2010-07-28 10:59:25

የር.ሊ.ጳ የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ (25.07.2010)


ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና ረፋድ ላይ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ምእመናን የዕለቱ ቃለ ወንጌል በመጥቀስ ትምህርት ሰጥተው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካሳረጉ በኋላ በጀርመን የዲዩስበርግ ከተማ ለሙዚቃ በተሰበሰቡ ወጣቶች ላይ በደረሰው ኣደጋ ሕይወታቸው ላጡት 19 ወጣቶችና ለተጐዱት ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሓዘን ገልጠዋል።

ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በፊት ይህን ትምህርት ሰጥተዋል፤ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ የዛሬው ወንጌል ኢየሱስ ከሓዋርያቱ ለየት ብሎ በጸሎት ተጠምዶ መኖሩን ያስታውሳል፤ ኢየሱስ ጸሎቱ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። ኢየሱስ ምንም ዓይነት ተቋውሞ ኣላሰየም፤ ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ከባድ ጸሎትም ኣላስተማረም፤ የዋህ በሆነ መንገድ፤ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ በማለት ኣቡነ ዘበሰማያትን ኣስታማረ፤ (የሉቃስ ወንጌል 11፡2`4 ተመልከት)። ይህም እርሱ ራሱ ከሚጸልየው ጸሎት ማለትም ወደ አባቱ ከሚያቀርበው ጸሎት ያወጣው ነው። ቅዱስ ሉቃስ ኣቡነ ዘበሰማያትን ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ከቀረበው ኣጠር ባለ መንገድ ያቀርብልናል። የአቡነ ዘበሰማያት ጸሎት ቃላት ከሕጻንነት ጀምረን የምናወሳቸው የመጽሓፍ ቅዱስ ቃላት ናቸው። እነኚህ የኣቡነ ዘበሰማያት ቃላት በኣእምሮኣችን ይቀረጻሉ፤ ሕይወታችንን ያቆማሉ፤ እስከ መጨረሻ እስትንፋሳችን ደግሞ ይሸኙናል። እነኚህ ቃላት ገና በሙላት የእግዚአብሔር ልጆች ኣለመሆናችን ሆኖም ግን ከኢየሱስ ጥልቅ በሆነ መንገድ በመወሃሃድ ልንሆነው እና ልንኖረው የሚገባን የእግዚአብሔር ልጅነትን ይግለጡልናል፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆን ማለት ኢየሱስን መከተል ማለት ነውና።

ይህ ጸሎት የሰው ልጆች መንፈሳዊና ቊሳዊ ፍላጎቶችን ያካትታል፤ ይገልጣቸዋልም። “የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤” ሲል ዕለታዊ ፍላጎታችንና ያለንን ችግር እግምት ውስጥ በማግባት ኢየሱስ በሚቀጥለው የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ቊ 9 “እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።” ይለናል። ይህ ልመና ፍላጎታችን ለሟሟላት የምናቀርበው ጥያቄ ኣይደለም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር ያለንን ጓደኝነት ለማጠንከር ቀጥለው ባሉት ቊጥሮች “በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” በማለት መሠረታዊና ኣስፈላጊው መንፈሱ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይገልጣል። ይህንን በምድረበዳ የሚኖሩ መነኮሳንን ባህታውያን ኖረውታል፤ ሕይወታቸውን ለኣስተንትኖ በመወሰን በጸሎት የእግዚኣብሔር ጓደኞች የሆኑ፤ በኦሪት ዘፍጥረት 18፡23 32 ተጠቅሶ እንዳለው፤ የሰዶምን ከተማ ከቅጣቱ ለማዳን ኣብርሃም ለእግዚአብሔር እንደጠየቃቸው ጥቂቶች ጻድቃኖች ናቸው። የአቪላዋ ቅድስት ተረዛ እኅቶችዋን “እግዚአብሔር ከኣደጋ ነጻ እንዲያወጣንና ከፈተና እንዲያድነን ዘወትር መጸለይ ኣለብን፤ ፍላጎታችን ብቁ ባይሆንም ቅሉ በዚሁ ለመጽናት እንታገል፤ ሁሉን ወደ ሚችለው ስለምንለምን ብዙ መለመን ምን ያስቸግረናል፧ ትላቸው ነበር። የሚጸልይ ብቻው ስለማይጸልይ ኣቡነ ዘበሰማያትን በምንጸልይበት ጊዜ ድምጻችን ዘወትር ከቤተ ክርስትያን ድምጽ ጋር ያስተጋባል። ስለ ኣንቀጸ ሃይማኖት የሚያስብ ማኅበር ይህንን ለማስተማር በጥቅምት ወር 15 ቀን 1989 ባወጣው መግለጫ፤ “ቤተ ክርስትያን እንደምታስተምረው እያንዳንዱ ምእመን የክርስትያን ጸሎት እውነትና ሃብት መሻት ኣለበት ያገኘዋልም፤ በመንፈስ ቅዱስ እንዲመራ ይሁን ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር ኣባታችን ይመራዋል” በማለት ማብራርያ ሰጥቶ ነበር።

ዛሬ የትልቁ ቅዱስ ያዕቆብ ሓዋርያ በዓለም ተስታውሶ ይውላል፤ ቅዱስ ያዕቆብ ሓዋርያ ኢየሱስን ለመከተል ኣባቱንና ዓሳ የማጥመድ ሥራውን ትቶ ሓዋርያ የሆነ፤ ሕይወቱም ለክርስቶስ የሰዋ ከሓዋርያት ለመጀመርያ የተጠራ ነው፤ እንዲሁም በዚሁ ዕለት በሳንትያጎ ደ ኮምፖስተላ ለንግደት ለተሰበሰቡት ነጋድያንን በልቤ እንደማስባቸው ለመግለጥ እወዳለሁ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም የክርስትያን ጸሎት ጣዕምና ጥልቀት ለማግኘት ትርዳን ብለው ካስተማሩ በኋላ የመልኣከ እግዚአብሔር ጸሎት ኣሳርገዋል።

ከመልኣከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ፤ በጀርመን የዲዩስበርግ ከተማ ለሙዚቃ በተሰበሰቡ ወጣቶች ላይ በደረሰው ኣደጋ ሕይወታቸው ላጡት፤ ለተጐዱትና ለቤተ ሰቦቻቸው፤ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ በጀርመን የዲዩስበርግ ከተማ ብዙ ወጣቶች የጉዳት ሰለባ ያደረገ ኣሰቃቂ ዜና እጅግ ኣሳዝኖኛል፤ ሕይወታቸውን ላጡ ለቆሰሉና ቤተ ሰቦቻቸውን በጸሎቴ ኣስባቸዋለሁ።” ሲሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሓዘን ገልጠዋል።

በመጨረሻም ኣብሮዋቸው ለመጸለይና ስብከታቸውን ለመስማት ለተሰበሰቡት ምእመናንና ነጋድያን በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነው ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.