉ በኋላ አክለውም “ስለ ክርስቶስ ኃዋርያት አንድነት ጸጋ ስንለምን ያ በሥቃዩና በሞቱ ዋዜማ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ‘እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ’ ሲል የገለጠው ጥልቅ ፍላጎት የገዛ እራሳችን ፍላጎት እናደርጋለን ማለት ነው” ብለዋል። ስለዚህ ስለ ክርስትያኖች አድነት የሚደረገው ጸሎት ለቤተ ክርስትያን በሆነው መለኮታዊው እቅድ መሳተፍ ማለት” ነው፣ የቤተ ክርስትያን ውህደት ዳግም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ታታሪ መሆን ግዴታ እና የሁሉም ትልቅ ኃላፊነት ነው” በማለት ያሰሙት ሥልጣናዊ አስተምህሮ እንዳጠቃለሉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።







All the contents on this site are copyrighted ©.