2010-08-06 11:34:40

ከ55 ሺ በላይ መዘምራን ወአናጒንስጢስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ


ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ረፋድ ላይ ከ55 ሺ በላይ የሚሆኑ ከመላው ኤውሮጳ ለንግደት በሮም ለሚገኙ መዘምራንና ኣናጉንስጢስ ለማግኘት እንዲሁም ከወጣቶቹ ጋር ለተሰበቡት ክ35 ሺ በላይ ለሚሆኑ ምእመናንና ነጋድያን የተለመደውን ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ ለማስተማር፤ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በሄሊኮፕተር በረው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ መጥተዋል። ወጣቶች ምእመናንና ነጋድያን የቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይን ከጫፍ እስከ ጫፍ ኣጥለቀልቀውት የተለያዩ ኣገሮች ባንደራዎች እያወለበለቡና የተለያዩ መዝሙሮች እየዘመሩ ቅዱስ ኣባታችንን በትልቅ ደስታን ጭብጨባ ተቀብለዋቸዋል።

ቅዱስነታቸው ሰላምታና መልካም ምኞትን ከንግደቱ ኣዘጋጆች ከተቀበሉ በኋላ ይህን ትምህርት ሰጥተዋል፤ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ ዛሬ በዚሁ አደባባይ በዚህ ቀን ለሚቀርበው የዕለተ ሮቡዕ ሳምንታዊ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ በከፍተኛ ቊጥር ተሰብስባችሁ በምትገኙበት ጊዜ እናንተው መሀከል በመገኘቴ የሚሰማኝ እጅግ የላቀ ደስታ ለመግለጥ እወዳለሁ፤ እንደምታዩት ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዛሬ ዕለት በብዙ ሺ በሚቈጠሩ ከኤውሮጳና ከሌሎች ክፍለ ዓለማት በመጡ መዘምራንና ኣናጒንስጢስ አጠለቅልቃ ትገኛለች። ውድ ወንድ ወጣቶችና ሴት ወጣቶች እንኳን ደህና መጣችሁ ባሉ ግዜ ኣደባባዩ እንደገና በጭብጨባ ኣስተጋባ፤ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል፤ በአደባባዩ ከተሰበሰቡ መዘምራንና ኣናጒንስጢስ ኣብዛኛዎቹ የጀርመነኛ ቋንቋ ተንጋሪ ስለሆኑ በእናቴ ቋንቋ በሆነው በጀርመነኛ ሰላምታ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ፤ ውድ የጀርመነኛ ቋንቋ ተናጋሪ መዘምራንና ኣናጉንስጢስ ውንድ ልጆችና ሴት ልጆች፤ እዚህ ሮም እንኳን ደህና መጣችሁ፤ የእናንተ ጠበቃ ቅዱስ ታርቺዝዮ ነው፤ እግረ መንገዴ ደግሞ ስማቸው ከቅዱሱ ጋር የሚተሳሰር የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ ካርዲናል ታርቺዝዮ በርቶነን ሰላም ለማለት እወዳለሁ፤ የመዝምራንና አናጒንስጢስ ጠበቃ ቅዱስ ታርቺዝዮ መሆኑን ከገለጡ በኋላ ከነጋድያን መዘምራንና ኣናጒንስጢስ አብረዋቸው ለመጡት ዲያቆናት ካህናትና ጳጳሳት ሰላምታ አቅርበዋል፤ ለየት ባለ መንገድ ደግሞ የመዘምራንና ኣናጒንስጢስ ዓለም ኣቀፍ ንግደት ኣዘጋጅ ላቀረቡላቸው ሰላምታ ኣመሰገኑ፤ በተለይ ደግሞ የቅዱስ ታርቺዝዮ ምስል ያለበት መሃረም ስላበረከቱላቸው ይህም ወጣት ሳሉ የቤተ ክርስትያን ኣገልጋይ በመሆን በግብረ ዲቊና ያገለገሉትን እንዲያስታውሱ እንዳደረጋቸው ገልጠዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለአጋጣሚው ተብሎ የተዘጋጀው የቅዱስ ታርቺዝዮ ሓውልት እውን እንዲሆን ላበረከቱ ሁሉ ኣመስግነዋል፤ የቅዱስ ታርዝዮ ምስል እ.አ.አ በ2008 ዓም በእስዊዘርላንድ ቀርቦ እንድነበር እንዲሁም በሃንጋሪና ሉክሰንበርግ ለትው ውቅ ቀርቦ እንደነበር፤ ምናልባትም በኣደባባዩ ከሚገኙ ያዩት ሊኖሩ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ዋናው ትምህርታቸው በመመለስ የመዘምራንና ኣናጒንስጢስ ጠበቃ የሆነው ቅዱስ ታርቺዝዮ ማን ነው ሲሉ ስለ ቅዱስ ታርቺዝዮ ሕይወት እንዲህ ሲሉ ኣስተምረዋል፡

