2010-10-01 16:02:31

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከበጋ የዕረፍት ቦታቸው ወደ ቫቲካን ተመለሱ


ቅዱስ አባታችን ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከበጋው የዕረፍት ቦታቸው የካስቴል ጋንዶልፎ ሐዋርያዊ አዳራሽ ሲሰናበቱ የሰጡት ትምህርት ቅዱስ ጂሮምን በመጥቀስ “መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ክርስቶስን አለማወቅ ነው” በማለት አመልክተዋል።

ትላንት ድኅረ ቀትር ቅዱስነታቸው በካስቴል ጋንዶልፎ ሐዋሪያዊ አዳራሽ ሚገኘውን የበጋ እረፍት ቦታቸውን ለቀው ወደ መንበራቸው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተመለሱ ከቅድስት መንበር የወጣ ዜና አመልክተዋል።

ቅዱስነታቸው ከቦታው ሲሰናበቱ ባደረጉት ንግግር፡ “የእግዚኣብሔርን ቃል በየቀኑ በገርነትና በደስታ መቀበል ኣለብን” ሲሉ በካስቴል ጋንዶልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ የሚሰሩትን ሠራተኞችን በእረፍቱ ወራት ስላደረጉላቸው መስተንግዶ በማመስገን በተለይም የሠራተኞቹ ዋና ኅላፊ ዶክተር ሳቨርዮ ፔትሪሎን አጥብቀው አመስግነዋል።

ቅዱስ ጂሮምን በመጥቀስ ባስተማሩት ትምህርት፡ ቅዱስ ጂሮም በ4ኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረ፡ የቤተክርስቲያን ሊቅ በተለይም የሥርዓተ አምልኮ መምህር እንደነበር ሲያውሱ የቅዱሱም ሕይወት በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ የታነፀ እንደነበርና መጽሐፍ ቅዱስንም በዛን ዘመን ከግሪክ ቋንቋ ወደ ላቲን ቋንቋ መተርጎማቸውን አውስተዋል። እንደእርሱ የእግዚአብሔርን ቃል በየዋሕ ልብ እንድንቀበልና እንድናዳምጥ ኣደራ፡ ምክንያቱም የእግዚብሔር ቃል የሚያበራና የሚገልፅ፣ አቅጣጫን የሚመራ፣ የሚከላከል፣ የሚመክርና፣ የሚጠግን፣ ነው ሲሉ አስተምረዋል።

በተጨማሪ የቤተክርስቲያን ሊቁ የቅዱስ ጅሮምን አባባል በመጥቀስ መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ክርስቶስን አለማወቅ ስለሆነ እያንዳንዱ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በማድረግ መኖር ኣለበት። መጽሓፍ ቅዱስን እንደ የጥንት ታሪክ በመውሰድ ሳይሆን እንደ ኣዲስ ቃለ ሕይወት በእርሱ መመገብና እርሱን መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለሁሉም የክርስትና ሕይወት ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ምክንያትና ምንጭ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር ሁሉም ሊያውቅና ሊረዳው ይችላል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃለ እግዚአብሔርን በትሕትና የማዳመጥ አብነት ናት ከእርሷ ተማሩ ብለዋል።

እ.አ.አ. ኅዳር 7 ቀን 2007 ዓ/ም ባካሄዱት ሳምንታዊ የዕለተ ሮብዕ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ስለ ቅዱስ ጅሮም ሲያስተምሩ ቅዱሱ የሰው ልጅ ከቃለ እግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ የተናገሩትን ሁለት መንገዶች ገልጠው ነበር። አንደኛው መንገድ የግል ግንኙነት ሲሆን በዚሁ መንገድ ቃለ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን እንደሚሰጥ መልዕክት ነው። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ማኅበራዊ ነው። ቅዱስ መጽሐፉን ከቤተክርስቲያን ጋር በሕያው አንድነት ማንበብ ያስፈልጋል። የእግዚአብሔር ቃል ከግዜ በላይ መሆኑን መርሳት የለብንም …የሰው ልጅ አስተያየቶች የሚመጣና የሚሄድ ነው፡ ዛሬ እንደዘመናዊ የምንመለከተው ነገ ግዜው ያለፈ አሮጌ ይሆናል። የእግዚአብሔር ቃል ግን የዘላለማዊ የሕይወት ቃል ነው። ቃሉን በውስጣችን ካኖርን ለዘላለም እንኖራለን። በማለት ኣስተምረው ነበር፡፡








All the contents on this site are copyrighted ©.