2010-11-25 12:23:17

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ (24.11.10)


የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ቁጥር 28 “ሸክማችሁ የከበደባችሁ እናንተ ደካሞች ሁሉ ወደ እኔ ኑ! እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን በጫንቃችሁ ተሸከሙ፡ ከእኔም ተማሩ፡ እኔ የዋህና ትሁት ነኝ ፡ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ነው ሸክሜም ቀላል ነው።”

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፥ ዛሬ በቤተክርስቲያን ታሪክ ታላቅ አበርክቶ ስላደረገች አንዲት ሴት ልጅ መናገር እወዳለሁ፡ ስለ ቅድስት ካተሪና ዘስየና እናገራለሁ። እርሷ ትኖር የነበረችው በ14ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ያኔ በኢጣልያና በመላው ኤውሮጳ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ተከፋፍላ ነበር። ሆናም ግን እግዚአብሔር በችግርና በከባድም ጊዜም ይሁን ሕዝቡን ሁሉግዜ ይባርካል። ቅዱሳንና ቅዱሳትን እየላከ የሕዝቡን ልብ በመንካት ለንስሓና ለተሃድሶ ይጠራቸዋል።

ቅድስት ካተሪና ከእነዚህ ቁዱሳን መካከል አንዷ ናት። ዛሬም ቢሆን ሁላችንንም በጀግንነትና በብርታት ለቅድስና ሕይወት እንድንታገልና ሙላት ባለበት መንገድ የጌታ ሐዋርያት እንድንሆን አደራ ትለናለች።

ቅድስት ካተሪና በ1347 ዓ.ም. በስየና ተወለደች። ቤተሰቦቿ ብዙ ልጆች ነበርዋቸው። በተወለደችበት አገር ስየና በ1380 ዐረፈች።

በ16 ዓመት ዕድሜዋ የቅዱስ ዶሜኒኮ ራዕይ ታያት። በዚህ ራዕይ ተገፋፍታ የ3ኛ የደሞኒካውያን ደናግል ማኅበር ኣባል ሆነች፡፡ ይህ የደሞኒካውያን የደናግል ማኅበር ማንተላተ ማለትም ባለ ካባ ደናግል በሚል ስምም ይታወቅ ነበር። ከቤተሰቦችዋ ጋር ትኖር በነበረችበት ግዜ በግልዋ የድንግልና መሓላ በማድረግ በጸሎትና በተጋድሎ ስትኖር እንዲሁም በምግባረ ሠናይ በተለይ ሕመምተኞችን ትረዳ ነበር።

የሕይወትዋ ቅድስና በሁሉም ዘንድ በታወቀና በተስፋፋ ግዜ የመንፈሳዊ ምክር ምንጭ ነበረች። ምክርዋን ለመጠየቅ እርሷ ጋር ይሄዱ የነበር ከሁሉም የኅብረተሰቡ ክፍል ነበሩ፡ መሳፍንት፣ ባለሥልጣኖች፣ ሊቃውንት፣ አርቲስቶች፣ ውሉደ ክህነት እንዲሁም ያኔ በአቪኞ ይቀመጡ የነበሩት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ግሬጎርዮ 11ኛም ሳይቀር መንፈሳዊ ምክርዋን ይጠይቁ ነበር። ቅድስት ካቴሪና ለርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሬጎርዮ 11ኛ ወደ ትክክለኛ መንበራቸው ወደ መንበረ ሮሜ እንዲመለሱ በብርታት ምክርዋን እንዳቀረበችና ውጤትም እንዳገኘችበት ይነገራል።

ቤተክርስቲያን እንድትታደስና በሃገራት መካከል ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ተጉዛለች። ለዚህም ነው ስመ ጥር ር.ሊ.ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅድስት ካቴሪና የኤውሮፓ ጠበቃ እንድትሆን ያወጁት። ጥንታዊው የአውሮፓ ክፍለ ዓለም ክርስቲያናዊ መሠረቱን እንዳይዘነጋ እንዲሁም የጉዞው መሠረት የሆኑ በቅዱስ ወንጌል የሚገኙ መሠረታዊያን የፍትሕንና የስምምነትን ዕሴቶችን ለማረጋግጥ በሚል ዓላማ ነው።

