2009-10-21 13:15:21

ሁለተኛው የአፍሪቃ ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የጉባኤው ማጠቃለያ ሰነድ


እዚህ በቫቲካን በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪቃ ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የጉባኤው ማጠቃለያ ሰነድ በይፋ ማቅረቡ ተገለጠ። ይህ እርቅ ፍትሕ እና ሰላም በሚል ዋና ርእስ ተመርቶ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪቃ ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወደ ፍጻሜው በመቃረብ ላይ መሆኑ ሲነገር፣ ትላትና በ17ኛው ቀነ ጉባኤው በሚቀጥሉት ቀናት ድምጸ ውሳኔ የሚሰጥበት የማጠቃለያው ሰነድ በይፋ RealAudioMP3 በማቅረብ መወያየቱ የሲኖዶስ የግኑኝነት እና የማስታወቂያ ጉዳይ ጽ/ቤት ካሰራጨው ዜና ለማወቅ ተችለዋል። ይህ በንዲህ እንዳለም ብፁዓን የሲኖዶስ አበው ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ በተገኙበት የጉባኤው ሂደት በአፍሪቃ የዓበይት ሓይቆች ክልል ሰላም ይረጋገጥ ዘንድ ጥሪ በማቅረብ፣ በአሥርቱ ትእዛዛት ቁጥር 6 አትግደል የሚለው በሰው ልብ ዘንድ ታትሞ ያለው ትእዛዝ መርህ በማድረግ የቀረበው የሰላም ጥሪ፣ የጦር መሣሪያ በውይይት ባህል ይተካ ዘንድ በማሳሰብ በጦርነት እና በግጭት ካልሆነ በስተቀረ በሰላም የሚጠፋ ምንም ነገር እንደሌለ በቀረበው የሰላም ጥሪ ተመልክቶ ይገኛል።

ጉባኤው ባቀረበው የሲኖዶስ ማጠቃለያ ሰነድ ሰላም እና እርቅ ተደጋግሞ የተጠቀሰበት መሆኑ ሲነገር፣ ይህ ሁለተኛው፣ የአፍሪቃ ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጰራቅሊጦስ የሚል መጠሪያ የተሰጠው እና የአፍሪቃ ኅብረተሰብ ለመተባበር የሚያነቃቃ፣ የትብብር ሓዋርያዊ ግብረ ኖልዎ እንዲረጋገጥ የሚያሳስብ መሆኑ ተገልጠዋል።

ሰነዱ፣ በአፍሪካ ከተለያዩ ሃይማኖቶች በተለይ ደግሞ ከእስላም ሃይማኖት ጋር የሚደረገውን ውይይት ላይ በማተኮር እ.ኤ.አ. በ 1986 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በአሲዚ የተካሄደው የሁሉም ሃይማኖቶች የጋራ ስርዓተ ጸሎት፣ የሃይማኖት እና የአምልኮ ነጻነት እንዲከበር የሚያሳስበውን መልእክት ብጹዓን የሲኖዶስ አበው በማስተጋባት፣ በአፍሪቃ አቢያተ ክስርትያን እውቅና እንዲኖራቸው እና የተወረሱባቸው ንብረት ይመለስላቸውም ዘንድ በማሳሰብ፣ ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት እንዲወገድ የሚጠራ መሆኑ ተረጋገጠዋል። ለአፍሪቃ ባህላውያን ሃይማኖቶች ከወዲሁ በር ከመዝጋት ፈተና ተላቆ ቀርቦ በማወቅ እና በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ቲዮሎጊያ መሠረት ተጠንተው ግኑኝነት እንዲደረግ ብፁዓን ጳጳሳት በማሳሰብ፣ ቤተ ክርስትያን ከተለያዩ የሴራ ሃይማኖቶች የሚሰነዘርባት ፈተና የማሸነፍ ብቃት እንዲኖራት እና እንዲሁም የጥንቆላ እና የምትሃት ተግባሮችን በኃይል በመቃወም የነዚህ ጎጂ ተግባሮች ሰለባ የሆኑትን ቀርባ በማነጽ ከወደቁበት ስነ አእምሮአዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ጉዳት እንዲላቀቁ ኣ ለዚህ ዓላማ ያተኮረ ግብረ ኖልዎ ማነቃቃት እንደሚገባት ብፁዓን አበው በማጠቃለያው ሰነድ ያመለክታሉ።

አፍሪቃን ለተለያዩ ችግሮች ከሚያጋልጡዋት አንዱ የምሁራንዋ ስደት መሆኑ ብፁዓን ጳጳሳት በማሳወቅ አፍሪቃውያን ምሁራን በአፍሪቃ ለአፍሪቃ እርባና እና እድገት እንዲጠመዱ ለስደት የሚዳርጋቸውን ምክንያቶች እንዲፈቱ በማሳሰብ፣ በመቀጠል አፍሪቃን ከእድገት ጎዳና ውጭ እያደረገ ያለው የውጭ አገር የብድር ጫና እንዲሰረዝ እና የተናንሽ ብድር መርሃ ግብር በዚህች ክፍለ አለም እንዲስፋፋ እፊታችን ዓርብ ድምጽ ይሚሰጡበታል በሚባለው የማጠቃለያ ሰነድ ውስጥ አስምረውበታል።

