2009-12-14 17:26:51

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮ


እውነተኛ የክርስትያን ደስታና የልደት ግርግም: የእውነተኛ ደስታ ምንጭ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ በመሆኑ ነው፣ ሲሉ ቅዱስ ኣባታችን ትናንትና የመልአከ እግዚአብሔር ከማሳረጋቸው በፊት የፍቅር የትሕትናና የደኅንነት ምልክት የሆነውን የልደት ግርግም ለማዘጋጀት የሚያገልግሉትን ምስሎች ባርከዋል። በመጨርሻም በዚሁ ቀናት በአፍሪቃ የተገደሉትን አራት ሰባክያነ ወንጌልን በማስታወስ ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው የተለመደውን ሰላምታ አቅርበው፣ “እውነተኛ ደስታ የሚሰጠን ስሜት የያንዳንዳችንና የማኅበረሰባችን በሕይወት መኖር በጌታ እንደሚጠበቅና ሁል ጊዜ በትልቁ የእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ መሆኑን ማወቅ ነው” ሲሉ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎትና ለተለመደው ለልደት ምስሎች የሚሰጥ ቡራኬን ለመከታተል ለተሰበስቡ ምእመናንና ነጋድያን አስተምረዋል።

“የተከበራችሁ ሁላችሁንም በትልቅ ስሜት ሰላም እላለሁ እስከ እዚህ ድረስ በመምጣታችሁም አመሰግናለሁ፣ በቤተ ሰቦቻችሁ የልደት ግርግም መዘጋጀት ልማድ መኖሩ ደስ ያሰኘኛል፣ ነገር ግን የልማድ ነገርን መድገም ብቻ በቂ አይደለም፣ የልደት ግርግም የሚያመለክተውን የኢየሱስ ክርስቶስ መሀክላችን መገኘት የእርሱ ፍቅር ትህትናና ድህነት በዕለታዊ ኑሮአችን በእውነት መኖር አለብን” ብለዋል።

በላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ግጻዌ የትናንትናው እሁድ 3ኛ የምጽአት እሁድ በመሆኑ፣ ቅዱስነታቸው ይህንን አስመልክተው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ያደረገውን እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፣ “ቅዱስ ፍራንቸስኮ በግረቾ የልደት ታሪክን በሕያው ትያትራዊ ዓይነት በማቅረብ በበለጠ ለማስተንተንና ልደትን ለማክበር ችለዋል፣ በተለይ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ለእኛ ሲል ያደረገው ማለት ስለ ፍቅራችን ሁሉንም ትቶ ትንሽ ሕፃን በመሆን የሰጠንን መልእክት በተግባር ለማሳየት ነው፣ የልደት ግርግም ማዘጋጃ ምስሎችን ስንባርክ የልደት ግርግም የሕይወት ትምህርት ቤት መሆኑን ያመልክታል፣ የልደት ግርግምን ስንመለከት ድንግል ማርያምን ቅዱስ ዮሴፍ የታደሉ ቤተ ሰብ አይመስሉም፣ የመጀመርያ በኵር ልጃቸውን በብርቱ ችግር መሀከል ነው የወለዱት፣ ሆኖም ግን ስለሚዋደዱና እርስ በእርሳቸው ስለሚረዳዱ ከሁሉም በላይ ደግሞ በታሪካቸው የእግዚአብሔር ሥራ መኖሩ ማለትም በሕፃኑ ኢየሱስ የተፈጸመው በትልቅ ውሳጣዊ ደስታ ይመላቸዋል። እረኞቹስ፤ በደስታ የሚሞላቸው ምን ነበር፣ እርግጥ ሕፃኑ የኑሮ ሁኔታቸው አይቀይርም ደህነታቸውም ይሁን የተገለሉ መሆናቸው በሕፃኑ አይለውጥም፣ ሆኖም ግን በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ በበረት በከብት መመገቢያ ግርግም ተኝቶ በሚያገኙት ሕፃን እግዚአብሔር ለሚያፈቅራቸው የሰው ልጆችና ለእርሳቸውም ሳይቀር የተሰጠው ተስፋ እንዲሚፈጸም ለማየት እምነታቸው ይረዳቸዋል። ደስ እንዲለን ገንዘብና ነገሮች ብቻ ኣይደሉም የሚያስፈልጉን፣ ፍቅርና እውነት ያስፈልጉናል፣ ልባችንን የሚያሞቅና ለምንፈልጋቸውና ለምንጠብቃቸው ነገሮች መልሽ የሚሰጥ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር አጠገባችን የሚኖር እግዚአብሔር ያስፈልገናል፣ ይህም ከድንግል ማርያም በተወለደው ኢየሱስ እውን ሆነ፣ በዘመነ ልደት በልደት ግርግም የምናኖረው የኢየሱስ ሕፃን ምስል የሁሉም ነገር ማእከል ነው፣ የዓለም ልብ ነው፣” ካሉ በኋላ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገዋል።

ከጸሎቱ በኋላ በሮማ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች የጸሎትና የመንፈሳዊ ኵስኰሳ ቦታዎች ለሚያዘጋጁ በተለይም ይህንን ዕለት “የአዲስ አብያተ ክርስትያን ዕለት” በመሰየም የሚያከብሩትን ባለ በጎ ፈቃድ ሰዎች ስለቸነታቸውና ለቤተ ክርስትያን ስለሚያደርጉት እርዳታ አመስግነዋል፣ በመጨረሻም በዚህ ቀናት በአፍሪቃ ለተገደሉት 4 ልኡካነ ወንጌል በማስታወስ እንዲህ ብለዋል፣ “ኣብ ዳኒኤላ ቺዚምያ ኣባ ልዊስ ብሎንደል ኣባ ጀርይ ሮሸ እና እናቴ ደኒስ ካሃምቡ የሚባሉ ታማኝ ሰባክያነ ወንጌል እና በጽናት ጌታን በደማቸው ሳይቀር ለመመስከር የበቁ ናቸው። በትልቅ ሓዘን ለሚገኙ ለቤተሰቦቻቸውና ለማኅበሮቻቸው ቅርበቴን እየገለጽሁ፣ ጌታ ነፍሳቸው በመንግሥቱ እንዲቀበልና በሓዘን ለተጎዱት ጽናት እንዲሰጥ በልደቱም ዕርቅና ሰላም እንዲያመጣ በማሳርገው ጸሎት ሁላችሁ እንድትሸኙን እማጠናለሁ፣” ካሉ በኋላ ለሁላቸውም በተለያዩ ቋንቋዎች በማመስገን ሓዋርያዊ ቡራኬ ቸሩ።








All the contents on this site are copyrighted ©.