ቅድስት ካተሪና እንደሌሎች ቅዱሳን ሁሉ ብዙ ተሰቃየች። በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ በእርሷ መጠራጠር ጀመሩ። ከመሞትዋ 6 ዓመት በፊት በ1374 ዓ.ም. በፊሬንሰ የጣልያን ከተማ በተካሄደው የዲሜኒካውያን ገዳም አጠቃላይ ጉባኤ ፊት በመቅረብ ስሕተት አንዳይኖራት ተመረመረች፡ ምንም ስሕተትም ኣልተገኘባትም፡፡ በዚ በዚሁ ኣስቸጋሪ ግዜ እርስዋ በምክር ትረዳው የነበረች እርሱም አንደ አበ ነፍስ ያገልግላት የነበረ የዶሜኒኮ መነኩሴ ኣባ ራይሞንዶ ካፕዋ ነበሩ። እኝህ መነኩሴ ከግዜያት በኋላ የዶሜኒካውያን ማኅበር አበምኔት ሆኑ። የቅድስትዋን ገድልና ሕይወት ታሪክም ፃፉ። ቤተ ክርስቲያን የካቴሪናን ሕይወትና ገድል ካጠናች በኋላ በ1461 ቅድስናዋን አወጀች።

የቅድስት ካቴሪና ትምህርት ስለ መለኮታዊ ኀልዮ ወይም ኣሳቢነት ይናገራል። ማንበብና መጻፍ የጀመረችው በወጣትነት ዕድሜዋ ስለነበር ማንበብ ብዙ ያስቸግራት ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን ብዙ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ካነበበችና ካስተነተነች በኋላ እንደ መልዕክትና የጸሎት ስብስቦች፡ “የመለኮታዊ ኅልዮ ወይም አሳቢነት ውይይት” በሚል ርእስ ዋና ትምህርትዋ ደርሰች።

ትምህርትዋ እጅግ ሰፊና ጥልቅ በመሆኑ ስመጥር የእግዚአብሔር አገልጋይ ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ 6ኛ በ1970 ዓ.ም. የቤተክርስቲያን ሊቅ(ዶክተር) ብለው ሰይመዋታል። ይህ ማዕረግ ር.ሊ.ጳ ፕዮስ 9ኛ የሮማ ከተማ ጠበቃና የእግዚአብሔር አገልጋል ር.ሊ.ጳ ፒዮስ 12ኛ ደግሞ የጣልያን ኣገር ጠበቃ በማለት በሰየማት ማዕረግ ላይ ተጨምራል።

ቅድስት ካተሪና ከተገለጡላት ብዙ ራዕዮች በአንዱ፡ ኢየሱስ ክርስቶስና ማርያም ሲታይዋት በዚህም ራዕይ ኢየሱስ ለካቴሪና አንፀባራቂ ቀለበት በመስጠት “እኔ ፈጣሪሽና አዳኝሽ በእምነት አገባሻለሁ፣ በሰማያት ከእኔ ጋር ዘለዓለማዊ ጋብቻ እስክታደርጊ ድረስ ይህን እምነት ዘወትር በንጽህና መጠበቅ አለብሽ” አላት። ያ ቀለበት ለእርሷ ብቻ ይታይ ነበር። የቅድስት ካቴሪና መንፈሳውነት ከዚህ ራዕይ በኋላ ክርስቶስን የሕይወቷን ማእከል ያደረገ ነበር። ከክርስቶስ ጋር ጥልቅ መወሃሃድና መተማመን ፈጠረች። ከሁሉም መልካም ነገር በላይ የሚወደድ መልካም ነገር ኢየሱስ ነው። ይህ ውህደት በሌላ መንገድም በቅድስትዋ ሰቂለ ኅሊናዊ ሕይወት ጠንክሮ እናገኘዋለን። ከክርስቶስ ጋር ልብ ለልብ እንደተለዋወጠች ገድልዋና የሕይወት ታሪክዋ የጻፉት አባ ራይሞንድ ካተሪና ያየችውን ራዕይ ታካፍላቸው ስለነበር፡ ኢየሱስ በእጁ አንፀባራቂ ቀይ የሰው ልብ ይዞ እንደታያትና ጐንዋን ከፍቶ “ውድ ልጄ ሆይ፡ ትናንትና ልብሽን ስለሰጠሽኝ ዛሬ ልቤን እሰጥሻለሁ በልብሽ ምትክ ይህን ልቤን አስቀምጣለሁ ከዛሬ ወዲህ የልብሽን ቦታ ልቤ ይይዘዋል” አላት።

