2010-02-15 16:16:55

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ(14.02.2010)


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንት ጥዋት በሮማ ሃገረ ስብከት ካሪታስ የሚተዳደረውን በተርሚኒ ምድር ባቡር ጣቢያ የሚገኘውን የድኆች መመገቢያና መጠለያ ከጐበኙ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በብዙ ሺ ለሚገመቱ ምእመናን የተለመደውን የእሁድ ጉባኤ አስተምህሮ አቅርበዋል። ትምህታቸውም እንደሚከተል ነበር።

“ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ የሥርዓተ አምልኮ ዘመናት ቤተ ክርስትያን በድንግል ማርያም ተመርታ የምትፈጽመው ትልቅ የእምነት ጉዞ ነው። የዛሬው መደበኛው የሥርዓተ አምልኮ ዘመን ሰንበት ወደ ዘመነ ጾም የምንሸጋገርበት ሆኖ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ይደመደማል። የዕለቱ ወንጌል ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቍ. 17 “ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፥ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ።” ይላል። በዚሁ አጋጣሚ የብፅዕና ንግግሩን ያደርጋል፣ እነኚህ ንግግሮች በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ከቍ.1-12 እናገኛቸዋለን። ወንጌላዊው ሉቃስም በምዕራፍ 6 ከቍ.20-26 አስፍሮታል፣ “ኢየሱስ መለስ ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው። እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።  እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ።” ይላል። ለምን ብፁዓን ይላቸዋል፣ ምክንያቱ የእግዚአብሔር ጽድቅ ወይም ፍትሕ ይክሳቸዋል፣ ከወዲያውኑ ጀምሮ በመንግሥቱ ይቀበላቸዋል። የብፅዕና ጉዳይ በመልእልተ ባህርያዊ ፍትሕ ይመሠረታል። ይህ ፍትሕ በስሕተት የተዋረደውን ከፍ ያደርጋል፣ ራሱን ከፍ ያደረገውን ያዋርዳል። ስለዚህም ነው ወንጌላዊው አራት የብፅዓን ተስፋ ከሰጠ በኋላ፣ እነዚህን የሚጻረሩ “ወዮላችሁ” ሌሎች አራት ጉዳዮች ይዘረዝራል፣ “እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።” በማለት ሁሉም የተገላቢጦሽ እንደሚሆን ይነግራል፣ ወንጌላዊው በምዕራፍ 13 ቍ.30 ላይ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፣ ሲል ሁሉ ነገር የተገላቢጦሽ እንደሚሆን ይነግራል።

ይህ ፍትሕና ብፅዕና በዓለም መጨረሻ ላይ በሰማያዊው መንግሥት ወይም በእግዚአብሔር መንግሥት እውን ይሆናል።ሆንም ግን ይህ መንግሥት መሀከላችን አለ፣ ድኆች በተጽናኑበትና በማእድ በቀረቡበት ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ይገለጣል፣ የጌታ ሐዋርያት ይህን ለማወጅ ነው የተላኩት፣ ባለነው ኅብረተሰብም ይህን ነው ማድረግ ያለብን። ዛሬ ጥዋት በሮማ ሃገረስብከት ካሪታስ በሚካሄደው በተርሚኒ ያለው መጠለያ ያደርግሁት ጉብኝትን አስታውሳለሁ፣ በዚሁ የፍቅርና የፍትሕ ግብረ ሠናይ ተቅዋምና በሁሉም የዓለም ክፍሎች ይህን ዓይነት ተግባር ለሚፈጽሙ ሁሉ የልቤን ድጋፍ እገልጻለሁ።

ዘንድሮ የላክሁት የአርባ ጾም መልእክት ይዘት ስለፍትሕ ይናገራል። በዚሁ አጋጣሚ ሁላችሁ እንድታነቡትና በእርሱ ላይ እንድታስተነትኑ አደራ እላለሁ፣፣ የኢየሱስ ወንጌል የሰው ልጅ ለፍትሕ ያለውን ጥማት የሚያረካ ነው፣ ይህ ግን ባልጠበቁትና በሚያደንቅ መንገድ ነው የሚሆነው። ኢየሱስ ኅብረተሰብአዊና ፖሎቲካዊ አብዮት አይደለም የሚያቀርብልን፣ በመስቀሉና በትንሣኤው እተግባር ላይ ያዋለውን የፍቅር ለውጥ ነው የሚያቀርብልን። በዚሁ ለውጥ ብፅዕና ይመሠረታል፣ ይህም በፋሲካ የሚዘከረውን የፍትሕ መዓዝንን በማሳየት ፍትሓውያን እንድንሆንና የተሻለ ዓለም ለመንገንባት ይረደናል።

ውድ ጓደኞቼ ወደ ድንግል ማርያም እንመለስ፣ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ብሎ ይጠራታል፣ ምክንያቱም ጌታ ባወጀው የድኅነት መልካም ዜና ስላመነች፣ በዚሁ የጾም ግዜ ራሳችን የቻለን መስሎን ከመቃዠት ነጻ አውጥታ እግዚአብሔርና ምህረቱ እንደሚያስፈልገን ተረድተን በመንግሥቱ ማለት በጽድቅ በፍቅርና በሰላም መንግሥቱ እንድንገባ እርስዋ እንድትመራን ይሁን፣” ካሉ በኋላ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አስርገዋል።

ቅዱስነታቸው ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ትናንትና በኤስያ እነ ቻይናና ቬትናም ባሉ አገሮች ርእሰ ዓመታቸው ለሚያከብሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጠው፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ትምህርታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.