2011-12-12 13:27:37

ብፁዕ ካርዲናል በርቶነ፦ ቁጠባ ፖሊቲካ ዕደ ጥበብ ከሥነ ምግባር ጋር ማጣመር


የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ ብፁዕ ካርዲናል ታርቺዚዮ በርቶነ ቅዳሜ ጧት በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ የኵላዊት ቤተ ክርትያን የማኅበራዊ ጉዳይ ትምህርተ አንቀጸ ሃይማኖት መሠረት በማድረግ አገልግሎት የሚሰጡ የኢጣሊያ የትብብር ማኅበራት ፈደረሽን እና የኢጣሊያ አበዳሪ ባንክ ቤቶች ኅብረት RealAudioMP3 ፈደረሽን አባላት እና የኢጣሊያ የባህል ጉዳይ ሚኒ. ሎረንዞ አርናጊ የተሳተፉበት መሥዋዕተ ቅዳሴ አቅርበው ባሰሙት ስብከት፣ የካቶሊክ ቤተ ክርትያን የአንቀጸ ሃይማኖት ክፍል የሆነው የማኅበራዊ ጉዳይ ትምህርት መሠረት በማኅበራዊ ጉዳይ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበሮች መቼም ቢሆን ትምህርቱ ያለው ክብር ሳይዘነጉ በሁሉም መስክ በማካተት ገቢራዊ ያደርጉ ዘንድ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ማኅበራዊ ጉዳይ ትምህርት በባህርዩ ኩላዊ ነው ብለዋል።
በኢጣሊያ በ 270 ከተሞች በ 101 አውራጃዎች እና በ 550 አነስተኛ ከተሞች በጠቅላላ 4 ሺሕ 400 ከአካባቢ እና ነዋሪዎች ሁኔታ ጋር ጥብቅ ግኑኝነት ያላቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የማኅበራዊ ጉዳይ ትምህርት መርህ በማድረግ አገልግሎት የሚሰጥ አበዳሪ ባንክ ቤቶች እንዳሉ ሲገለጥ፣ እነዚህ ባንክ ቤቶች ከ 80 ቁምሳናዎች ጋር በመተባበር የኤኮኖሚ ችግር ላለባቸው ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚያቀርቡም ሲታወቅ፣ በተለይ ደግሞ በዚህ በአሁኑ ወቅት የኤኮኖሚ እና የቁጠባ ቀውስ በስፋ በሚታይበት፣ እነዚህ ባንክ ቤቶች በኤኮኖሚ ችግር ለሚጠቁት ዜጎች ከቤተ ክርስትያን የትብብር እና የድጋፍ ተቋሞች ጋር በመተባበር የሚያቀርቡት እገዛ የሚመሰገን መሆኑ ብፁዕ ካርዲናል በርቶኔ ባቀረቡት ስብከት አስታውሰው፣ ይህ ሰብአዊነት ግብረ ገባዊ እና መንፈሳዊ ጠባይ ያለው በመሆኑም የሁሉም ክርስትያን የማያወላውል ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ቁጠባ ኤኮኖሚ ፖሊቲካ ዕደ ጥበብ ከሥነ ምግባር ጋር የማያሻማ ጥምረት ሊኖራቸው ይገባል። የኅብረተሰብ የአገር የሁሉም ዜጎች የጋራው ጥቅም ለማረጋገጥ ሥነ ምግባር መሠረት ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ኤኮኖሚ ቅን እና አሳቢ መተባበር እና መደጋገፍ የተካነ እንዲሆን በሥነ ምግባር የተመራ መሆን አለበት ብለዋል።
እነዚህ የኵላዊት ቤተ ክርስትያን የማኅበራዊ ጉዳይ ትምህርት መሠረት የተቋቋሙት የትብብር እና የድጋፍ ማኅበራት እንዲሁም አበዳሪ ባንክ ቤቶች ተጠሪዎች እና ሠራተኞች ያለባቸው ኃላፊነት ግምት በመስጠት እና የቤተ ክርስትያን የማኅበራዊ ጉዳት ትምህርት የሚከተሉ በመሆናቸውም ሙያዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕንጸት ያስፈልጋቸዋል ካሉ በኋላ፣ ከጥንት ጀምሮ እነዚህ ባንክ ቤቶች እና የትብብር ድርጅቶች ማኅበራዊ ኤኮኖሚ ሃሳብ በጥልቀት የተረዱ በመሆናቸውም ለድኾች የሚሰጡት ድጋፍ የወጣት የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ የማግኘት ዕድል ከፍ እንዲል የሚያቀርቡት የባህል እና የሕንጸት ድጋፍ መቼም ቢሆን እንዳይዘነጉት አደራ ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል በርቶነ፣ እነዚህ አበዳሪ ባንክ ቤቶች እና የትብብር እና የድጋፍ ማኅበራት ማኅበራዊነት የሚከተሉ፣ የሰው ልጅ ሰብአዊነት ማእከል በማድረግ እና ለሰብአዊው ክብር አቢይ ግምት የሚሰጡም ናቸው። ማኅበራዊ የትብብር ግብረ ገብ የድርጅቶች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአባላቱ ጭምር መሆኑ እንዳይዘነጋ አደራ በማለት ያቀረቡት ስብከት እንዳጠቃለሉ የቅድስት መንበር መገልጫ አስታወቀ።







All the contents on this site are copyrighted ©.