ቅድስት ካቴሪና ቅዱስ ጳውሎስ “የምኖረው እኔ አይደለሁም ክርስቶስ ነው በእኔ የሚኖረው” ያለውን በተግባር ተረጐመችው። እንደ የሲየናዋ ቅድስት እያንዳንዱ ምዕመን ከክርስቶስ ልብ ስሜት ጋር በመዋሃድ እግዚአብሔርን ማፍቀርና ጓደኛውን እንደራሱ አድርጎ ለመውደድ ይፈልጋል። እያንዳንዳችን ልባችን እንደሚለወጥ ማድረግ እንችላለን፡ ክርስቶስ እንደሚያፈቅረው ለማፍቀር ለመማርም እንችላለን።

ይህንን ለማድረግ ለየት ያለ የኑሮ ዘዴ ያስፈልጋል። ይህም በጸሎትና የእግዚአብሔርን ቃል በማስተንተንና ቅዱሳት ምሥጢራትን በመሳተፍ በተለይም አዘውትሮ ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል የሚመገብ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ መሆ “ሳክራመንቱም ካሪታቲስ” የፍቅር ሚስጢር በሚለው ሓዋርያዊ መልእክቴ እንደጠቀስኩት ቅድስት ካቴሪና ቅዱስ ቁርባንን ከሚያከብሩ ሠራዊት አንዷ መሆንዋን ለመጥቀስ የፈለግሁትም ለዚህ ነው።

ውድ ወንድሞችና እህቶች ቅዱስ ቁርባን እግዚአብሔር በቀጣይ ሁኔታ የሚያሳድስልን ልዩ የፍቅር ስጦታ ነው። የእምነት ጉዞኣችንን በመመገብ፡ ተስፋችንን በማበረታታት ፍቅራችንን በማቀጣጠል ዘወትር እርሱን እንደምንመስል ያደርገናል።

ቅድስት ካተሪና ለብዙዎች አብነት ሆነች። በምክርዋና በሕይወትዋ ብዙዎችን ትመግብ ስለነበር እማማ ብለው ይጠርዋት ነበር። መንፈሳዊ እናታቸውም ነበረች። ዛሬም ቢሆን ቤተክርስቲያናችን በብዙ ቅዱሳት እናቶች አመካኝነት ትልቅ ፀጋ ታገኛለች። እነኝህን እህቶች ለነፍሳት የእግዚአብሔርን ሐሳብን እንዲሰርፅ በማድረግና የምእመናን እምነትን በማጐልበት ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና ከፍተኛ የቅድስና ሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋሉ።

ቅድስት ካተሪና ለመንፈሳውያን ልጆችዋ በምትጽፍበት ግዜ በጣፋጩ ኢየሱስ በመንፈስ የወለድኩህ ልጄ በማለት እናታዊ ምክርዋን ትለግስላቸው ነበር። ሌላው ልዩ ስጦታዋ ደግሞ የእንባ ስጣታ ነበር። ይህ የርኅራኄና የገርነት ምልክት ነው። ብዙ ቅዱሳን የኢየሱስ ርኅራኄና ገርነት በማሳደስ የእንባ ስጦታ አግኝተዋል። ኢየሱስ የጓደኛውን የአልአዛር መቃብር እና የማርታና ማርያ ሐዘንን በተመለከተ ግዜ ስሜቱንና እንባውን ሊደብቅ አልፈለገም። እንዲሁም የኢየሩሳሌምን የመጨረሻ ውድቀት ባስታወሰ ግዜ በዚሁ ምድር በመጨረሻ ቀኖቹ ኣንድ ኮረብታ ላይ ወጥቶ በተመለከታት ግዜ አልቅሶላታል።