በሮም ከተማ በኣፕያ ጎዳና በሚገኘው የካሊስቶ መቃብር የቅዱስ ታርቺዝዮ ሰማዕት ዝክር ኣለ፤ ቅዱስ ታርቺዝዮ ጥቀ ቅዱስ ቊርባን በርኩሳን እጅ ገብቶ ከሚራከስ ሕይወቴን እሰዋለሁ በማለት በድንጋይ ተደብድቦ ሰማዕት የሆነ ኣናጒንስጢስ ነው። በ15 ነሐሴ 257 ዓም ክርስትያኖች በብርቱ ግፍ እየተሰደዱና በጉድጓድ እየኖሩ ቅዱስ ታርቺዝዮ በእስር ቤት ላሉ ቅዱስ ቊርባን ደብቆ ሲወስድ በመንገድ ኣሳጆች ኣገኙት፤ ቅዱስ ቊርባንን ሊነጥቁት ቢያስገድዱት እምቢ ብሎ ቅዱስ ቊርባንን በእጁ ጨብጦ በመሞቱ ያሳየው ታማኝነት በማስታወስ ለመንበረ ታቦት ኣገልጋዮች ለሆኑ መዘምራንና ኣናጒንስጢስ በጣልያንኛ፤ ውድ ጓደኞቼ የቅዱስ ታርቺዝዮን ኣብነት በመከተል በቅዱስ ቊርባን የሚገኘውን ኢየሱስ በለጋሥነት ኣገልግሉት ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በዚሁ ኣጋጣሚ በሩስያ በኣፍጋኒስታንና በፓኪስታን በተፈጥሮ ኣደጋ ለተጐዱ ወገኖች ይህንን መልእክት ኣስተላልፈዋል፤ “በዚሁ ጊዜ ሓሳቤና ቀልቤ ሕይወት ያጠፉና ጉዳት ባደረሱ ባህርያዊ አደጋዎች በተጐዱ ወገኖች እንዲሁም አለመጠለያ በቀሩት ወግኖች ላይ ነው። በተለይ ደግሞ በፈደረላዊት ሩስያ በእሳት ቃጠሎ ለተጐዱና በፓኪስታንና በኣፍጋኒስታን በውኃ ማጥለቅለቅ ለተጐዱ ወገኖች ኣስባለሁ። የኣደጋው ሰለባ ለሆኑ ወገኖች በመንፈስ እጐናቸው መሆኔና ጌታን ስለ እነርሱ እንደምለምን ለማረጋገጥ እወዳለሁ። በሥቃያቸው ጌታ እንዲያጸናቸው በችግራቸውም ጌታ እንዲረዳቸው እጸልያለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ የሁሉ ወገን ኣጋርነትና ትብብር እንዳይለያቸው አደራ እላለሁ።” ሲሉ በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታ ከተቀበሉና ካቀረቡ በኋላ ከወጣቶቹ ጋር ኣብረው ኣባታችን በሰማይ የምትኖር በላቲን ቋንቋ ኣዚመው ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.