2012-01-06 12:12:39

በዓለ ግልጸት (አስተርእዮ ለእግዚእነ)


የላቲን ሥርዓት የምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ዛሬ እ.ኤ.አ. ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በዓለ አስተርእዮ ለእግዚእነ የክርስቶስ መለኮታዊነት ግልጸት አክብራ ውላለች። ይህ በዓል ጠቢባን ወይንም የከዋክብት ተመራማሪዎች በምሥራቅ ባዩት ኮከብ ተመርተው ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ሥፍራ RealAudioMP3 በመሄድ ስግደት እና ገጸ በረከት በማቅረብ ያሳዩት ጥልቅ መንፈሳዊነት የሚከበርበት ሲሆን፣ በዓሉን ምክንያትም ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ መሥዋዕተ ቅዳሴ መምራታቸው የቅድስት መንበር መግለጫ ሲጠቁም፣ የአጎስጢኖሳውያን ገዳማውያን ማኅበር ጠቅላይ አለቃ አባ ጋብሪኤለ ፈርሊሲ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለመላ ሰው ዘር ድህነት የመጣ መሆኑና ሁሉም አሕዛብ በዚያ በተለወለደው ሕፃን ኢየሱስ የተገለጠው ፍጹም ሰው ይፋዊ እወቅና የሚሰጥበት ዕለት ነው። “ጠቢባኑ (የከዋክብት ተመራማሪዎች) ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፣ ወድቀውም ሰገዱለት፣ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት፣ ወርቅ የኢየሱስ ክቡርነት፣ ዕጣኑ መለኮታዊነቱን፣ ከርቤውም ስብአዊነቱን፣ ቃል ሥጋ ሆነ የሚለው ግልጸት የሚወክል መሆኑ አብራርተው፣ ቅዱስ አጎስጢኖስ በዚህ በዓል ምክንያት፣ የከዋክብት ተመራማሪዎቹ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ (ማቴ. 2፣ 2) የሚለው ወንጌላዊ ቃል መሠረት በማድረግ፣ ጠቢባኑ ‘ያበሥራሉ፣ ይጠይቃሉ ያምናሉ ይፈልጋሉም’ እነዚህ ቃላቶች በእምነት ጎዳና ለሚደረገው ጉዞ ትእምርትና ራዕይ መሻት ወሳኝ መሆኑ ያመለክታሉ ሲል የሰጠው ማብራሪያ ጠቅሰው፣ ስለዚህ በተወለደው ሕፃን ዘንድ የሚገለጠው ሰብአዊነት ብቻ ሳይሆን መለኮታዊነትነት ጭምር በማወቅ እና በማጤን መንፈሳዊነት ማደግ ይኖርብናል። ዛሬ እየጠፋ በመሄድ ላይ ያለው የእምነት ጥልቅ አድማስ ዳግም መጎናጸፍና ማግኘት ይኖርብናል። ዕለት በዕለት በቀጣይነት የሚገለጠውን የክርስቶስ መለኮታዊነት መለየት አለብን። በቤተልሔም በሚወለደው ሕፃን በዓለም የእግዚአብሔር ተግባር ለማየት የሚያበቃውን እምነት መሻት እና መኖር ይጠበቅብናል።
ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በዚህ በተገባው አዲስ ዓመት (እ.ኤ.አ. 2012 ዓ.ም.) ጥቅምት ወር እንዲካሄድ የወሰኑት ዳግመ አስፍሆተ ወንጌል ማእከል ያደረገው የኵላዊት ቤተ ክርስታያን ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ በአዲስ አስፍሆተ ወንጌል አማካኝነት የወንጌል ብሥራትና የእምነት ኅያውነት እንዲኖር የሚያነቃቃ ነው። በዚህ ክርስትናውን በዘልማድና በውጫዊ ገጽታው ብቻ በሚኖረው ክርስትያን ዘንድ አስፍሆተ ወንጌል በአዲስ መንፈስ ማነቃቃት የማያሻማ የቤተ ክርስታያን ተልእኮ መሆኑ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በመለየት፣ ለዚህ ዓላማ ቤተ ክርስትያንን እያነቃቁ ይገኛሉ። ብሥራተ ወንጌል ዳግም መንፈሳዊነት በተጎናጸፈ ሕይወት እና ቃል አማካኝነት ለማበሰር የተጠራን መሆናችን በዓለ አስተርእዮ ለእግዚእነ የሚያቀርበው ጥሪ ነው በማለት የሰጡትን ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.