2010-07-28 12:26:34

የመግደላዊትዋ ማርያም


በላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ ትናንትና የኢየሱስ ተከታይ የሆነችውና የጌታን ትንሣኤ የመሰከረች የመግደላዊትዋ ቅድስት ማርያም በዓል ተስታውሰዋል። የጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በመጀመርያ ለቅዱስ ጴጥሮስና ለሌሎች ሓዋርያት በማብሠርዋ የሓዋርያት ሓዋርያ ብለ ይጠርዋታል። ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ የመግደላዊትዋን ማርያምን ኣስመልክተው በሰጥዋቸው ስብከቶች ልክ እንደ እርስዋ ኢየሱስን ሁል ጊዜ መፈለግ እንዳለብን በዚህም እንዳንሰልች ኣደራ ይላሉ።

መግደላዊትዋ ቅድስት ማርያም እውነትን ሳትታክት የምትሻ ሴት ነበረች። ቅድስት ኤዲት ሽታይን ስለ እርስዋ “እውነትን ትፈልጋለች እግዚአብሔርን ሳታውቀው ትፈልጋለች” ትላለች። ቅዱስ ኣባታችንም ይህንን ፍለጋ በማስታወስ ነው፤ ከጌታ ፍቅር ምንም የማይገታት ሴት፤ በጌታ ሕማማት ጊዜ ከዮሓንስ በቀር ሓዋርያት ሁላቸው ሲሸሹ እርስዋ ግን ኢየሱስን እስከ መስቀል ሥር ተከተልችው፤ ኢየሱስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላም ሌሎች ሁላቸው መቃብሩን ትተው ሲሄዱ እርስዋ ግን ባዶ መቃብር ኣከባቢ ሁና ታለቅስ ነበር፤ ኢየሱስን ትፈልግ ነበር፤ ፍለጋዋን ኣለመታከት ስለቀጠለችም ሞትን ሽሮ የተነሣውን ጌታ ለማየት በቃች።

ቅዱስነታቸው እ አ አ ሚያዝያ 11 ወን 2007 ባቀረቡት የዕለተ ሮቡዕ ኣጠቃላይ ሳምንታዊ ትምህርተ ክርስቶስ ስለመግደላዊትዋ ማርያም በዮሓንስ ወንጌል ም ዕራፍ 20፡11 ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም። ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም። ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም። ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች”። የሚለውን ሲተረጒሙ “ኢየሱስን እንደገና ኣገኘችው በስምዋ ሲጠራትም ኣወቀችው፤ እኛም ጌታን በየዋህ መንፈስና በንጽሕና የፈለግነው እንደሆነ እናገኘዋለን፤ እንዲያው እርሱ ራሱ ሊያገኘን ይመጣል፤ ይገለጥልናልም እንደ እርስዋም በስማችን ይጠራናል፤ በፍቅሩ እንድንጠመድም ያደርገናል” ብለው ነበር።

የመግደላዊትዋ ማርያም ጌታን በማግኘት የተሰማት ደስታ ወደር ኣልነበረውም፤ ኢየሱስ ግን ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ይላታል፡ ይህም የሚያስተምረን፤ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ጌታ እንደ ድሮ ዓይነት ግኑኝነት ሳይሆን ሌላ ከፍ ያለ ድረጃ ኣለ፤ ከመስቀል በፊት ወደ ነበረ ሁኔታ መመለስ እንደማይቻል ያመለክታል፤ ወደ ፊት መራመድ ያስፈልጋል፤ ቅዱስ በርናርዶስ የሚለውን እንስማ፤ ኢየሱስ ሁላችንን ወደ ኣዲሱ ሕይወት ይጠራናል፤ ወደ ሕይወት ለመሻገር ጌታን ለማግኘት ከተፈለገ ወደ ኋላ በመዞር ሳይሆን ወደ በመራመድ ነው ይላል።

ይህንን ለማድረግ እምነት እንደሚያስፈልግ እምነትም ሥነ ሓሳብ ወይም ርእዮተ ዓለም ወይም ግብረ ገብነት ሳይሆን ከሙታን ተለይቶ ከተነሣው ክርስቶስ ጋር የምናደርገው ግኑኝነትና የሕይወት ተመኩሮ ነው ሲሉ ቅዱስነታቸው የመግደላዊትዋ ማርያም የእምነት ጉዞ ሕይወትን በኣጠቃላይ የሚለውጥ ልክ እርስዋ እንዳደረገችው ትልቁን ነገር ለሌሎች ለማብሰር ጌታን ኣየሁት የሚያሰኝ ነው፤ እየውላችሁ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ኢየሱስ የሚያገኝ ሕይወቱ በኣጠቅላይ ይለወጣል፤ በእርሱ ሳያምኑ ከሞት የተነሣውን ማየት ኣይቻልም፤ እንደ መግደላዊትዋ ማርያም እያንዳንዳችን በስማችን ሊጠራን በዚህም ጥሪ የእምነት ዓይነ ልቦናችን ተከፍቶ ሕይወታችን በኣጠቃላይ እስኪለወጥ ድረስ እንጸልይ፤ እምነት ከሞት ከተነሣው ክርስቶስ ጋር በሚደረግ የግል ግኑኝነት ይወለዳል፤ የጽናትና የነጻነት መቀስቀሻ በመሆንም ኢየሱስ ከሞት ተነሣ ለዘለዓለምም ይኖራል ብሎ ለመጭህ ያስችላል፤ የሁል ጊዜ የጌታ ሓዋርያት ተል እኮም ይህ ነው፤ ከእኛም የሚጠበቀው ይህ ተል እኮ ነው ብለው ነበር።

ወንጌላዊው ሉቃስ ይህችን ቅድስት ሲገልጥ በወንጌሉ (8፡2) ሰባት ኣጋንንት የወጡላት ሴት ይላታል። በዚህም የመግደላዊትዋ ማርያም ታሪክ ወደ መሠረታዊ ሓቅ ይወስደናል፤ የኢየሱስ ተከታይ መሆን ማለት በሕይወት ዘመን ውስጥ ትሕትና በመከናነብ ቢያንስ ኣንዴ እርዳታ በመጠየቅ ሰብ ኣዊ ድካሙን በመታመን በኢየሱስ የዳነና እርሱን ለመከተል በመብቃት የእርሱ ምሕረታዊ ፍቅር ከኃጢአትና ከሞት የሚያይል መሆኑን የሚሰብክ ነው፤ በማለት በሓሞሌ 23 ቀን 2006 ዓም ባቀረቡት የመል ኣከ እግዚአብሔር ኣስተምህሮ ገልጠው ነበር።








All the contents on this site are copyrighted ©.