2010-09-15 15:48:42

የር.ሊ.ጳጳሳት ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ (14.09.2010)


ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ረፋድ ላይ በጳውሎስ 6ኛ ኣደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናንና ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት ለመጡ ነጋድያን የተለመደውን ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ ለማስተማር፤ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በሄሊኮፕተር በረው ወደ ቫቲካን ከተማ መጥተዋል።

ቅዱስነታቸው ስለ ቅድስት ክያራ ኣስተምረው በደቡብ ኤስያ ስላለው ችግር ጥሪ በማቅረብ ትምህርቱን ከደመደሙ በኋላ እንደገና በሄሊኮፕተር ወደ ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያው ኣደራሽ ተመልሰዋል።

ቅዱስነታቸው ኣስተምህሮኣቸውን በስፊው በጣልያንኛ ቋንቋ ኣቅርበው በእንግሊዘኛም አሳጥረው ይህንን ኣስተምረዋል።

“ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ የዛሬ ትምህርተ ክርስቶስ ስለ ትልቅዋ የብሕትውና ኣብነትና የቅዱስ ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ ጓደኛና የቅድስት ክያራ ደናግል ማኅበር መሥራች ስለሆነችው ስለ የኣሲዚዋ ቅድስት ክያራ ይመለከታል። ብዙ ንብረት ከነበራቸው ቤተሰብ ተወለደች፤ ግን ሥርነቀል ድህነት ንጽሕናና በእግዚአብሔር የመተማመንን ሕይወት መረጠች፤ ሕይወትዋን በሙላት ለክርስቶስ ለመሰዋት ቅድሱ ፍራንቸስኮ በገዳሙ ተቀበላት፤ ከሌሎች እኅቶችዋ በቅዱስ ዳምያን ቤተ ክርስትያን የኅብረት ሕይወትን ጀመረች። በቅድስት ክያራና በቅዱስ ፍራንቸስኮስ መሀከል የነበረው መንፈሳዊ ጓደኝነት በሊሎች ቅዱሳን መሀከል እንደሚደረገው መንፈሳዊ ጓደኝነት ለላቀው የክርስቶስ ፍቅር የሚረዳና ለፍጽምና ጉዞ ኣዲስ ኃይል የሚሰጥ ጓደኝነት ነው።

ለመጀመርያ ጊዜ በሴት ልጅ የተጻፈው የቅድስት ክያራ ሕገ ማኅበር የቅዱስ ፍራንቸስኮስና የእርሷን ኣብነት በመከተል በእድገት ለነበሩት የሴት ልጆች ገዳማት የቅዱስ ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ እሴትን መመርያ በማድረግ እንዲጠቀሙበት በማለት ነበር። ከጥቀ ቅዱስ ቊርባን የመነጨው የቅድስት ክያራ መንፈሳውነት ክርስቶስን እንደ ጸጋ ምንጭና ፍጽምና ማስተንተንን በማፍቀር የተመሠረተ ነበር። ቅድስት ክያራ ለእግዚአብሔር የተሰዋ ድንግልና ቤተ ክርስትያን ለሰማያዊ ሙሽራዋ ለሆነው ክርስቶስ ያላትን ፍቅር እንድሚያመለክት እንዲሁም በቤተ ክርስትያን ታሪክ ውስጥ ብርታትና እምነት የሞላቸው ሴቶች ያበረከቱትን ወሳኝ ሚና ያመልክታል፤” በማለት ስለ ቅድስት ክያራ ካስተማሩ በኋላ በደቡባዊ የኤስያ ክፍል በዚሁ ሳምንት ስለተከሰተው ግጭት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤ “በዚሁ ቀናት በተለያዩ የደቡብ ኤስያ ክፍሎች በተለይም በህንድ በፓኪስታንና በኣፍጋኒስታን የሚከሰቱትን ችግሮች በሥጋት እየተከታተልኩት ነው፤ የዚሁ ግጭት ሰለባ ስለሆኑ እጸልያለሁ፤ የሃይማኖት ነጻነት እንዲከበርና፤ ከጥላቻና ከዓመጽ ቅ የዕርቅና የሰላም መንገድ እንዲመረጥ ኣደራ እላለሁ” ሲሉ ጥሪ ኣቅርበዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.