2011-02-19 11:45:41

የር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ ኣስተምህሮ(13.02.2011)


ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ የዕለቱ ቃለ ወንጌል በተመለከተ እንዳተስተማሩና በአደባባዩ ከተገኙ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናንና ነጋዳያን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማሳረጋቸው ተመለከተ።

ቅዱስነታቸው ባለፈው ሳምንት በሮማ ከተማ ኣከባቢ ሮም በሚል ስም የሚታወቁ ዘላን ጂፕሲዎች 4 ሕፃናት መሞታቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው፣ ወንድማማችነትና መተጋገዝ የተሞላበት ማኅበረሰብ ቢኖር ኖሮ ይህ ዘግናኝ ፍጻሜ ሊገታ ይችል ነበር ሲሉ ማኅበረሰቡ እነዚህን ሰዎች መቀበል መንከባከብና ተገቢ የኒሮ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ኣሳስበዋል።

በላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ ግፅው ትናንትና እሁድ የተነበበው ወንጌል የማቴዎስ ምዕራፍ 5 ነው። ጌታ በዚሁ ስብከት ኣዲስ ሕግ ማወጁን ይነግረናል። ኢየሱስ ኦሪትን ሙላት ለመስጠት እንጂ እንዲሽረው እንዳልመጣ ‘እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።  እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።’ በማለት ይገልጣል። እንዲሁም ለሐዋርያቱ ጽድቃቸው ከፈሪሳውያንና ከጸሐፊዎች ጽድቅ ያልበለጠ እንደሆነ በመንግሥተ ሰማያት እንደማይገቡ ያስተነቅቃቸዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን ጥቅስ በመመርኮስ ክርስቶስ የሚሰጠው ፍጽምና በምን ላይ የቆመ ነው፣ ከፈሪሳውያንና ጸሓፊዎች ጽድቅ በላይ የሚያስፈልገውስ ምን ይሆን በማለት ጠይቀው የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል። ኢየሱስ ይህን ሁኔታ ኣከታትሎ በሚያቀርባቸው በጥንታዊ ትእዛዞችና እርሱ ባቀረባቸው ኣዳዲስ ትእዛዞችን በማነጻጸር ያቀርበዋል፣ ኣዲስ ዓረፍተ ነገር በሚጀምርበት ግዜ ‘ለቀደሙት። እንዲህ ኣታድርጉ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤..’ ካለ በኋላ ‘እኔ ግን እንዲህ እላችዋለሁ..’ በማለት ኣሳደሰው፣ ለምሳሌ ያህል ‘ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።’ (ማቴ 5,21-22)

በዚህ ኣኳሃን ስድስት ግዜ ያህል ይናገራል። ይህ ዓይነት ንግግር ለሕዝቡ ኣስደንጋጭ ነበር፣ ምክንያቱም እኔ ግን እላችኋለሁ የሚለው ኣነጋገር ልክ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ሲናገር የነበረው የሕግ ምንጭ የሆነ የእግዚአብሔር ሥልጣን ነበረው። ኢየሱስ ያመጣው መታደስ እርሱ ራሱ ትእዛዛቱን በእግዚአብሔር ፍቅር በመፈጸም በእርሱ ላይ በሚርኖረው መንፈስ ቅዱስ ኃይል በማሳደሱ ነው። እኛም በክርስቶስ ባለን እምነት መለኮታዊው ፍቅርን ለማጣጣም የሚያስችለን የመንፈስ ቅዱስ የመታደስ ኃይል ለማግኘት ልባችንን ለመክፈት እንችላለን፣ በዚህም እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ትእዛዝ የፍቅር ምንጭ ይሆናል፣ ሁሉም ትእዛዛት ፍቅር በሚለው በኣንድ ቃል ይተሳሰራል፣ እግዚአብሔር ኣምላክህን በሙሉ ልብህ ኣፍቅር ጓደኛህን እንደ ገዛ ራስህ ውደድ፣ በሚለው ሙሉ ሐሳብም ሊጠቀለል ይችላል፣ የቅዱስ ጳውሎስን ቃላት ያስታወስን እንደሆነ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ‘የሕግ ፍጽምና ፍቅር ነው’ የሚለው ይህንን ያመለክታል።

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሳለን ባለፈው ሳምንት በሮማ ከተማ ኣከባቢ በኣሳዛኝና ኣሰቃቂ ሁኔታ በቤታቸው የተቃጠሉ የአራቱ ሕፃናት ሞት ወደ ኅሊናችን ተመልሰን ወንድማማችነትና መተባበር ያለበት ማኅበረሰብ ቢኖር ኖሮ በእውነት በክርስትናና በፍቅር የሚኖር ማኅበረሰብ ቢኖር ኖሮ ይህ ድራማ ሊወግድ ይችል ነበር። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በየአከባቢው በየዕለቱ ለሚወርዱ ሌሎች ችግሮችም ሊጠየቅ ይችላል፣ ራሱ ፍቅርና የፍቅር ምንጭ የሆነው ጌታ የመጀመርያውን ስብከት በተራራ ላይ ሆነ የሰበከው ያጋጣሚ ነገር ኣይደለም፣ በኦሪት እግዚአብሔር ለሙሴ ትእዛዛቱን እንዲሰጠው በደብረ ሲና እንዲወጣ እንዳዘዘው ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ኣንድያ ልጅ የሆነ ኢየሱስ ራሱ ከሰማየ ሰማያት በፍቅር መንገድ ወርዶ እኛን ወደ ሰማይ ሊያወጣ መጣ፣ እርሱ ራሱ እውነተኛ መንገድ ስለሆነ እርሱን ከመከተል ሌላ የምናደርገው ነገር የለም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸምና በዘለዓለማዊ ሕይወት የሆነው መንግሥቱ እንድንገባ እርሱን እንከተል። በዚህ ረገድ በተራራው ጫፍ ላይ የደረሰች ፍጥረት ብትኖር እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ለዚህም የበቃችበት ከኢየሱስ በነበራት ፍጹም ኣንድነት ነው፣ ይህ ኣንድነት ጽድቅዋ ፍጹም እንዲሆን ኣደረገው፣ እኛንም በክርስቶስ ፍቅር እንድራመድ እንድትመራን ዘንድ እንማጠናት’ በማለት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ኣሳርገዋል። በመጨረሻም ጌታ የሰጠንን ፍቅር በዕለታዊ ኑሮኣችን በተግባር እንድንኖረው በማሳሳሰብ ምእመናኑን በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነው ሐዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት ትምህርታቸው ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.