እንደ ቅድስት ካቴሪና አስተሳሰብ የቅዱሳን እንባ ከኢየሱስ ደም ጋር ይዋሃዳል። ሰዎችን ስትመክር ደግሞ “የተሰቀለ ኢየሱስ ትዝታ ይኑራችሁ እንደ ዓላማም የተሰቀለው ኢየሱስን ያዙ፡ በተሰቀለው ኢየሱስ ቁስሎች ተደበቁ በፈሰሰው በኢየሱስ ደም ታጠቡ” በማለት ታስተምር ነበር። ሌላው የሚያስደንቀው የቅድስት ካተሪና ጠባይም ለካህናት የነበራት ክብር ነው። የካህናት ድካም ብታውቅም ቅሉ “ቅዱሳን ተላላኪዎች” ብላ ትጠራቸው ነበር። ለር.ሊ.ጳ ደግሞ በምድር ላይ ያለ ጣፋጭ ኢየሱስ ብላ ትጠራው ነበር፡፡ በቅድስትዋ ኣመለካከት ካህናት በቃለ እግዚአብሔርና በቅዱሳት ምሥጢራት ነፍሳትን በኢየሱስ ደም አጥበው ያንፃሉ፡፡ ካህናት ኢየሱስ ለቤተክርስቲያን ባለው ጥልቅና የማያቋርጥ ፍቅር ተንቀሳቅሰው ለኅላፊነታቸው ታማኝ መሆን አለባቸው በማለት አደራ ብላለች። ከመሞትዋ በፊት ከስጋዋ ስትሰናበት ሕይወቴን በቤተክርስቲያን በመሆን ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሰጠህዋት ይህም ለኔ ልዩ ፀጋ ነው ብላ ነበር።

ከቅድስት ካቴሪና የምንማረው ነገር ኢየሱስንና ቤተክርስቲያንን ማወቅና ማፍቀር ነው። “የመለኮታዊ ኅልዮ ወይም አሳቢነት ውይይት” በሚለው ጽሑፍዋ ለኢየሱስና ለቤተክርስቲያን የሚደረገው እውቀትና ፍቅር በሰማይና በምድር መሃከል የቆመ ድልድይ ትለዋለች። ይህ ድልድይ በሶስት ደረጃዎች የቆመ ነው። በእየሱሱ እግር ጐንና አፍ የቆመ ድልድይነው፡፡ በፍፅምናና በቅድስና ለመኖር፡ ከኅጢኣት መለየት፡ መንፈሳውያን ኅይለት ማዘውተርና፡ ከእግዚአብሔር ጋር ጣፋጭና ስሜታዊ ውህደት ማድረግ ያስፈልጋል።

ውድ ወንድሞችና እህቶች ከቅድስት ካቴሪና በብርታት ማፍቀር እንዳለብን እንማራለን። ኢየሱስንና ቤተክርስቲያንን በጋለና በሙሉ ፍቅር ማፍቀር አለብን። በመጽሐፍዋ ማጠቃለያ ላይ የኢየሱስን ምረት በማስተንተን በደረሰችው ፀሎት፡ “በምሕረቱ በደምህ አጠብከን፡ በምህረት ከፍጡሮችህ መወያየት ፈለግህ፣ ኦ በፍቅር ያበድክ እንደእኛ ሥጋ መልበስ አልበቃ ብሎህ ስለኛ መሞትን መረጥክ! ኦ ምሕረት አንተን ሳስብ ልቤ ይቃጠላል፥ ለማሰብ በምፈልግበት ግዜ ከምሕረትህ ሌላ ምንም ማግኘት አልቻልኩም” ያለቻቸውን የቅድስት ካቴሪና ቃላት የእኛ እናድርጋቸው።








All the contents on this site are copyrighted ©.