2010-03-03 16:39:58

የር.ሊ.ጳ. የዕለተ ሮቡዕ የትምህርተ ክርስቶስ አጠቃላይ አስተምህሮ 03.02.2010


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳጳሳት በነዲክቶስ 16 ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ የተለመደውን አጠቃላይ ሳምንታዊው የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መክፈቻ ጸሎት አሳርገው ከትንቢተ ኢርምያስ ምዕ 18:18 “እነርሱም። ሕግ ከካህን፥ ምክርም ከጠቢብ፥ ቃልም ከነቢይ አይጠፋምና ኑ፥ በኤርምያስ ላይ አሳብን እናስብ። ኑ፥ በምላስ እንምታው፥ ቃሉንም ሁሉ አናድምጥ አሉ። አቤቱ፥ አድምጠኝ፥ የክርክሬንም ቃል ስማ። ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረዋልና በውኑ በመልካም ፋንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም እናገር ዘንድ ቍጣህንም ከእነርሱ እመልስ ዘንድ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስብ።” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ ቅዱስነታቸው ዋና ትምህርቱን በሰፊው በጣልያንኛ አቅርበዋል፣ ባጭሩም የሚከተለውን ትምህርተ ክርስቶስ ለእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች አስተምረዋል። “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ በመሀከለኛ ክፍለ ዘመን ስለ ነበረ የክርስትና ባህል የጀመርነውን ትምህርተ ክርስቶስ በመቀጠል ዛሬ ከመጀመርያዎቹ የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ተከታዮች አንዱ ከነበሩ፣ ዝነኛ የንባበ መለኮት ሊቅና የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ስለ ነበሩ ቅዱስ ቦናቨንቱራ እንመለከታለን። በመሀከለኛው ክፍለ ዘመን በድኆች ወይም መንዲካንትስ የሚታወቁ፦ የፍራንቸስካውያን ማኅበርና የዶመኒካን ማኅበር የመንፈስ ጥሪ እውነተኛነት በሚመለከት ክርክር ተነስቶ በነበረበት ጊዜ ቅዱስ ቦናቨንቱራ ይህንን ለመከላከል ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። የእነዚህ ማኅበራት ወንድማሞች በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠውን የብፅዕና ሕይወትን የተመለከተ የወንጌል ምክርን በመከተል በድህነት በንጽሕናና በተአዝዞ እውነተኛ የሃይማኖት ሕይወት እንደሚያዘወትሩ አስረድተዋል። የንኡሳን አኅው አበምኔት ተመርጠው ለ17 ዓመታት በችሎታና በመንፈስ ማኅበሩን አስተዳድረዋል። በቅዱስ ቦናቨንቱራ ጊዜ የፍራንቸስካውያን ጥሪ እውነተኛነት ብዙ ክርክር ተነሥቶ ነበር። ቅዱስ ቦናቮንቱራ ግን በነበራቸው ጥበብና ብልኃት የማኅበሩን ሕግ በማጽደቅና የቅዱስ ፍራቸንኮስ ገድልና ሕይወት በማቅረብ ቅዱስ ፍራቸስኮስ ማኅበሩን ሲመሥርት ክርስቶስ በልበ ምሉነት በመከተል አልተር ኪርስቱስ ማለት የክርስቶስ ምትክ በመሆን ነው ሲሉ የፍራንቸስካውያን ማኅበር በጽናት የመሥራቹ መንፈስን እንደሚከተል አድርገዋል።

ቅዱስ ቦናቨንቱራ ከዚህ በኋላ መጀመርያ አቡን ቀጥሮም ካርዲናል በመሆን ቤተ ክርስትያንን በብቃትና በትጋት ካገለገሉ በኋላ ከልዮን ጉባኤ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የቅዱስ ቦናቨንቱራ ጽሑፎች በትልቁ የክርስቶስ ፍቅርና እግዚአብሔር ለማየት በነበረው ትልቅ ጉጉት እና በሰማያዊው ቤታችን ስላለው ደስታ በማስተንተን የተጻፉ ስለሆነ ዛሬም ገና የመንፈሳዊ ዕውቀትና አስተንትኖ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ናቸው።”








All the contents on this site are copyrighted ©.