ጥልቅ እና ወደር የማይገኝለት የቤተ ክርስትያን ማኅበራዊ ትምህርት በሚገባ በዚህች ክፍለ አለም እንዲጠና እና እንዲስፋፋ፣ ሁሉም እንዲረዳውም በሕንጸት መርሃ ግብሮች አማካኝነት በማሰራጨት በሁሉም ደረጃ ይንጸባረቅ ዘንድ ማነቃቃት እንደሚያፈልግ ሰነዱ ያመለክታል። ከዚህ ጋር በማያያዝም የአፍሪቃ ተፈጥሮአዊ ሃብት ጥበቃ ለአፍሪቃ እድገት ወሳኝ መሆኑ ብጹዓን የሲኖዶስ አበው በማሳሰብ፣ የጦር መሣሪያ ንግድ፣ የብዙ አፍሪቃውያን ሕይወት እየቀጨ ያለው በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ከቦታ ቦታ የማዘዋወሩ ተግባር ጭምር እንዲወገድ፣ አፍሪቃውያን ስደተኞች ከማውገዝ እና ላደጋ ከማጋለጥ ይልቅ፣ የስደተኛው ሰብአዊ መብት እና ፈቃድ ይከበርላቸው ዘንድ ብፁዓን የሲኖዶስ አበው ጥሪ በማቅረብ ለስደት የሚዳርጋቸው ምክንያት መጤን አለበት ብለዋል። ቀጥለውም በዓለማችን እውን እይሆነ በመምጣት ላይ ያለው ዓለማዊ ትሥሥር በሥነ ምግባር የተለካ እና ትብብር የሚያነቃቃ መሆን እንደሚገባውም በማሳሰብ፣ የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ለአፍሪቅ እድገት እንጂ የግጭት እና የውጥረት ምክንያት እንዳይሆን፣ በአፍሪቃ ኅብረ ኢንዳስትሪዎች የሚፈጸሙት ለአፍሪቃ እድገት ያላቀና የብዝበዛ ተግባራቸውን እንዲገቱ በማሳሰብ፣ የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ለአፍሪቃ ልማት በሚል ውሳኔ እንዲስተጋባ እና እግብር ላይ እንዲውል ብፁዓን አበው በማጠቃለያው ሰነድ አመልክተዋል።

ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጋገጥ መሠረት የሆነው ነጻው ሕዝባዊ ምርጫ ዋስትና ይኖረውም ዘንድ፣ መንግሥታት የዲሞክራሲው ሥርዓት የሚያቆማቸው፣ ግልጽ ከማንኛው ዓይነት አድልዎ ነጻ መሆን እንደሚገባቸው ብፁዓን አበው በማሳሰብ፣ የህዝብ ውሳኔ ሕጋዊ ኃላፊነት የሚያስረክባቸው ያመራር አካላት እንጂ፣ ኃይል ተገን ያደረገ መንግሥት ለአፍሪቃ ጉዳት መሆኑ በማስገንዘብ፣ በፖሊቲካው መድረክ የሚሳተፉ ካቶሊክ ምእመናን ወንጌላዊ ሕይወት እንዲያንጸባርቁ እና እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች ለማንም ወገን የማያደሉ የሕዝብ እና አገር ጥቅም ላይ ያተኮሩ መሆን እንደሚገባቸው ብፁዓን ጳጳሳት በማሳሰብ፣ ጽንስ ማስወረድ እናታዊ ባኅርይ የሚያንቋሽሽ፣ ላደጋ የሚያጋልጥ የቤተሰብ ክቡርነት የሚቀናቀን ተግባር ሁሉ እንዲወገድ እና አፍሪቃን እያሰቃየ ያለው ቀዛፊው የኤይድስ በሽታ፣ ድህነት እንዲወገድ ለዚህ የሚያበቃ መርሃ ግብር በአፍሪቃ አቀፍ እንዲረጋገጥ በማሳሰብ የሞት ፍርድ በመቃወም የሕይወት ባህል እንዲስፋፋ እና ቤተ ክርስትያን በመገናኛ ብዙኅን በኩል ንቁ ተሳታፊ ሆና ለኅብረተሰብ ህንጸት ቀዳሚ ሚና መጫወት እንደሚገባት ብፁዓን አበው አስገንዝበዋል። በመጨረሻም የዛሬ 40 ዓመት በፊት የተቋቋመው በአፍሪቃ ለመንፈሳዊ ለሰብአዊ እና ለማኅበራዊ እድገት አቢይ አስተዋጽኦ በመስጠት ላይ የሚገኘውን የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ብፁዓን የሲንዶስ አበው በማመስገን ጉባኤው በአፍሪቃ ማኅበረሰብ ያለው ንቁ ተሳትፎ ያጎለብት ዘንድ የማጠቃለያው ሰነድ ያስገነዝባል።








All the contents on this site are copyrighted ©.