2010-11-07 11:02:48

ዘጽጌ 5ኛ


መዝ፤ ጸገየ ወይን ወፈርየ ሮማን

ንባባት፤ ሮሜ 11፡13~24፤ ራእይ 12፡13~18፤ ግ.ሐ 11፡1~11፤ ማቴ 21፡33~45

ምስማክ ዐጸደ ወይን ኣፍለስከ እምግብፅ፤ ሰደድከ አሕዛበ ወተከልከ ኪያሃ፤ ወጸህከ ፍኖተ ቅድሜሃ (ከግብጽ የወይን ግንድ ኣፈለስክ፤ ኣሕዛብን ኣባረርክ እርሷን ተከልክ፤ በፊቷም መንገድን ጠረግህ፤ መዝ 79፡8)

ቅዳሴ ዘእግዚእትነ ማርያም (ጐሥዐ)

ውድ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሲነበብ የሰማነው ቃለ ወንጌል ለእመ ቤታችን ድንግል ማርያም የተሠጠው በአበባና በፍሬ ያሸብረቀው ዘመነ ጽጌ በመገባደድ ላይ በመሆኑ ወደ ሌላ ዘመን መሸጋግራችንን የሚያመለክት የወይን ኣትክልት ምሳሌ ያቀርብልናል፤ የወይን ተክል በክረምት እንደ ደረቅ ነገር ደክሞ በመክረም በበጋ ወራት ሊያብብና ፍሬ ሊሰጥ ይጀምራል፤ ሆኖም ግን ክፍተኛ ጥንቃቄ ሰለሚያስፈልገው ዙርያው ታጥሮ ተቀጥሮ በተጨማሪም ኣጥፊ ከሆኑ ቀበሮዎችና ሌሎች ነገሮች ለመጠበቅ ሰው በግንብ ተቀምጦ በደምብ ይከታተለዋል። የዚህ ምሳሌ ትርጉም ኢሳይያስ ነቢይ በትንቢቱ 1፡8 ሲያብራራው፤ ‘የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፥ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች።’ በማለት ምሳሌው በመጀመርያ ሕዝበ እስራኤልን ሲመለከት በዘመነ ኣዲስም ቤተ ክርስትያንን እንደሚያመለክት ሊቃውንት ይናገራሉ። የወንጌሉ ኣንድምታ ስለ ቅጥሩ ትርጓሜ ሲገልጽ የረድኤተ እግዚአብሔር ምሳሌ መሆኑን ያብራራል። በምድረ እስራኤል እንደ በሁሉም ወይን የሚያፈሩ ኣገሮች እርሻው እንዲሳካ ጥሩ ፍሬ እንዲያፈራ ብርቱ ክንክን እንደሚያስፈልገው በትንቤተ ሕዝ 16፡6 ሓረጉ እንዳይሰበር መደገፍያ እንደሚሰራለት፤ በኦሪት ዘሌዋ 25፡13 የበለጠ እየሰፋና እየጠነከረ እንዲያፈራም በየዓመቱ መገረዝ እንዳለበት ይናገራል። ሌላው ይቅርና ቀበሮዎች ረጋግጠው እንዳያበላሹት በክልሉም ኣካባቢ እንዳያልፉ በመሃልየ መሃለይ 2፡5 የወይን ጓሮ የሚያጠፉትን ቀበሮዎች ኣጥምዱልን በምንም ዓይነት ተክሉ እንዳይረበሽ ያስጠነቅቃል።

ቅዱስ ዳዊትም በዛሬው ምስማክ መዝ 79፡8 ከግብጽ የወይን ግንድ ኣፈለስክ፤ ኣሕዛብን ኣባረርክ እርሷን ተከልክ፤ በፊቷም መንገድን ጠረግህ ሲል የዚህ የወይን ኣትክልት ምሳሌ ቤተ እስራኤል መሆኑን ይገልጣል። ምሥጢሩም እስራኤልን ከግብጽ አወጣህ፤ አሕዛብን ከከነዓን አውጥተህ የደረሰ መከራቸውን የታነሸ ግንባቸውን ለእስራኤል አውርሰህ በከነዓን ተከልካቸው። ቀን በደመና ለኢሊት በብርሃነ እሳት እየመራህ ሲዋጉ አሕዛብን እየመታህ መንገዷን አቀናህላት ማለት ነው።

መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ምሳሌ ለማን እንደሆነ ወዲያውኑ የተረዱት ፈሪሳውያን ሊገድሉት እንደፈለጉ ግን ሕዝብ እንደ ነብያ ይመለከተው ስለንበረ ፈርተው ዝም እንዳሉ ወንጌሉ ይነግረናል፤ ስለዚህ ገበሬዎቹ ሕዝበ እስራኤልን ለማገልገል የተላኩ ኣበውና ነቢያት መሆናቸው ግልጽ ነው፤ በመጨረሻ ላይ የተላከው የውይኑ ጌታ ልጅ ደግሞ ራሱ የመድሃኒታችን የኢይሱስ ክፍስቶስ ምሳሌ ሲሆን ከዐፀደ ወይኑ ኣውጥተው መግደላቸው በቀራንዮ ክከተማ ውጭ ተሰቅሎ ስለ ሕዝቡ መሞቱ የሚያመለክት ምሳሌ ነው።

የወይኑ ትርጉም በበለጠ ለመረዳት ትንቢት ኢሳይያስ 5፡1~5 የተመለክትን እንደሆነ ‘አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው። በዙሪያው ቈፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት፥ በመካከሉም ግንብ ሠራ፥ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ፥ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ። አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ። ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ? አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል።’ ሲል ልክ ያኔ እንደነበረ ኣሁንም የሃይማኖት መሪዎች መጠንቀቅ እንዳለባቸው ያመለክታል።

ይህ ለእስራኤል የተባለው ትንቢት ቤተ ክርስትያንን በአጠቃላይ ሲመለከት ለየት ባለ መንገድ ደግሞ እያንዳንዳችን እኛንም ይመለከታል። ጌታ ኢየሱስ ስለ ቤተ ክርስትያን ብዙ ሥቃይና መከራ ተቀበለ፤ በመስቀል ተሰቅሎ ደሙ ስለ እርሷ አፈሰሰ፤ በአጽናኙ መንፈስ ቅዱስና ስጦታዎቹ አጌጣት፤ በስሙ ለለመንችው ሁሉ እንደሚያደርግላት ቃል ገብቶላት ሕያዋንና ሙታንን ለመፍረድ በክብር ዳግም እስኪ መለስ ድረስ እስከ መጨረሻ ታማኝ ሆና እንድትቆይ ኣደራ ጥሎላት ወደ ሰማያዊ ኣባቱ ተመለሰ።

ይህች በወይን ተክል የምትመሰል ቤተ ክርስትያን እንዲሁም የእያንዳንዳችን በደሙ የታጠበች ነፍስ ሁኔታ በሃይማኖት መሪዎችና በእያንዳንዳችን ትጋት እንደምትወሰን በማስረዳት የሃይማኖች መሪዎች ጠንቅቀው መጀመርያ ራሳቸውን ከዛ ም እመናኖችን መጠበቅ እንዳለባቸው እንዲሁም እያንዳንዳችን ደግሞ ከወይን ግንድ የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳንለይ እንድንኖር ከወይን ግንድ ከሚለዩ ቀበሮዎች የወይኑን ፍሬ የማይሰጡ ለራሳቸው ከሚውጡ የሰው አውሬዎችን እንዲያጠምድልን እንደ ጠቢቡ ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር በመለመን በጸሎት እንትጋ።








All the contents on this site are copyrighted ©.