2010-08-12 16:34:08

የሳንታ ማርያ ማጆረ ባዚሊካ ሕንፀት ዝክረ በዓል


የሮማ ቤተ ክርስትያን ትናንትና የሳንታ ማርያ ማጆረ ባዚሊካ ሕንፀት ዝክረ በዓል ከፍ ባለ ድምቀት ኣክብራ ዋለች። በላቲን ሥር ዓተ ኣምልኮ የምትመራ ም ዕራባዊት ቤተ ክርስትያን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከታነጹ መካነ ንግደቶች ጥንታዊና ዓቢይ የሆነው ሳንታ ማርያ ማጆረ በስመ ጥር ር.ሊ.ጳ ሲስቶ ሶስተኛ እመቤታችንን የኣምላክ እናት ብሎ ከሰየመው በ431 ዓም ከተካሄደው የኤፈውሶን ጉባኤ በኋላ ነበር።

ቅዱስነታቸው ስለ እመቤታችን ሲያስተምሩ፤ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ለመሆን ስለፈለገና በእመቤታችን ድንግል ማርያም ትሕትና ስለተማረከ ድንግል ማርያምን እናቱና እናታችን ኣደረጋት፤ የኤፈውሶን ጉባኤ የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊነት ለመከላከል እመቤታችንን ቲዮቶኮስ ማለትም የኣምላክ እናት ብሎ ሰይሞታል፤ ከጉባኤው በኋላ ትልቅ የእመቤታችን ኣክብሮት በቤተ ክርስትያን ተስፋፋ፤ ትላልቅ ኣብያተ ክርስትያንትም በስሟ ታነጹ፤ ከእነዚሁ ኣንደኛና ትልቁ እዚሁ በሮማ የሚገኛ የሳንታ ማርያ ማጆረ ባሲሊካ ነው፤ የእግዚአብሔር እናት የሚለው ቅጽል ከጥንት ማኅበረ ክርስትያን ድንግል ማርያምን የሚያከብሩበት ነው። ይህ ቅጽል በሰው ልጆች የደኅንነት ታሪክ የእመቤታችንን ተልእኮ ይገልጻል፤ ለእመቤታችን የምናቀርባቸው ሌሎች ስሞችና ቅጽሎች ሁላቸው መሠረታቸው የመድኃኔ ዓለም እናት ለመሆን የተቀበለችው ጥሪ ነው፤ የሰው ልጅ ደኅንነት ዕቅድን እውን ለማድረግ እግዚአብሔር የሰው ልጅ ፍጥረት የሆነችውን መርጦ ምሥጢረ ሥጋዌ በእርሷ እንዲፈጸም ኣደረገ፤” ሲሉ በተለያዩ ግዝያት ኣስተምረዋል።

ቅዱስነታቸው የዚህ ምሥጢር ትርጉም ሲገልጡ፤ ለምን ነው እግዚአብሔር ከሌሎች ሴቶች ሁሉ የናዝሬቲቱን ማርያም የመረጠ በማለት ይጠይቃሉና እንዲህ ሲሉ ይመልሳሉ፤ “መልሱ ልንመረምረው በማንችለው መለኮታዊ ፍቃድ ተደብቆኣል፤ የሉቃስ ወንጌል 1፡30 የተመለከትን እንደሆነ ግን ኣንድ መልስ ኣለ፤ እርሱም ትሕትናዋ፤ ኣዎ እግዚአብሔር በእርሱ ፊት ሞጎስና ጸጋ ባገኘው የእመቤታችን ድንግል ማርያም ትሕትና ተማርከዋል፤ በዚህም የኣምላክ እናት ሆነች፤ የቤተ ክርስትያን ኣምሳልና ኣብነት በመሆን የጌታን ቡራኬ ለመቀበልና ቡራኬውም ለመላው የሰው ልጅ ዘር እንድታስፋፋ ከሕዝብ ተመረጠች። ይህ ቡራኬ ከኢየሱስ ሌላ መሆን ኣይችልም፤ ከመፈጠርዋ በፊት የመረጣትና የባረካት የዚሁ ጸጋ ምንጭ ኢየሱስ ራሱ ነው፤ እርስዋም ኢየሱስን በእምነትና በፍቅር ተቀበልችው፤ ለዓለምም ሰጠችው፤ የእኛ ጥሪና ተልእኮም እንዲሁም የቤተክርስያን ይህ ነው፤ ማለትም ክርስቶሥ በሕይወታችን መቀበልና በእርሱም ኣማካኝነት ዓለም እንዲድን ለዓለም ማበርከት ነው” ሲል ጥልቅ ትምህርት ሰጥተው ነበር።

ስለዚህ እመቤታችን ድንግል ማርያም የኣምላክ እናት ናት፤ ይህ እናትነት ከእኛም ኣይርቅም፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ዘወትር ኣጠገባችን ናት፤ ልባችንን ታውቃለች ጸሎታችንን ለመስማት ትችላለች፤ በእናታዊ ርኅራኌ ልትረዳን ትችላለች፤ እነሆ እናትህ የሚለው የጌታ የመጨረጻ ቃል እንደ እናታችን ዘወትር እንደምትሰማን ኣጠገባችን እንድምትገኝ የኢየሱስ እናት ስለሆነችም ከችሎታው እንደምትካፈል እናውቃለን፤ ስለዚህ ሁለመናችን ለእርሷ መማጠን እንችላለን።

የተከበራችሁ ኣድማጮቻችን በሥር ዓተ ኣምልኮኣችን ባሕረ ሓሳብ መሠረት ነገ የወርሓ ነሓሴ መባቻ የፍልሰታ ጾምና ምህለላ የምንጀምርበት ስለሆነ በዚህ ኣጋጣሚ ይህ የሰማነው የእመቤታችን ማንነትና ቅርበት የሚገልጸው የቅዱስ ኣባታችን ትምህርት ለዘመነ ፍልሠታ ጥሩ የጸሎት ሓሳብ እንዲሆነን እየተመኝን መልካም ዘመነ ፍልሠታ እንዲሆንልን እየተመኘን የጸጋ ግዜ ስለሆነ ያለንን ችግር ለእርሷ በመማጠን ለጾምና ለጸሎት እንድንተጋ በዚሁ ኣጋጣሚ ኣደራ ማለት እንወዳለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.